Thursday, October 23, 2014

ከምርጫ ’97 ‹የተማረው› ኢህአዴግና የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ

October 23,2014
በላይ ማናዬ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ከሰሞኑ ለመነሻ ያህል የቀረበ ነው በሚል ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ለፓርቲዎቹ ለማስተዋወቅ ሞክሮ ነበር፡፡ ይህን የጊዜ ሰሌዳና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከፓርቲዎቹ ጋር ለመምከር በሶስት ዋና ዋና ከተሞች (አዲስ አበባ፣ አዳማ እና ሀዋሳ) ፓርቲዎቹን ከፋፍሎ ለውይይት ጠርቶ የነበረ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ፓርቲዎች መድረኩን ጥለው መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ 

ፓርቲዎቹ የምርጫ ጊዜውን በተመለከተ ከመነጋገራችን በፊት በርካታ ልንነጋገርባቸውና ሊስተካከሉ የሚገቡና በደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ የገለጽናቸው ጉዳዮች ስላለሉ ለእነዚያ ጉዳዮች ቅድሚያ መሰጠት ይገባዋል ከሚል መነሻ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ቦርዱ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እንዳለ የቀጠለ ቢሆንም፡፡

ያም ሆነ ይህ ምርጫ ቦርድ ለውይይት ያቀረበው ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ስንመለከት አንድ ነገር እንድንገነዘብ ያደረገ ሆኗል፡፡ ይኸውም ቦርዱ ቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችን በተመለከተ ለሚሰሩ ስራዎች በቂ ጊዜ ያለመመደቡን ነው፡፡ ለፓርቲዎቹ የክርክርና የቅስቀሳ ጊዜ የተመደበውን ስናይ ፕሮግራሙ በእጅጉ ወደፊት የተገፋ መሆኑንና በቂ ጊዜ ያለመስጠቱን መመልከት ይቻላል፡፡ ይህም በተለይ ለገዥው ፓርቲ በብዙ መልኩ ጠቃሚ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ገዥው ፓርቲ፣ አንድም ልክ እንደ 97 ምርጫ ከተቃዋሚዎቹ ጋር በግልጽ የክርክር መድረክ ሀሳቦቹን ማቅረብ አለመሻቱን (የደረሰበትን ሁሉ ስለማይዘነጋ)፣ ሁለትም ህዝብ በቂ የቅስቀሳ ጊዜ ተመድቦ አማራጮችን በሚገባ ለማየት እድል እንዳይኖረው መፈለጉን በገደምዳሜ በቦርዱ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በኩል ያንጸባረቀ ይመስላል፡፡

በእርግጥ መንግስት/ገዥው ፓርቲ ከምርጫው በፊት ‹የቤት ስራዎችን› በሚገባ ሰርቷል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ነጻውን ፕሬስ አፍኗል፣ የህዝብ ልሳኖችን ዘግቷል፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪዎችን፣ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችን አስሯል፤ እንዲሰደዱም አድርጓል፡፡ ስለሆነም በምርጫው መድረክ ኢህአዴግን ሊያጋልጡት የሚችሉ አካላት ላይ ሁሉ የማሳደድ ስራውን ሰርቷል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ ደካማ የህዝብ ተቀባይነቱን በመገምገም በህዝብ እንደማይመረጥ በመገንዘቡ አፈናውን ቀድሞ ጀምሮታል፡፡ በዚህም ልክ እንደ ምርጫ 97 አንጻራዊ ነጻነትን በመስጠት በህዝብ መድረክ ሽንፈትን ከመከናነብ ይልቅ ጭል ጭል የምትለውን ነጻነት ማፈንን ምርጫው አድርጎ ይታያል፣ ከ97 ምርጫ ‹የተማረው› ትምህርት መሆኑ ነው፡፡

ወደ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ስንመለስ ፕሮግራሙ ረቂቅ የመነሻ ሰሌዳ ነው ቢባልም እምብዛም ለውጥ እንደማይደረግበት መገመት ይቻላል፡፡ ለማነኛውም በፕሮግራሙ መሰረት ‹ከህዳር 15-30/2007 ዓ.ም በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተገኝተው የመወዳደሪያ ምልክታቸውን ይመርጣሉ› ሲል ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰሌዳ መሰረትም ፓርቲዎቹ እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ የመወዳደሪያ ምልክታቸውን አያውቁም/ይፋ አያደርጉም ማለት ነው፤ ምንም አይነት የምርጫ ክርክርም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በምርጫ 97 ወቅት በዚህ ወር (ህዳር) በፓርቲዎች መካከል የምርጫ ክርክር ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዘንድሮ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ታህሳስ 1/2007 ዓ.ም የምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች ተከፍተው በይፋ ስራ የሚጀምሩበት እንደሚሆን የጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል፡፡ ታህሳስ 12/2007 ዓ.ም ደግሞ መራጩ ህዝብ ‹በይፋ በሚደረግለት ጥሪ መሰረት በሚካሄደው የአንድ ቀን ስብሰባ የምርጫ ጣቢያ የህዝብ ታዛቢዎችን የሚመርጥበት› እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በቀናት ልዩነት ውስጥ ደግሞ፣ ከታህሳስ 16/2007 እስከ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ በየምርጫ ክልሉ ጽ/ቤት የሚካሄድበት ይሆናል ይላል፡፡ በመሆኑም ምርጫው አራት ወራት ያልሞላ ጊዜ እስኪቀረው ድረስ እጩዎቹ ምዝገባ አያከናውኑም ማለት ነው፡፡ ይህም የእጩዎቹን የምረጡኝ ቅስቀሳ ጊዜ ያሳጠረ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው፣ ከጥር 1 ቀን እስከ የካቲት 10 ቀን ድረስ የመራጮች ምዝገባ በየምርጫ ጣቢያው እንደሚካሄድ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል፡፡ በነገራችን ላይ እጩዎች የእጩነት ማረጋገጫ መታወቂያ ካርድ የሚሰጣቸው ከየካቲት 2-7/2007 ዓ.ም ባሉት ቀናት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህም ለምርጫው ሶስት ወራት ብቻ ሲቀረው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለሆነም እስከ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ምንም አይነት ይፋዊ የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ አይኖርም እንደማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በይፋ የሚጀመርበት መሆንን አስቀምጧል እና ነው፡፡

በዚህ መልኩ ለሶስት ወራት ያህል ክፍት ሆኖ የሚቆየው የምረጡኝ ቅስቀሳ እንቅስቃሴ ግንቦት 13 ቀን ከምሽቱ 12፡00 በይፋ የሚጠናቀቅ ይሆናል፣ በፕሮግራሙ መሰረት፡፡ ግንቦት 16 ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ደግሞ የሚጠበቀው ምርጫ የድምጽ መስጫ ዕለት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የምርጫ ውጤት ይፋ ስለማድረግ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ደግሞ ጊዜያዊ ውጤት ግንቦት 21 የሚገለጽ ሲሆን፣ አጠቃላይ ውጤቱ ደግሞ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ የምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል፡፡ በዚህ መሰረት ይፋዊ የምርጫ ውጤትን ለማወቅ አንድ ወር ሙሉ መጠበቅ ግድ ሊል ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች የታሰቡ ይመስላል፡፡ በተለይም ኢህአዴግ ለተቃውሞ አደባባይ እንዳይወጡ የሚፈራቸው ተማሪዎች ትምህርት ቤቶች ስለሚዘጉ ይበተናሉ፡፡ ሰኔ ላይ ገበሬው ስራ የሚበዛበት ወቅት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ክረምት በመሆኑ የምርጫ ታዛቢዎች በገጠር አካባቢ እንዳሻቸው ተዘዋውረው ስራቸውን ለማከናወን ዝናብና ጭቃ ይፈትናቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ማንን ሊጠቅመው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እሱም በምርጫ 97 ‹ትምህርት የቀሰመው› ኢህአዴግ ይሆናል፡፡

No comments: