Friday, October 10, 2014

በኢትዮ ምህዳር ላይ የተከፈተው ክስ ላይ አለመግባባት ተፈጠረ

October 10,2014
‹‹ጋዜጣውንም ሆነ ጋዜጠኛውን አልከሰስኩም›› አቶ ማሙሸት አማረ

‹‹አቶ ማሙሸት የከሰሰበት ሰነድ በዝርዝር ተነቦልኛል›› ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ


በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቅጽ ሁለት ቁጥር 80 ላይ የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሊቀመንበሩ ‹‹ፖርቲውን እያፈረሱ ያሉት ምርጫ ቦርድ፣ ኢህአዴግና አቶ ማሙሸት አማረ በጋራ ሆነው ነው፡፡›› በሚል በሰነዘሩት ሀሳብ አቶ ማሙሸት አማረ ጋዜጣውን ከሰዋል በሚል የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ማክሰኞ መስከረም 26/2007 ዓ.ም ማዕከላዊ ቀርቦ ቃል መስጠቱ ይታወሳል፡፡ 

ይሁንና አቶ ማሙሸት አማረ ጋዜጣውን አልከሰስኩም በማለት ዜናውን ያወጣውን የሰንደቅ ጋዜጣ ‹‹እንደ ጋዜጠኛ ግራና ቀኝ መረጃ ማየት ባለመቻላቸውና እኔንም ስላላናገሩኝ እንጅ እኔ አልከሰስኩም፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አቶ ማሙሸት ጨምረውም ‹‹አራዳ ፖሊስ ጣቢያ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ማዕከላዊ ምርመራ ቃለ መጠይቁን የሰጡትን አቶ አበባው መሃሪን ለመክሰስ በበቀረብንበት ወቅት ጋዜጣውንስ ትከሳላችሁ? የሚል ጥያቄ ቀርቦልን የነበረ ቢሆንም ‹አንከስም፣ ይህ ጋዜጣውንም ሆነ ጋዜጠኛውን (ዋና አዘጋጁን) ሊያስከስሰው የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ስማችን ያጠፋው ቃለ መጠይቁን የሰጠው ሰው እንጅ ጋዜጣው ወይንም ጋዜጠኛው አይደለም› ብለን ጋዜጣውን ስለመክሰስ ቃል አልሰጠንም፣ መስካሪዎቹም ቃል አልሰጡም፡፡ ስለ አቶ አበባው እንጅ ስለ ኢትዮ ምህዳር ያወራነው ነገር የለም›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮ ምህዳር ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ቃል ለመስጠት ወደ ማዕከላዊ ባቀናበት ወቅት አቶ ማሙሸት የከሰሱበት ሰነድ በዝርዝር እንደተነበበለት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ጋዜጠኛው አክሎም ‹‹ፖሊስ ሊከሰኝ ሰበብ ከፈለገ በአቶ ማሙሸት በኩል ሊመጣ አይችልም፡፡ አቶ ማሙሸት ነው ዱላ ያቀበላቸው፡፡›› ሲል ገልጾአል፡፡

ጋዜጠኛው ‹‹አቶ ማሙሸት ልክ ጋዜጣው እንደወጣ ስሜን አስጠፍተሃል በማለቱ እኔ የሰራሁት ቃለ መጠይቅ መሆኑንና ይህም ስም ማጥፋት እንዳልሆነ ከማስረዳትም በተጨማሪ፣ እሱንም ጓደኞቹንም ሀሳባቸውን ቢሰጡ እንደማስተናግድ ነግሬው ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ እኔ ያለሁበት ቦታ መጥተህ ቃለ መጠይቅ ስራ በማለቱ የጋዜጠኝነት ሙያን የሚጋፋ በመሆኑ በጽሁፍ አሊያም መጥቶ ቃለመጠይቅ እንዲሰጥ ስጠይቀው ዝቶብኛል፡፡›› ሲል አቶ ማሙሸት ከመጀመሪያው ጋዜጣው ስማቸውን እንዳጠፋ እንደሚያምኑና ሊከሱ የሚችሉበትን መነሻ አብራርቷል፡፡

አቶ ማሙሸት በበኩላቸው ‹‹ሰንደቅ ሳያናግረኝ እኔ እንደከሰስኩት አድርጎ ዜና ሰርቷል፡፡ የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኛም አልደወለልኝም፡፡ ይህ ራሱ ሌላ ስም ማጥፋት ነው፡፡ መጀመሪያ እኛም መጠየቅ ነበረበት፡፡ ጋዜጠኛው መጀመሪያም ለእሱም የሰጠነው ሰነድ እጁ እያለ የአንድ ሰው ሀሳብ አቅርቧል፡፡ የእኛን ሀሳብ ለማቅረብ አልሞከረም፡፡›› ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ ጌታቸው በበኩሉ ‹‹አቶ አበባውን ባናገርኩበት ወቅት አቶ ማሙሸት ምንም አይነት ሰነድም መረጃም አልሰጠኝም፡፡ ሀሳቡን በነጻ ሀሳብም ሆነ በሌላ መልኩ መግለጽ እንደሚችል ግን ገልጨለት ነበር፡፡ አሁን አልከሰስኩም የሚለው የሚዲያ ጫና ሲበዛበት ነው፡፡›› ሲል ‹‹አልከሰስኩም›› የሚለው የአቶ ማሙሸት ማስተባበያ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

No comments: