Wednesday, May 14, 2014

መሠረታዊ የአገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም የክልልና የፌደራል መንግሥታትን አከራከረ

May14/2014

-ለጋሾች በበጀት አጠቃቀም ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው
የመሠረታዊ አግልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ለጋሽ አገሮች መንግሥት ላይ ባሳደሩት ጫና ነበር፡፡
በተለይ የአውሮፓ ኅብረት ከምርጫው ማግሥት በኋላ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ መንግሥትን በመኮነን ለአንድ ዓመት ያህል ዕርዳታ ከመስጠት ታቅቦ ቆይቶ ነበር፡፡

ሆኖም ለጋሽ አገሮች በቀጥታ ድሀ ተኮር የሆኑ ፕሮግራሞች በአግባቡ ስለመተግበራቸው እርግጠኛ ለመሆን፣ በጋራ ከማቀድ ጀምሮ አፈጻጸማቸውና ያስገኙትን ውጤት በጋራ መገምገም የሚያስችላቸውን መድረክ ከመንግሥት ጋር በመፍጠር ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ በያመቱ የአሥር ቢሊዮን ብር ዕርዳታ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተተገበረውንና በ2005 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም የግማሽ ዓመት የበጀትና ዕርዳታ አፈጻጸም ግምገማ ከለጋሽ አገሮች ጋር በግዮን ሆቴል ማካሄድ የተጀመረው ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ በመጪው ግንቦት 8 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

በግምገማው መክፈቻ ወቅት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በጤና፣ በትህምርት፣ በግብርና፣ በውኃና በመንገድ ንዑስ ዘርፎች ላይ ለጋሾች ለአፈጻጸማቸው የገንዘብ ድጎማ ያደርጋሉ፡፡ የሠራተኞችን ደመወዝ፣ የሥራ ማስኬጃ በጀትና ሌሎች ወቅታዊ በጀት የሚያካትታቸውን የፕሮግራሙን ወጪዎችን ይደጉማሉ፡፡ በተለይም በሰው ኃይልና በአስተዳዳራዊ ዘርፎች፣ በፋይናንስና በጀት ግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ ያተኩራሉ፡፡ በመሠረታዊ አግልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ  እስካሁን የታዩ ለውጦች ጥሩ የሚባሉ ቢሆኑም፣ በታዳጊ ክልሎች የተመዘገቡት ለውጦች ከታቀደው በታች ነው በማለት መረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተውጣጥቶ የቀረበው የ2005 በጀት ዓመት የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም ውጤቶች ሪፖርት ላይ ጥቂት የማይባሉ መስኮች ላይ ከታቀደው በታች ውጤት መመዝገቡን ቢገልጽም፣ ክልሎች ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡

በትምህርት መስክ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ላይ የተመዘገቡትን ውጤቶች በማስመልከት ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እንዳቀረበው፣ ባለፈው በጀት ዓመት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የተመዘገው የተጣራ የተማሪዎች ቁጥር 86 ከመቶ አቅራቢያ ነው፡፡ በዕቅድ ይመዘገባል የተባለው መጠን ግን 94 ከመቶ ገደማ ነው፡፡ ይህም ማለት በመላ አገሪቱ ከአንድ እስከ ስምንት የሚሰጠው የትምህርት አገልግሎት ሽፋን 94 ከመቶ ይደርሳል የሚል ነበር፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባለው የትምህርት ዕርከንም ይጠበቅ የነበረው የተማሪ ቁጥር 69 ከመቶ አቅራቢያ ሲሆን፣ በተጨባጭ የተመዘገበው ግን 47 ከመቶ በመሆኑ ከዕቅዱ በብዙ ርቆ ታይቷል፡፡ የስምንተኛ ክፍልን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ቁጥር በአገር አቀፍ ደረጃ 53 ከመቶ አቅራቢያ ሲሆን፣ ይጠበቅ የነበረው ግን 78 ከመቶ ይደርሳል ተብሎ ነበር፡፡

ከ86 ከመቶው አገራዊ አማካይ ውጤት በታች ውጤት አስመዝግበዋል የተባሉት ክልሎች፣ አፋር ክልል 42 ከመቶ በማስመዝገብ ዋናው ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 69 ከመቶ፣ ሐረሪ ክልል 75 ከመቶ በማስዝገብ ወደኋላ መቅረታቸው ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በመምህራን ሥልጠናና ብቃት ላይም አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌና ደቡብ ሕዝቦች በዝቅተኛ ደረጃ ውጤት ያሳዩ ተብለው ተተችተዋል፡፡

የቀረቡትን አኃዞች የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ የአፋርና የሶማሌ ክልሎች አጣጥለዋል፡፡ የአፋር ክልል ያጣጣለው የራሱን መረጃ በማጣቀስ ሲሆን፣ በክልሉ የሠለጠኑ የአንደኛ ደረጃ መምህራን ቁጥር 95 ከመቶ ደርሶ እያለ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር 53 ከመቶ አቅራቢያ ነው ማለቱ ከምን በመነሳት እንደሆነ እንዲገለጽለት ጠይቋል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በተማሪዎች ቁጥር ላይ ያለበትን ችግር ይፋ አድርጓል፡፡ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዕድሜያቸው የደረሱ ሕፃናት ትምህርት የሚጀምሩት በሰባተኛ ዓመታቸው ነው፡፡ ቢሮው አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ዕድሜም 14 ዓመት መሆኑን ገልጾ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ውስጥ 40 ከመቶው በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩና ከተቀመጠው የትምህርት ዕድሜ በታች የአንደኛ ደረጃ ትምርትን የሚጀምሩና የሚያጠናቅቁ በመሆናቸው፣ ስታቲስቲካዊ መረጃ አያያዝ ላይ መቸገሩን አመልክቷል፡፡

በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩት ሕፃናት አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚጀምሩት በስድስት ዓመታቸው ሲሆን፣ የሚያጠናቅቁትም በ13ኛ ዓመታቸው ነው፡፡ ይህንን የገለጸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ከዚህ ባሻገርም ከመደበኛው የትምህርት ዕድሜ በላይ የሆኑ ታዳጊዎች በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ በመሆኑ እነሱም የሚያካትት አኃዝ እንዳልቀረበ ይፋ አድርጓል፡፡

የትምትርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሒም በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን ተማሪዎች በአገሪቱ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ሁለት ሚሊዮን አዲስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታው መምጣት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ማቋረጥና መቅረት አሳሳቢ መሆኑን ያመኑት አቶ ፉአድ፣ ይህም ሆኖ በመረጃ አሰባሰብ ላይ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጋር ልዩነት እየታየ በመሆኑ የአኃዝ ተቃርኖ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው የሚሰበስበው መረጃ በቤሰተብ ደረጃ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ግን ከየትምርት ቤቶቹ መረጃ የሚሰበስብ በመሆኑ በመረጃ ምንጭ ላይ ያለው ልዩነት ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከቀረበው የዕድሜ ጉዳይ በተጨማሪ 44 ትምህርት ቤቶች ለግምገማው አለመካተታቸውን አቶ ፉኣድ ተናግረዋል፡፡

በግብርና በኩል የታየው ችግር በኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቁጥር ላይና በምርታማነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በሔክታር ይጠበቅ የነበረው ምርት ከ19 ኩንታል በላይ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን በሔክታር 18 ኩንታል አልሞላም፡፡ በዋና ዋና ሰብሎች ላይ የታየው አዝጋሚ ምርታማነት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ወደ ኋላ ሊቀር ችሏል ተብሏል፡፡ በዚህ አኃዝ ላይ ደስተኛ ያልሆኑት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ ያለፈው ዓመት መረጃ የዚህን ዓመት አፈጻጸም ሊገልጽ የማይችል ከመሆኑም በላይ፣ ባለፈው ላይ ከመነጋገር አሁን ባለው ላይ መወያየት እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡ በዚያም ላይ ባለፈው ዓመት የተዘራው በዚህ ዓመት ውጤት የሚሰጥ በመሆኑ ምክንያት፣ ያለፈው ዓመት ዝቅተኛ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጤና በኩልም በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣት ላይ ሪፖርት ቀርቦ ጤና ጥበቃ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በድኅረ ወሊድ እንቅብካቤና በፀረ አምስት ሦስተኛ ዙር ክትባት አግልግሎት ላይም የታዩ ለውጦች ለቤቱ ቀርበዋል፡፡  ጤና ጥበቃ የመረጃ ጥራትና ብዛት፣ የአስተዳደር ችግር፣ ከታሰበው ዓላማ ማፈንገጥ የመሳሰሉት ችግሮች በክልሎች እያጋጠመው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በመንገድ ዘርፍ ላይ የታውን በተመለከተ እንደቀረበውም ከዚህ በፊት በሁሉም ዓይነት የአየር ጠባይ የሚያገለግሉ መንገዶች ሽፋን እተሸሻለ መምጣቱ ታይቷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ወደ እነዚህ መንገዶች ለመድረስ 3.7 ኪሎ ሜትር መንገድ መጓዝ ይጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ወደ 2.1 ኪሎ ሜትር ዝቅ ማለቱ ተጠቁሟል፡፡ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ መንገዶች ሽፋን 90 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በዕቅድ የሚጠበቀው ግን 85 ከመቶ ገደማ ነበር፡፡

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባሻገር የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ተቋም (ደፊድ)ም በበጀት፣ በፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም በሌሎች መስኮች ላይ ታይተዋል ያላቸውን ጉድለቶችና ጥሩ ውጤቶችን አስገኝተዋል ያላቸውን አፈጻጸሞች ገምግሟል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተርና የለጋሽ አገሮች ተወካይ ጉዋንግ ዚ ቼን እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳ ላለፉት ሦስት ዙሮች ሲተገበር የቆየው ፕሮግራም ለውጦችን ቢያስመዘግብም ችግሮች ግን አልተለዩትም፡፡ በመሠረታዊ አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራሙ ላይ ከሚቀርቡ ዕቅዶች ውስጥ በበጀት አጠቃቀም ላይ የታዩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመንገድ ዘርፉ ላይ የሚመደብ ፈንድ በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋሉ፣ የሀብት አመዳደብ ችግር፣ የበጀት አደላደል፣ የመረጃ ምንጭ ላይ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጥራት ያለው መረጃ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ባሉ መዋቅሮች ላይ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት ቼን፣ የአገልግሎት አሰጣጡ በሠራተኛው ላይ የሚንጠለጠል በመሆኑም የሰው ኃይል ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በውኃ አቅርቦቶች ላይ የፌደራል መንግሥት ድጋፍ በሚሰጣቸው ታዳጊ ክልሎች ላይ ጎልቶ ታይቷል፡፡ ይህንን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋራቸው የዓለም ባንክ ዳይሬክተር፣ ክልሎቹ ራሳቸው ከዝቅተኛ ደረጃ ላይ እየተነሱ ያሉ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ምንም እንኳ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እየተሻሻለም ቢሆንም፣ ዕርዳታ ሰጪ አገሮች ቃል ከገቡት ውስጥ የተወሰነ መጠን እስካሁን እንዳልቀቁና በቀሩት ወራት ውስጥ በጀቱን እንዲለቁ አሳስበው ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው ቼን በበኩላቸው አልተቀቀም የተባለው በጀት በዝቅተኛ አፈጻጸም ጋር የተያያዘ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ በተለይ የተመደበው ገንዘብ እንዴትና በምን አኳኋን ሥራ ላይ እንደዋለ በአግባቡ መረጃ ስለማይገኝ፣ የሚሰጠው ዕርዳታ ሊዘገይ መቻሉን ቼን ተናግረዋል፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የቻናል አንድ ፕሮግሞች አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ነገራ ግን በታቀደው መሠረት ገንዘብ መለቀቁን ይናገራሉ፡፡ ለ2005/2006 በጀት ዓመት ፈሰስ ይደረጋል የተባለው በሙሉ ተለቅቋል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ከግንቦት ወር በኋላ መለቀቅ አለበት ተብሎ በሚጠበቀው የበጀት መጠን ላይ ያተኮረ ግምገማ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

No comments: