Wednesday, March 12, 2014

“ኢህአዴጋዊ ምርጫ” በሰሜን ኮሪ

march12/2014

ኪም ጆንግ ኧን 100% ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል!
kim un


ድምጽ የመስጫው ጊዜ ተጠናቅቆ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መቁጠር በጀመሩ ጊዜ ኪም ጆንግ ኧን የማሸነፋቸው ጉዳይ አሳስቧቸው በስጋት ውስጥ ነበሩ፡፡ ቆጠራው ተጠናቀቀ፤ ውጤቱ ይፋ ሆነ፤ አሸናፊው ታወጀ፤ ኪም ጆንግ ኧን ሥልጣን ከያዙ የመጀመሪያውን ምርጫ በ100% አሸነፉ፤ ከጭንቀታቸው አረፉ፤ ሕዝቡም በደስታ ፈነጠዘ፣ የክት ልብሱን ለበሰ፤ በአደባባይ ወጥቶም ዳንኪራ ረገጠ፡፡
korea2እሁድ በተደረገው ምርጫ የተሰጠውን እያንዳንዱን ድምጽ ኪም ጆንግ ያለተቀናቃኝ የራሳቸው አድርገዋል፡፡ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው ምርጫ የተሳተፈው ሕዝብ የምክርቤት አባላትንም መርጦዋል፡፡ በደንቡ መሠረት ምርጫው የሚካሄደው ለምክርቤት ምርጫ ሲሆን የተመራጮች ዝርዝር ውጤት ከመታወቁ በፊት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት ኪም ጆንግ ኧን ያለተቀናቃኝ በተወዳደሩበት ወረዳ አንድም ተቃዋሚ ድምጽ ሳይሰጥባቸው የሁሉንም መራጭ ይሁንታ በማግኘት መመረጣቸውን ዘግቧል፡፡ ያለፈው ምክርቤት 687 መቀመጫ የነበሩት ሲሆን የአሁኑ ምን ያህል እንደሚኖረው እስካሁን አልታወቀም፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጠቃቸውና የኒዎሊበራል አቋም የሚያራምዱ ጽንፈኛ ኃይሎች ታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተከፈለበትን ምርጫ በማጣጣል ልማታዊውን መሪ መመረጥ ለመቃወም ቢሞክሩም “ምርጫው የኮሪያ ሕዝብ በታላቁ መሪ ኪም ጆንግ ኧን ላይ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበትና በእርሳቸው ራዕይ ለመመራት መወሰኑን በአንድ ድምጽ የገለጸበት ነው” በማለት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት አጣጥሎታል፡፡
ምርጫ በተደረገበት እያንዳንዱ ወረዳ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የቀረበ ሲሆን መራጮች ድምጽ ሲሰጡ የሚመርጡት በተወዳዳሪው ስም አቅጣጫ “እመርጣለሁ” ወይም “አልመርጥም” የሚል ብቻ እንደነበር ተገልጾዋል፡፡ በህመምና በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው መምረጥ ለማይችሉ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ሳጥን ተዘጋጅቶ ያሉበት ቦታ የምርጫ ኮሮጆ በመውሰድ ድምጻቸውን እንዲሰጡ መንግሥት ያመቻቸላቸው መሆኑን የሰሜን ኮሪያ መንግሥታዊ ዜና አገልግሎት ጨምሮ ዘግቧል፡፡korea4
የሰሜን ኮሪያው ተሞክሮ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማድረግ ልምድ ላላቸው አገራት ተምሳሌት ከመሆኑ አኳያ በርካታ ልምምድ ሊወሰዱበት የሚችሉ እንደሆነ ምርጫውን የታዘቡ ገለልተኛ ያልሆኑ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በአንድ የምርጫ ቀበሌ አንድ ተመራጭ ብቻ “በማወዳደር” አላስፈላጊ የሆኑና የማያሸንፉ ተወዳዳሪዎችን በማስወገድና ወጪን በመቀነስ ልማታዊ ምርጫን ማበረታታት ከአሁኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ እነዚሁ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡
በምርጫው ወቅት አብዮታዊና አውራ ፓርቲያዊ ቀስቃሽ ዜማዎች የተሰሙ ሲሆን ሰሜን ኮሪያን ለ46ዓመት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጠ/ሚ/ርነት እና በፕሬዚዳንትነት አገልግለው የተሰውትን የቀድሞውን ባለራዕይ መሪ፣ የኮሪያ ላብአደር ፓርቲ ሊቀመንበር፣ የጦር ኃሎች አዛዥ፣ ማርሻል እና የሪፑብሊኩ ዘላለማዊ መሪ ኪም ኢል ሱንግን የሚያወሱ “በሌጋሲ” የተሞሉ ዜማዎችም ቀርበዋል፡፡

No comments: