Tuesday, October 7, 2014

ፖሊሶች ዩኒፎርም ለብሰው ቤተክርስቲያን ሲሳለሙ ከተገኙ ይገመገማሉ፤ ማዕተባቸው ከዩኒፎርማቸው በላይ እንዲታይ አይፈቀድም

Oktober 7,2014
(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ ፖሊሶች የፖሊስ ዩኒፎርም ለብሰው ቤተክርስቲያን ሲሳለሙ ከተገኙ እንደሚገመገሙና እንደሚቀጡ፤ ማዕተባቸውም ከዩኒፎርማቸው በላይ እንዳይታይ እንደሚገደዱ ታወቀ። በሌላ በኩል ዛሬ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዩኒቨርሲቲዎች ሃይማኖታዊ ስነስርአትና አለባበስን በሚመለከት ያወጡትን የስነምግባር ደንብ በመቃወም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በሽብር ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ 13 ግለሰቦች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው ሲሉ ዘገቡ።

police1በአዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ያሉ የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስተር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይሄን የኦርቶዶክሳውያን ማዕተብ መበጠሳችን አይቀርም” በሚል መናገራቸውን ተከትሎ ዜናው እጅጉን መናገገሪያ ቢሆንም ፖሊሶች የደንብ ልብስ ለብሰው ቤተክርስቲያን መሳለም ከተከለከሉ ቆይተዋል። እንደምንጮቹ ገለጻ የደንብ ልብስ ለብሰው ቤተክርስቲያን በሚሳለሙ ፖሊሶች ላይ ከግምገማ አንስቶ እስከ ሥራ መባረር የሚደርስ ቅጣት የሚጣልባቸው ሲሆን የደንብ ልብስ ሲለብሱም የሚያደርጉት መስቀል ከዩኒፎርማቸው በላይ እንዳይታይ እንደሚከለከሉ እነዚሁ ምንጮች ጠቅሰው በዚህ የተነሳ ሥራቸውን ያጡ በርካታ መሆናቸውን አስታውቀውናል።
ማህተባችን ከሚወልቅ የፖሊስ ዩኒፎርማችን ይውለቅ በሚል በርካታ ፖሊሶች ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ የሚገልጹት እነዚሁ የዘ-ሐበሻ ምንጮች የመንግስት አካሄድ ምን እንደሆነ የራሱን አባላት ግራ እንዳጋባ ይገልጻሉ።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሃይማኖታዊ ስነስርአትና አለባበስን በሚመለከት የስነምግባር ደንብ ማውጣታቸውን ተከትሎ ማንኛውም የቢሮ ሰራተኛ በቢሮው ውስጥ የቁርአን ጥቅስ፣ ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንዳይለጥፍ የሚከለከል ሲሆን በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። በዚህም መሠረት ዛሬ እንኳን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት እስማኤል ኑር ሁሴን፣ ፈትያ መሃመድ፣ ኑርዬ ቃሲም፣ ያሲን ፈያሞ፣ መሃመድ አሚን፣ መሃመድ ሰይድ፣ የሱፍ ከድር፣ ጣሂር መሃመድ፣ መሃመድ ሰይድ፣ ሰይድ ኢብራሂም፣ አብደላ መሃመድ፣ አብዲ መሃመድ እና ኢብራሂም የሱፍ ኢብራሂም የተባሉ ኢትዮጵያውያን “የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ሃይማኖታዊ ስነስርአትና አለባበስን በሚመለከት ያወጡትን የስነምግባር ደንብ በመቃወም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በሽብር ድርጊት ፈጽመዋል” በሚል ውሃ በማይዝ ክስ ጥፋተኛ መባላቸውን ዘግበዋል።
እንደመንግስታዊ ሚዲያዎች ዘገባ “ተከሳሾቹ በ2005 ዓ.ም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሃይማኖታዊ አለባበስን በሚመለከት የወጣውን ደንብ ተከትሎ በጥቂት ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች የተጀመረው አመጽና አድማ በተናጠል ከሚሆን ሃገር አቀፍ መሆን አለበት በማለት በየዩኒቨርስቲዎች በስልክ፣ በማህበራዊ ድረ ገጾችና በአካል በመንቀሳቀስ ቀስቅሰዋል።” የሚል ክስ ቢቀርብባቸውም ታዛቢዎች ግን ተከሳሾቹ ሃይማኖታቸው የሚያዛቸውን ነው የተከተሉት በሚል የተላለፈባቸውን ውሳኔ ፖለቲካዊ ሲል ይቃወሙታል።
የኢትዮጵያ መንግስት “ሃይማኖታዊ ስነስርአትና አለባበስን በሚመለከት ያወጣው የስነምግባር ደንብ” ሙስሊሙንም ሆነ ክርስቲያኑን እጅግ እያስቆጣ ሲሆን በተለይ ክርስቲያኑን ወገን መስቀል እናስወልቃለን ብለው ዶ/ር ሽፈራው ከተናገሩ በኋላ በሶሻል ሚዲያዎች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲደርስባቸው ወዲያው “አላልኩም” ብለው ለማስተባበልና ነገሩን ለማብረድ ቢጥሩም ጉዳዩ የተሳካ አይመስልም። ልክ የክርስቲያኑን መስቀል እናስወልቃለን አላልንም በሚል ለማስተባበል የተጠቀሙትን ቃል ለሙስሊሙም ሂጃብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል በሚል ዶ/ር ሽፈራው በሶሻል ሚዲያዎች ከፍተኛ ውተወታ እየደረሰባቸው ነው። በተለይም ዶ/ር ሽፈራው መንግስት በሃይማኖት አለባበስና ስነ ስር ዓት ውስጥ እንደማይገባ በሚዲያዎቻቸው በዋሹ በሰዓታት ውስጥ የመንግስት ሚዲያዎች 13 ሙስሊሞች በተመሳሳይ ክስ ጥፋተኛ ተባሉ ተብሎ መፈረዱ አነጋጋሪ ሆኗል።

No comments: