Monday, October 6, 2014

ነገረ ህወሓት: ህወሓትና ‹‹ወያኔ›› ምንና ምን ናቸው?

Oktober 6,2014
ጌታቸው ሺፈራው (ጋዜጠኛ)
‹‹ህ.ወ.ሓ.ት›› የተሰኘው የፖለቲካ ቡድን ሙሉ ስሙ ሲዘረዘር ‹‹ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ›› መሆኑ ለማንም ግራ የሚያጋባ አይደለም፡፡ በተለይ በርሃ በነበረበት ጊዜ ከረዥም ስሙ ይልቅ ‹‹ወያኔ›› መጠሪያው ሆኖ አገልግሏል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ይህን ስም ህወሓት ከዚህ በፊት የነበረ ታሪክ ቀጣይና የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ እንቅስቃሴ አስቀጣይ (ወራሽ) ለመምሰል ተጠቀመበት፡፡ ህወሓት ‹‹ወያኔ›› የተሰኘ ስሙን በመጀመሪያዎቹ ለጥቂት ጊዜያት በተለይ ውስጥ ለውስጥም ሆነ በቀጥታ ካስተዋወቀ በኋላ ይህን ስሙን ሌሎችም እንዲለምዱት አደረገ፡፡ ይህን ያደረገበት ምክንያቱ ደግሞ ስሙ በታሪካዊነቱም ሆነ ትርጉሙ የህወሓትን ሰብዕና የሚገነባ በመሆኑ ነው፡፡
tplf-rotten-apple-245x300
‹‹ወያኔ›› ማለት በትግርኛ አብዮት ወይንም አመጽ እንደ ማለት ነው፡፡ ህወሓት ይህን መልካም መጠሪያ የወሰደው ደግሞ በ1935 ዓ/ም አካባቢ ተነስቶ ከነበረው ‹‹ወያኔ›› ከተባለው የአርሶ አደሮች አመጽ የቀጠለ ታሪካዊና አልጋ ወራሽ ለመምሰል ነው፡፡ ሆኖም በ1930ዎቹ መጨረሻ ትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ተመሳሳይ የአርሶ አደሮች አመጽ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የ‹‹ወያኔ›› አመጽ የፊውዳሉ ስርዓት ከነበረው ብልሹነት የመነጨና በኋላም ለተማሪዎች አብዮትም ጭምር እንደ እርሾ እንዳገለገለ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ የወቅቱ አማጺያን ህዝብ ይቀሰቅሱበት ከነበረው መፈክር መካከል ቀዳሚው ‹‹ሰንደቃችን የኢትዮጵያ ነው›› የሚል ነበረበት፡፡ በአጠቃላይ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ አንድነትን መሰረት ያደረገ እንጂ ህወሓት ‹‹ወያኔ››ን በቅጽል ስምነት አንጠልጥሎ ይከተለው ከነበረው ‹‹ተገንጣይነት›› ፖሊሲ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነው፡፡ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ‹‹ወያኔ›› ወይንም አመጽ ከስርዓት እንጂ ከአገር ‹‹ነጻ›› መውጣት ወይንም መገንጠልን ጋር የተገናኘ አልነበረም፡፡
ህወሓት ከአርሶ አደሮቹ አመጽ ብቻ ሳይሆን በነ መንግስቱ ንዋይ ከተሞከረው የመንግስት ለውጥ ሙከራ በተጨማሪ ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚል መፈክርን አንግቦ ለተነሳው የተማሪዎች አብዮት እርሾ እንደነበር ከሚነገርለት የአርሶ አደሮች እንቅስቃሴ እጅጉን ተቃራኒ ነው፡፡ ህወሓት ‹‹እየሱስ አምላካችን ነው›› የሚል መፈክር ካነገቡት አርሶ አደሮች ይልቅ የወቅቱ የማርክሲዝም አንድ መርህ ከነበረው ስለ መሬት ለአራሹ፣ ስለ ዓለም ላብ አደሮች ትብብር ከሚያወራው የተማሪው አብዮት ቅርብ ነበር፡፡ ሆኖም ከአርሶ አደሮቹ ይልቅ ለተማሪው እንቅስቃሴ አንድ አካል ነበር የሚባለው ህወሓት ከመሬት ለአራሹ ይልቅ ‹‹ስለ ትግራይ ህዝብ›› መሬት እንደሚጨነቅ አስመሰለ፡፡ ስለ ዓለም ላብ አደሮች ትብብር ሲያወራ ከነበረው የ1960ው አብዮት ወርዶ ለአንድ ብሄር ተወላጆች ትብብር፣ መገንጠል…የመሳሰሉት ተገንጣይ ጉዳዮች ቅድሚያ ሲሰጥ ነው ከተማሪዎች አብዮትም ያፈነገጠው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ወያኔ››ነት (አብዮት) ይህኔ ነው ያከተመው፡፡ ከዚህ በኋላ ህወሓት ‹‹ወያኔ›› የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አጥቷል፡፡ ምክንያቱም ከአርሶ አደሮችም ሆነ ከተማሪው አብዮት አፈንግጧልና ነው፡፡
ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እንኳን ያፈነገጠው ህወሓት የቀዳማዊ ወያኔ ወራሽ ነኝ በሚል ዳግማዊ ‹‹ወያኔን›› በመጠሪያነት መጀመሪያ አካባቢ ተጠቀመበት፡፡ ህወሓት በደርግ ላይ ድል እያስመዘገበ ሲመጣ ‹‹ወያኔ›› በተለይ በወቅቱ ተቃዋሚዎች ዋነኛ መጠሪያው ሆነች፡፡ ስሙ ከመለመዱ የተነሳ እነ መንግስቱ ኃ/ማርያም ሳይቀሩ ተግባሩን ሲያወግዙ ከህወሓትና ከረዥም ዝርዝሩ ስሙ ይልቅ ‹‹በወያኔ››ነት መጥራቱን ተያያዙት፡፡ ይህ ለህወሓት መልካም ስም ነበር፡፡ እሱ ቢጀምረውም ትርጉምና ታሪካዊ ተያያዥነቱን ሳያጤኑ ያጋነኑለት የሚቃወሙትና የሚጠሉት አካላት ናቸው፡፡
የአርሶ አደሮች አመጽ በተቀሰቀሰበት ወቅት በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ አመጾች የነበሩ ቢሆንም ከህወሓት ጋር የተማሪው አብዮት አካል የነበሩት ወደ ትጥቅ ትግል ሲገቡ ‹‹ዳግማዊ፣ ሳልሳዊ…›› ብለው ስማቸውን አልወሰዱም፡፡ ወያኔ የአርሶ አደሮቹ አመጽ ኢትዮጵያዊ አላማ የነበረው ቢሆንም ልክ እንደ ህወሓት አሻፈረኝ ብለው ዱር የወጡትና ከእሱም የተሻለ አገራዊ አላማ እንደነበራቸው የሚነገርላቸውና ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ያፈነገጡት እንኳን ‹‹ወያኔ›› ነን አላሉም፡፡ በእርግጥ ህወሓት የአርሶ አደሮቹን ቀደምት አመጽ ከራሱ ጋር በማዛመድ ‹‹ዳግማዊ››ነቱን ያወጀው ከመርህና አላማ አንጻር ሳይሆን ከአርሶ አደሮቹ ጋር ‹‹በብሄር›› ግንኙነት እንዳለው ለመግለጽ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም በአብዛኛው መርህና አላማ ከተማሪዎች አብዮትም ሆነ ከአርሶ አደሮቹ አብዮት የራቀና ያፈነገጠ ያደርገዋል፡፡ አሁንም አብዛኛዎቹ የህወሓት/ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ‹‹ወያኔ›› የምትለዋን ስም አሉታዊ አድርገው በስፋት ይጠቀሙባታል፡፡ እኔ በበኩሌ ይህ ስም ለህወሓት ኢህአዴግ አይገባውም ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ህወሓት ራሱን ኢትዮጵያዊ አቋም ከነበራቸው አርሶ አደሮች የቀጠለ መሆኑን ለመግለጽ ‹‹ዳግማዊ ወያኔ›› ብሎ የሚጠራበት አላማም ሆነ ታሪካዊ ትስስር ስለሌለው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በእንግሊዘኛው ‹‹Tigray People Liberation Front›› ከተባለው ስሙ ውስጥ ‹‹ወያኔ›› ለሚባለው እኩያ ትርጉም አይገኝለትም፡፡ በቀጥታ እንተርጉመው ከተባለ ‹‹የትግራይ ህዝቦች ነጻ አውጭ ግንባር›› ነው የሚሆነው፡፡ Tigray ትግራይ ነው፡፡ People ህዝብ የሚለውን ይወክላል፡፡ Liberation አርነት (ኃርነት) ነው፡፡ Front ደግሞ ግንባር እንጂ አብዮት ሊሆን አይችልም፡፡ ስሙን እንዲሁ ለክብር ሲባል አገናኘው እንጂ ተያያዥ ትርጉም የለውም፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹Front››ን ‹‹ወያኔ እንዳሉት እንረዳለን፡፡ ወያኔ የተሰኘው የአርሶ አደሮች እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ እንቅስቃሴ እንጂ ‹‹ግንባር›› ወይንም ‹‹Front›› የሚባል አልነበረም፡፡ ከህወሓት ውጭ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (‹‹Tigray Liberation Front››) የሚባል ታጣቂ ቡድንም ነበር፡፡ ግን እንግሊዘኛ ስሙ ላይ ‹‹Front› የሚል ስላለው ብቻ ‹‹ወያኔ›› በሚል የሌሎችን ታሪክ ለመጋራት አልተንጠራራም፡፡
ምንም እንኳ በማርክሲሳዊ እይታ አብዮታዊ ባይሆንም ከህወሓት ይልቅ ኢዲዩ ራሱን ወያኔ ብሎ ቢጠራ ከህወሓት የተሻለ መሰረት ነበረው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የኢዲዩ አባላት ከአማጺያኖቹ አርሶ አደሮች ጋር የሚያመሳስል የርዕዮተ ዓለማዊም ሆነ ሌሎች ትስስሮች ስለነበራቸው ነው፡፡ የተገንጣይ አላማም ሆነ በአገራቸው ላይ ጥላቻ አልነበራቸውም፡፡ ይህን ስንመለከት ህወሓት በበርካታ ምክንያቶች ‹‹ወያኔ›› የሚለው ስያሜ እንደማይገባው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ‹‹ልማታዊ መንግስት››፣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ››…..የሚባሉትን ስሞች ዝም ብሎ በሌሉበት የመለጠፍ ታሪኩ የሚጀምረው ‹‹ወያኔ››ን በመጠሪያነት ያለ አግባብ ከቀላቀለበት ጊዜ የጀመረ ይመስለኛል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ያነሳው ሁሉ በስፋት እንደሚጠላ ያውቀዋል፡፡ ይህን የማይገባውን የክብር ስምም ገና በርሃ እያለ አስተዋውቆ ዘወር በማለቱ በአብዛኛው አሉታዊ መስሏቸው ሌሎች ናቸው መጠሪያው ያደረጉት፡፡ በተለይ በተቃዋሚዎቹ ዘንድ የማይወደው መስሎ ሳይታያቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ህወሓት/ኢህአዴግን ‹‹ወያኔ›› ብለው ሲጠሩት ግን ከሚገባው በላይ እንዳጋነኑለት፣ የማይገባውን ታሪክ እንዳወረሱት፣ አገር ወዳድና ቀናኢ አላማ እንዳለው አድርገው እየቆጠሩት መሆናቸውን መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡ በተለይ ህወሓትን ጠበብ ብለው እየከሰሱ ቢሆን ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ጋር የማይነጣጠል፣ ለትግራይ ህዝብ የሚሰራ አድርገው የሚቆጥሩት ‹‹ወያኔ›› ብለው ሲጠሩ ህወሓትን ከሚከሱበት ጠባብነት አልወጡም ማለት ነው፡፡
‹‹ወያኔነት›› በገዥዎች ላይ እምብይ ባይነት ነው፡፡ የድሮዎቹ አርሶ አደሮች ይህን ስም የራሳቸው ያደረጉት በበዝባዡ ፊውዳል ስርዓት ላይ አምጸው ነው፡፡ አሁን ‹‹ወያኔ›› የሚባለው ህወሓት ዘመናዊ ፊውዳል ሆኗል፡፡ ራሳቸውን ‹‹ወያኔ›› ባይሉም የህወሓትን ዘመናዊ ብዝበዛ የሚቃወሙ እምብይ ባዮች አሉ፡፡ እነዚህ እምብይተኞች ህወሓት አሸባሪዎች ይላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወያኔ የሚባል አካል መባል ካለበት ግን ያለ ምንም ጥርጥር ከበዝባዡና ከዘመናዊ ፊውዳሉ ከህወሓት ይልቅ ይህን አፋኝ ስርዓት በመቃወም ላይ ለሚገኙት ደፋሮች የሚመጥን ስም ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን ተቃዋሚዎች ራሳቸው ለራሳቸው የሚገባውን ስም ለበዝባዥ አሳልፈው የሚሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ለህወሓት መልካም ነገር ነው፡፡
እኔ በበኩሌ ‹‹ወያኔ›› ብዬ ጠርቼው አላውቅም፡፡ አይገባውማ! ያለ ታሪኩ!? ያለ አላማው!?

No comments: