Monday, March 31, 2014

የኑሮ ውድነት ሽክም የጫነብን ማን ይሆን? – ከግርማ ሠይፉ ማሩ

March 31/2014


10528_100568456628045_5522392_aበሀገራችን የኑሮ ውድነት ከእለት እለት እየከፋ የድሃውን ህዝብ ጉስቁልና እያበዛ እንደሆነ ነጋሪ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በቤተ መንግሰትና አካባቢ የሚኖሩት ይህ ጉዳይ አይመለከታቸውም፡፡ ለዚህ የኑሮ ውድነት አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የዋጋ ንረት መሆኑን ብዙዎች ይረዳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዛሬ ለፅሁፌ ዋና ማጠንጠኛም የማደርገው የዋጋ ንረት ምንስዔው ምን እንደሆነ በተለይ የመንግሰት ሚና ከዚህ አንፃር ምን እንደሆነ ማስረዳት ነው፡፡
በእኔ አረዳድ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ንረት አቅርቦቱ ሲሻሻል እንደሚቀንስ በሀገራችን እንደ ሲሚንቶ ያለ ጉልዕ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ከወጣበት ጣራ ወርዶ ትክክለኛም ባይሆን ጥሩ የሚባል ደረጃ ደርሶዋል፡፡ ጊዜው መቼ እንደሆነ ባላስታውሰውም በደርግ መንግሰት ማስታወቂያ ሚኒስትር የሚታተም አንድ መፅሄት “ወደ ላይ ተወርውራ የቀረች ኳስ” ብሎ በሀገራችን ዋጋ ከናረ የማይመለስ ነገር እንደሆነ መጣጥፍ ማቅረቡ ትዝ ይለኛል፡፡ እንደምሳሌ የተጠቀመው ግን አንድ ብር የነበረ ውስኪ ሦሰት ብር ገባ የጠርሙስ ውስኪ ዋጋ ቢቀንስም የመለኪያው አልቀንስ አለ የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን የኛ ችግር አይመስለኝም፡፡ የእኛ ችግር ስኳር ቢቀንስ፤ ዱቄት ቢቀንስ፤ ወዘተ የሻይና የኬክ ብሎም የዳቦና ማኪያቶ ዋጋ ይቀንሳል የሚል ተሰፋ የለንም፡፡ ተስፋችን ለምን ጠፋ? ማን አጠፋው? የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ይሆናል፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወደ መቃብር ካልወረደ ወይም አሁን ያሉተ ሰዎች መቃብር ከመውረዳቸው በፊት የዚህችን ሀገር የመሬት ስሪት የሚለውጥ ነገር ለህዝብ ይዘው በመቅረብ ይህን ጉዳይ ከህገ መንግሰት ድንጋጌነት ማውጣት የሚችሉበትን ዕድል ካልተጠቀሙና ተሰፋ ካልሰጡን ተሰፋችንን ያጠፋው ኢህአዴግ መሆኑ ግልፅ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ገዢው ፓርቲም እንደሚያምነው አብዛኛው ሌባ የተሰባሰበው በመሬት ዙሪያ ነው፡፡ መሬት የመንግሰት ነው፡፡ በፍፁም የህዝብ አይደለም፡፡ በፓርቲ ተመርጠው በመንግሰት የተሾሙት ሌቦች እንደፈለጉ የሚያዙበት የሀብታቸው ምንጭ ነው፡፡ ይህ እንዴት ዋጋ ያንራል ማለት ተገቢ ነው፡፡ ዋጋ ማናር ብቻ አይደለም ህይወትም ያስከፍላል፡፡ አለማየሁ አቶምሳን ልብ ይሏል!!
መንግሰት ዜጎችን እያፈናቀለ በሊዝ የሚቸበችበው መሬት አሁን ባለው ሁኔታ እስከ ሰላሳ ሺ ብር በካሬ ሜትር እየተከፈለበት ነው፡፡ በአዲስ አበባችን፡፡ ይህን በሰላሣ ሺ ብር በካሬ ሜትር የሚገዙ ሰዎች የገንዘብ ምንጫቸው ምንድነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በህጋዊ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ በካሬ ለባዶ መሬት (ወርቅ ውስጡ የሌለ ማለት ነው) ይህን ያህል ገንዘብ ከከፈለ፤ ይህን ገንዘብ ለማስመለስ ግልፅ የሆነው ህጋዊ መስመር መሬቱ ላይ ለሚገነባው ቤት ከፍተኛ ዋጋ መጠየቅ ነው፡፡ ይህ ቤት በሽያጭም ይሁን በኪራይ ውድ ይሆናል ስለዚህ እዚህ ቤት ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ወይም የሚሸጥ ዕቃም ቢያንስ የቤት ኪራዩን መሸፈን ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ዋጋውን መጨመር የግድ ይላል፡፡ ይህ ትንተና የሚሰራው አዲስ በሚሰሩ በሊዝ ለተገዙ ቤቶች ነው የሚል የዋህ አይጠፋም፡፡ ነገር ግን ቤት አከራዮች አዲሶቹ ዋጋ ሲጨምሩ የድሮዎችም ይህንኑ ተከትለው ነው የኪራይ ዋጋ የሚጨምሩት፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ሰርቪስ ቤት በሁለት መቶ ብር ተከራይቶ መኖር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በምንም ዓይነት አንድ ሰርቪስ ቤት ከሺ አምሰት መቶ በታች ማግኘት አይቻልም፡፡ ከገቢያችን አንፃር ማሰተካከያ ቢሰራለት ይህ ዋጋ አሜሪካን አገር እንኳን እንዲህ ዓይነት ዋጋ የለም፡፡
በቅርቡ ከአንደ ጓደኛዬ ጋር የመኖሪያ ቤት ገንብተው የሚሸጡ ሪል ኤስቴቶች አካባቢ ጎራ ብለን ነበር፡፡ እነዘህ ቤት ገንቢዎች ዋጋቸው በፍፁም በሀገር ውስጥ የምንኖር ዜጎችን ያማከለ አይደለም፤ ቤታችንን መንግሰት አይሰራልንም የምንል ዜጎችም ብንኖርም እጃችን ተጠምዝዞ መንግሰትን ደጅ እንድንጠና የሚያደርግ ነው፡፡ ለእነዚህ ቤቶች መወደድ አንዱ ምክንያት የመንግሰት የሊዝ ፖሊስ እንደሆነ መረዳት ብዙ እውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቤት ገንቢዎች ከቤት ገዢዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሰበው ለመንግሰት ገቢ ያደርጋሉ፡፡ ከቤቱ ዋጋ አስራ አምሰት ከመቶውን የያዘው ለመንግሰት የሚከፈለው ታክስ ነው፡፡ ሌላው የታዘብኩት ነገር ደግሞ ለዋጋ ንረቱ ከሊዝና ታክስ በተጨማሪ ሌላ አቁስል ምክንያት መኖሩ ነው፡፡ ከጋደኛዬ ጋር ቤቱን መግዛት እንዳለብን ከምታግባባን የሽያጭ ሰራተኛ ማዶ ሌላ ሽያጭ ሰራተኛ ሁለት ሴቶችን ከፊት ለፊቷ አሰቀምጣ ቤቱን እንዲገዙ በተመሳሳይ ዝርዝር መረጃ ሰጥታ የማግባባት ሰራዋን ሰታጠናቅቅ፤ በዋጋው ውድነት ብስጭት በማለት የተለያየ ሃሳብ መሰንዘር ይጅምራሉ አንዷ ግን እንደ መፍትሔ ሃሣብ አቅረበች “አንገዛም ማለት አለብን!!” አለች፡፡ ልክ ነበረች ገዢ ሲጠፋ ዋጋ መቀነስ የታወቀ የንግድ ሰርዓት ውስጥ የሚወሰድ እርምጃ ነው፡፡ ትክክለኛ የገበያ ህግ በሚሰራበት ሀገር ማለቴ ነው፡፡ ጓደኛዋ ግን በዚህ መፍትሔ አልተስማማችም እንዲህ አለች “ምን መሰለሽ እዚህ ሀገር ብዙ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች አሉ፤ እነርሱ ደግሞ በህገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ህጋዊ ማድረጊያ መንገዳቸው አንዱ ቤት መግዛ ነው” ብላ ተጨማሪውን የዋጋ ንረት ምንጭ ነካችው፡፡
ቤት ገንቢዎች ለምን ቤቱን አስወደዱት ብዬ እንደማልከሳቸው ማወቅ አለባቸው ግን በፍፁም ልክ ያልሆነ ነገር በእግረ መንገድ ላስቀምጥ “ይህን ያህል ካሬ ሜትር ቤት በዚይን ያህል ዋጋ” ብለው ማስታወቂያ ሰርተው ለመግዛት የሚሄደው ሰው ግን የሚያገኘው ሰባ ከመቶአይሆንም፡፡ ምን ነው ? ሲባል ለመኪና ማቆሚያ፤ ለመተላለፊያ፤ ለሊፍት፤ ለጋራ አገልግሎት፤ ወዘተ የሚሉ ቦታዎች ተደምረውበታልይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል ቤት ፈላጊዎችን እንደሚያሳስት ግን ከሻጮቹም የተሰወረ አይደለም፡፡ ማስታወቂያው ሀቅን መሰረት ያድርግ!!
ለቤት ገንቢዎች በእግረ መንገድ ያለኝ ምክር ነው፡፡
በዚህች ሀገር የገበያ ህግ እንዳይሰራ እነዚህ ህገወጦች በቀጥታ በጉቦ፣ አገልግሎት በመንፈግ የሚያደርሱብን ጉዳት አልበቃ ብሎዋቸው
ሰርቀው ያገኙትን ገንዘብ ህጋዊ ለማድረግ ምስኪን ዜጎች ማረፊያ እንዳይኖረን የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እንዲሁም ለዚህም ዋነኛው ተባባሪ
በውድ መሬት የሚቸበችበው መንግሰት መሆኑ ታሰቦኝ፤ እንደ አዲሰ እውቅት መብገን ጀመርኩና እናንተም ትበግኑ ዘንድ ነው ይህን
ላካፍላችሁ የወደድኩት፡፡ እንግዲ ይህ ገፊ ምክንያት ሆኖን የመሬት ሰሪቱ በዕለት ከዕለት ኑሮዋችን መጥቶ እያሰቃየን ነው ብልን ለለውጥ
ካልተነሳን፣ ሌላ ምን በቂ ምክንያት ነው የምንጠብቅው? የሚለው ጥያቄ በእንጥልጥል የሚቆይ ነው፡፡
በህጋዊ መንገድ መሬት የሚፈልጉ ሰዎችም ከህገወጦቹ ጋር ነው ግብ ግብ የሚያያዙት፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የቁጥ ቁጥ መሬት
አቅርቦት ፖሊስ ነው፡፡ መንግስት የመሬት አቅርቦቱን ሆን ብሎ እያሳጠረ፤ ሌቦቹ እንዲመቻቸው ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ ነው፡፡ መሬት
በመግቢያዬ እንዳልኳችሁ የመንግሰት ነው እንጂ በፍፁም የህዝብ አይደለም፤ ህዝብማ በመንግሰት እጅ በተያዘ መሬት ሰበብ የሻይና
ማኪያቶ ዋጋ ላይ ጭምር ጫና የሚፈጥር ሆኖበታል፡፡ የዚህ መሬትን በመንግስት እጅ የማቆየት ፖሊስ ዋናው ገፊ ምክንያት ፖለቲካም
መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መሬቱን ይዞ የሊዝ ሂሣብ ሳይከፍል፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይኖርበት፣ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ አሰገብቶ
ኮንዶሚኒየም በርካሽ እሰራላሁ እያለ ለዚህም በስልጣን መቆየት አለብን እያለ ይገኛል፡፡ ገዢው ፓርቲ፡፡ ዋናው ፖለቲካዊ ግቡ በስልጣ
ገዢውን ፓርቲ ማቆየት ነው፡፡ ይህ ገዢ ፓርቲ በስልጣን ላይ ከቆየ ገዢ መደቦች እየሰረቁ ገንዘብ ያገኛሉ፤ በስርቆት ያገኙትን ገንዘብ ደግሞ
በውድም ቢሆን መሬት በመግዛት ዘላቂ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው በኢኮኖሚ ደንዳና የሆነ ሰርዓት ይገነባል ብለው ያምናሉ፡፡
ይህች ፍልሰፍና ግን የብዙሃኑን ተጠቃሚነት በጎዳ መልኩ ስለሆነ እየተሰራ ያላው በምንም መልኩ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ በአሸዋ ላይ
የተሰራ ቤት ዓይነት ነው፡፡ አውሎ ንፋስ አይጠብቅም ትንሽ ንፋስ ጠራርጎ ያፈርሰዋል፡፡ ልብ መግዛት ያለብን ይመስለኛል፡፡
ፅሁፌን ከዘጋው በኋላ ዋጋው በአቅርቦት መሻሻል ይቀንሳል ብለን ተሰፋ ያደረግነው ሰኳርም ቢሆን የዋጋ ጭማሪ ያደረገ መሆኑን በሬዲዮ
ሰማው፡፡ ይህ ምንም አያስገርምም፡፡ የሚያስገርመው መግለጫ የሰጡት ኃላፊ ማብራሪያ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪ የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገር
ግን ለትራንስፖርት ተብሎ ዘጠና አምሰት ሳንቲም በኪሎ ተጨመረ እንጂ፤ የዚህ ምክንያት ደግሞ ቀደም ብሎ ሰኳሩ ከውጭ ስለሚመጣ
ከጅቡቲ በቀጥታ ይገባ ስለነበር ነው፡፡ በማለት ቀደም ሲል ስኳር የትራንሰፖርት ወጪ የለበትም የሚል መንፈስ ያለው መግለጫ ሰጡ፡፡
ይህ መግለጫ ህዝቡን እንዴት እንደናቁት ከማሳየት ውጪ አንድም የእውቀትና እውነት መሰረት የለውም፡፡ የዋጋ ጭማሪ አይደለም
የትራንሰፖርት ነው!! ምን የሚሉት ፌዝ ነው፡፡ ዋጋ እንዴት ነው የሚተመነው? ፋብሪካው ይህ የመጀመሪያ ምርቱ ነው? እሰከዛሬ
ትራንስፖርት ማን ነበር የሚሸፍነው? መግለጫውንም ሁሉንም ትተን አሁንም ቢሆን በተጨመረው ዋጋ ስኳሩ የታለ ነው? ያለው
ጭማሪውን ዋጋም ጨምሮ ይገዛል፡፡ የሌለው ድሮ ከሚገዛው መጠን ቀንሶ ይገዛል፡፡ በተለይ የመንግሰት ሰራተኛው በቅርቡ የትራንሰፖርት
ዋጋ ተጨመረበት፣ አሁን ደግሞ የስኳር ማጓጓዣ ተጨመረበት፣ ቀጥሎ ስኳርን ተከትሎ ዳቦ ይጨምራል ወዘተ.. ደሞዝ ግን እንዳለች ነው፡
፡ መፍትሔው ልጆችን ስኳር ለጤና ጥሩ አይደለም ብሎ ማስተው ነው፡፡ ዳቦ እንዴት ተብሎ ይከለከል ይሆን?
ታስታውሱ እንደሆነ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደረ ዋጋ ይጨምር የነበረው ሙገር ሲምንቶ ፋብሪካ አሁን ዋጋ መቀነሱን ማስታወቂያ
ከፍሎ እየነገረን ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሰት ያልሆኑ ተወዳዳሪዎች ስለመጡበት እና እየመጡበት ስለሆነ ነው፡፡ ስኳር ይህን እድል
እንዳያገኝ ማዕቀብ ያደረገብን መንግሰት ነው፡፡ ሁሉም ፋብሪካ እኔ እስራለሁ ብሎ፡፡ ቢሰራውም ዋጋ አይቀንስም፡፡ ለምን? የሚታለብ ላም
ነው ይለናል፡፡ ስለዚህ ይህን የኑሮ ውድነት የጫነብን እየጫነብንም ያለው፣ በመንግሰት ስም የተቀመጠው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘራፊ
ቡድን ነው፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

No comments: