Tuesday, October 7, 2014

በዋሽንግተን ዲሲ ጥቂት የወያኔ ኢምባሲ ሠራተኞች እና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በየፊናቸው ሰልፍ ወጡ

October 7,2014
(ዘ-ሐበሻ) ጥቂት የሕወሓት የዋሽንግተን ዲሲ ኢምባሲ ሠራተኞች እና አንዳንድ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ በሚሰጣቸው የስኮላርሺፕ ገንዘብ የደለቡ የስርዓቱ ደጋፊዎች በሰለሞን ተካልኝ መሪነት በስቴት ዲፓርትመንት ደጃፍ ዛሬ ሰልፍ ወጡ። በተመሳሳይም የአሜሪካ መንግስት በዋሽንግተን ዲሲ የሕወሓት ኢምባሲ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ጥይት የተኮሰውን የስርዓቱን ተላላኪ ከሃገሩ በማባረሩ ለዚህም ምስጋና ለማቅረብ ኢትዮጵያውያን በስቴት ዲፓርትመንት ተመሳሳይ ሰልፍ አድርገዋል::
ሃገር ወዳዱ ኢትዮጵያውያን ልሙጡን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በመያዝ እንዲሁም የሕወሃት ደጋፊዎች በመሃሉ ላይ ሰማያዊ ኮከብ ያለብትን እና ብዙዎች አይወክለኝም የሚሉትን ባንዲራ ይዘው ሰልፍ የወጡ ሲሆን በስቴት ዲፓርትመንት ደጃፍ በየፊናቸው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ አርፍደዋል። የሕወሓት ደጋፊዎች “ኢምባሲያችን ተደፈረ፣ ባንዲራችን ተዋረደ” በሚል ሰልፍ የጠሩ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ በበኩላቸው ሃገራችንን ከነክብሯና ባንዲራዋ ያዋረደው ገዢው የሕወሓት መንግስት ነው በማለት የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያውያኑ ላይ ጥይት የተኮሰውን ግለሰብ ወደሃገሩ በማባረሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ቀድሞ ከተቃዋሚዎች ጋር የነበረውና ተገልብጦ የሕወሓት ደጋፊ ሆኖ ቁጭ ያለው ሰለሞን ተካልኝ የሕወሓት ደጋፊዎችን ሰልፍ የመራ ሲሆን፤ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኑም ሰለሞን የሕወሓትን መንግስት ይቃወምበት የነበረውን “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” የሚለውን ዘፈኑን ከፍተው ለምስጋናው ሰልፍ ማድመቂያ አድርገውታል። ሰለሞን ጥቂት የኢምባሲ ሠራተኞችን ሰብስቦ ራሱን በራሱ በማይክራፎን “ሰለሞን እንዲህ የሚሆነው ለሃገሩ ለባንዲራው ነው፤” ያስባለ ሲሆን የሕወሃት ሰልፍ አላማውን ስቶ እንደተባለው የአሜሪካ መንግስትን መቃወሚያ ሳይሆን የሰለሞን ተካልኝ ሞራል መገንቢያና ማወደሻ ሆኖ አልፏል ሲሉ በአካባቢው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ መንግስትን የሚደግፍም ሆነ የሚቃወመው በአንድ ቦታ ቆሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ለራሳቸው ለወያኔ ደጋፊዎች ሊያሳፍራቸው ይገባል የሚሉት አንድ አስተያየት ሰጪ “እኛ እንዲህ ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ነው ትግላችን። ሕወሓትን የሚደግፍም የሚቃወምም በእኩል እንዲታይ። ሆኖም በሃገራችን መንግስትን መቃወም የማንችል መሆኑን የወያኔ ደጋፊዎች እያወቁት ሰሜን አሜሪካ ላይ ከእኛ እኩል ሰልፍ መውጣታቸውና የአሜሪካ መንግስት የመናገር መብትን መፍቀዱ የሚደግፉት መንግስት የሚሰራው ስህተት እንደሆነና እንዲማሩበት ትልቁን ሚና ይጫወታል: ሆኖም ግን ደጋፊዎቹ በአሜሪካ ሃገር ያገኙትን ነጻነት እኛ ሃገራችን ላይ እንድናገኝ ስለማይፈልጉ ከኛ እኲል ዲሞክራሲያዊ መንግስት እየደገፍን ነው ብለው መውጣታቸው ሊያሳፍራቸው ይገባል። ልክ እንደአሜሪካ መንግስት ሁሉ የሚደግፉት የሕወሓት መንግስት ተቃራኒ ሃሳብ ያላቸውን ወገኖች እኩል የመናገር መብት ሊሰጥ እንደሚገባ ከዚህ ሰልፍ ሊማሩ ይገባል” ብለውናል።


washington dc 3

No comments: