Thursday, October 9, 2014

የፋክት፣ አዲስ ጉዳይ እና ሎሚ መጽሔት ሥራ አስኪያጆች በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

October 8, 2014
(አዲስኒውስ) አዲስ አበባ – የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ የወንጀል ችሎት የፌዴራል ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ ተመልክቶ የፋክት መጽሄት ሥራ አስኪያጀ ወ/ሮ ፋጡማ ኑሪዬ በ3 ዓመት ከ11ወር ጽኑ እስራት እንዲሁም የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተሰፋዬ እና የሎሚ መጽሔት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ውሳኔ እንዳስተላለፈባቸው ከአዲስ አበባ የአዲስኒውስ ሪፖርተር ዘግቧል ፡፡
 የፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ህግ “ህገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ እና ሕዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ በማድርግ” በሚል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን የፋክት መጽሔት ካሳተማቸው ጽሁፎች መካከል “የፈራ ይመለስ” እና “የከተማ አብዮት” በሚል ርዕስ ስር በጻፋቸውና ባሰራጫቸው ጽሁፎች ሕዝብን ለአመጽ አነሳስቷል ሲል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው ነበር፡፡

 “የቁልቁለት መንገድ” በሚል ርዕስ ባሳተመው እና ለንባብ ባበቃው ጹሁፉ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት የተደረጉት አብዮቶች የብሔር እኩልነት ጥያቄን ያልመለሱ በመሆናቸው ሶስተኛ አብዮት ይቀጥላል የሚልና በመቶ ሺህ የሚቆጠር የታጠቀ ሀይል ቢኖር ሚልዮን ካድሬዎች ሀገሪቱን ቢያጥለቀልቁ አብዮቱ የማይቀር ጉዳይ ነው የሚሉ መልዕክት ያላቸውን ጽሑፎች አትሞ በማሰራጨት ህገ መንግስታዊውን ስርዓት በምርጫ መቀየር እየተቻለ በአብዮት ለመቀየር ተንቀሳቅሰዋል::” ይላል የዐቃቤ ህግ ክስ፡፡

“የፍትሕ እጦት አብዮት ይጠራል” በሚል ርዕስ ደግሞ መጽሄቱ “የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው በማረሚያ ቤት የሚገኙት ግለሰቦች ፍርደ ገምደል በሆኑና ፍትሕን በሚያጨናግፉ ነፃነት በሌላቸው ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንደተላለፈባቸው እና ፍርድ የተሰጠው በቤተ መንግስት እንጂ በፍርድ ቤቶቹ አይደለም የሚል ጽሁፍ ለሕዝብ በማቅረብ ህዝቡ በፍትህ ተቋማት ላይ እምነት እንዳይኖረው አድርገዋል” በሚል ዐቃቤ ህግ ክሱን አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ ዐቃቤ ህግ አዲስ ጉዳይ መጽሔት “እንደማይመለከትህ ስታስብ” በሚል ርዕስ ስር ባሳተመው ጽሁፍ “አሰታውስ እውነተኛ ሙስሊም ምንጊዜም ትግል ላይ ይገኛል፡፡ አቅሙ የፈቀደወን ሀይል ተጠቅሞም አሰፈላጊውን ነገር ያደረጋል፡፡” በሚል ህዝበ ሙስሊሙ ለአመጽ ቀስቀሷል ሲል ክስ ያቀረበበት ሲሆን በሌላ እትም ደግሞ “በኦሮሚያ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዱ ቦንቦች” በሚል ርዕስ ስር ዘረኝነትን የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ለህዝብ እንዲደረስ አደረገዋል፣ “ማረም የሚያስፈለገው ማረሚያ ቤት” በሚል ባዘጋጀው ጽሁፍ ህዝቡ በተቋሙ ላይ እምነት እንዳይኖረው እና ሀገሪቱ ውስጥ ፍትሕ እንደሌለ የሚያሰመስል ጽሁፍ በማሳተም ለህዝብ አሰራጭተዋል ይላል የዐቃቤ ህግ ክስ፡፡
በሎሚ መጽሄት ላይም ዐቃቤ ሀግ ተመሳሳይ ክስ የመሰረተ ሲሆን መጽሄቱ “የአሸባሪነት ፈርጦች” እና “የኢህዲግ የሽብርተኝነት መመዘኛ መስፈርቶች” በሚሉና በሌሎች ርዕስ ስር ያወጣቸውን ጽሁፎች በመጥቀስ ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶ ነበር፡፡

ዐቃቤ ህግ በሶስቱም መጽሄቶች ሥራ አሰኪያጆች እና አሳታሚዎች ላይ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን ለተከሳሾቹም በአዲስ ዘመን ጥሪ ተደርጎላቸው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው እና ፖሊስም በአድራሻቸው አፈላልጎ እንዳጣቸው ለፍርድ ቤቱ በማስታወቁ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ በሌሉበት ክሱን መርምሮ የጥፋተኝነት ውሳኔ ካሰተላለፈባቸው በኃላ በትላንትናው ዕለት የቅጣት ውሳኔውን አሳልፏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የፋክት መጽሄት ሥራ አሰኪያጅ ወ/ሮ ፋጡማ ኑሪዬ በ3 ዓመት ከ11 ወር ጽኑ እስራት፣ የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ሥራ አሰኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ እና የሎሚ መጽሄት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔውን አሰተላለፏል፡፡ የፋክት መጽሄት አሳታሚ  ዩፋ ኢንተርቴይመንት እና ፕሮስ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማ ፣ የአዲስ ጉዳይ መጽሄት አሳታሚ ዲዲሞስ ኢንትርቴይመንት እና የሎሚ መጽሄት አሳታሚ ሮዛ አሳታሚዎች ድርጅት በፍትህ ሚኒስቴር ስር አግባብ ባለው መንግስት አካል ስር እንዲቆዩ ሲል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል ፡፡
ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ተከሳሾቹን አፈላልጎ በመያዝ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብና ማረሚያ ቤቱም ቅጣቱን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ሰጥቷል ፡፡

No comments: