Wednesday, March 12, 2014

የአውሮፓ ሕብረት በአዲስ አበባ መንግስትን እና ተቃዋሚዎችን እያነጋገረ ነው

march12/2014

የፖለቲካ ምህዳር መስፋት፣ የ2007 ምርጫ፣ የታሳሪዎች ጉዳይ በአጀንዳነት ተነስቷል
ከዘሪሁን ሙሉጌታ

በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካና የኢትዮጵያ ቋሚ አምባሳደር የኢትዮጵያ መንግስትንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያነጋገረ ነው። የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር አማካኝነት መካሄድ የጀመረው ውይይት በሀገሪቱ የፖለቲካ መህዳር መስፋት፣ በ2007ቱ ምርጫ፣ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲሁም በሀገሪቱ ስላለው የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብቶች ዙርያ መሆኑ ታውቋል።

ባለፈው ዓመት የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች ኅብረቱን በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የበለጠ የሚከበሩበትን ገንቢ አማራጭ እያፈላለጉ ነው። በዚህም የአምባሳደሯ እንቅስቃሴ መሠረት የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በመገኘት ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በመሆን በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት አካሂደዋል። አምባሳደሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይት ካካሄዱ ከአምስት ቀናት በኋላ በሀገሪቱ ካሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ ከሆነው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር በጽ/ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል::

በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካና የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በተወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ዴሞክራሲያዊ ሕጋዊ መሠረት የተከተለ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ላይ ቢሆንም፤ የበለጠ መሻሻል በሚገባቸው ቀሪ ስራዎች መወያየታቸው መዘገቡ ይታወሳል። በተጨማሪም በመጪው ዓመት የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው አይዘነጋም።

በተመሳሳይ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም በአውሮፓ ኅብረት ጽ/ቤት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከኅብረቱ አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድና የህንድ ውቅያኖስ ክፍል ኃላፊ ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም በአጠቃላይ ፓርቲው እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴና “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚለው የፓርቲው ክፍል ሁለት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ መጠየቃቸውን፣ የገዢው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ በሀገሪቱ መሬት የጥያቄ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጥያቄ በመሆኑ በጥቅሉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጤናማ እንዳይሆንና መንግስታዊ የሙስና ሥርዓት እንዲጎለብት መደረጉን አርሦ አደሩም ከድህነት እንዳይወጣ በማድረግ ዋነኛ የዴሞክራሲ ማፈኛ መሆኑን ማስረዳታቸውን በውይይቱ የተሳተፉት አቶ ሀብታሙ አያሌው ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በእስር ስለሚገኙ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች የፓርቲው አመራሮችን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ አቶ አስራት ጣሴ ስለታሰሩበት ምክንያት፣ ምርጫ 2007 ላይ ፓርቲው ስላለው አቋም፣ በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለና በስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት፣ የሚዲያ ሞኖፖሊና የግል ፕሬሱ ወዳከም ጋር የተያያዙ ችግሮች ዙሪያ ውይይት ማካሄዱን ከአቶ ሀብታሙ ገለፃ መረዳት ተችሏል።
በመጪው ሚያዚያ ወር ብራስልስ ላይ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት በሚያካሂዱት የግራ ስብሰባ ላይ የአንድነት ፓርቲ ተወካይ ተገኝቶ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡንም አቶ ሀብታሙ አያይዘው ገልፀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች መካከል ገንቢ ውይይት ተደርጎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ከፍ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ይህ ካልሆነ ግን በምስራቅ አፍሪካ አደገኛ ወደሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊፈጠር እንደሚችል ገልፀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሰፊ የልማት፣ የቴክኒክ ድጋፎች እንደሚያደርግ ይታወቃል። በምትኩ ሀገራቱ የዜጎቻቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያከብሩ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋል። ኢትዮጵያም የሎሜ ኮንቬንሽንን እ.ኤ.አ በ1975 ዓ.ም ከፈረመች ጊዜ አንስቶ ከኅብረቱ ጋር የልማት ትብብር መስርታለች፤ ኅብረቱም በአውሮፓ የልማት ፈንድ (European Development Fund) (EDF) እገዛ ያደርጋል። በተለይ በትራንስፖርት፣ በገጠር ልማት፣ ባልተማከለ የማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፍ፣ በንግድ፣ በጾታ በሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ሀገሪቱን ይደግፋል። የድጋፍ መጠኑም በቅርቡም ወደ 600 ሚሊዬን ፓውንድ ይደርሳል።

አዲሲቷ የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር በመንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተካረረውን ግንኙነት በማለዘብና ወደ ገንቢ ውይይት እንዲመጡ ማበረታታታቸው በበጎ ዓይን እየታየላቸው ነው። አምባሳደር ቻንታል ባለፈው ዓመት የሹመት ደብዳቤአቸውን ከማስገባታቸው በፊት በአውሮፓዊቷ ኪርጊስታን ሀገር የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። የቤልጂየም ተወላጅ የሆኑት አምባሳደር ቻንታል በኢትዮጵያ የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር የነበሩትና ባለፈው ግንቦት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የሀገራቸውን ልጅ አምባሳደር ቫቪየር ማርሻልን ተክተው ወደ ኢትዮጰያ መምጣታቸው ይታወሳል።

(ዜናው የተገኘው ዛሬ በአዲስ አበባ ከታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ ነው)

No comments: