Sunday, March 30, 2014

በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በራሪ ወረቀት ተበተነ::

March 30/2014


በሰሜን ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ተከታታይና ቀጣይ የሆኑ አውደ ውጊያዎችን በመፈጸም የወያኔን ጦር እያሽመደመደው ከመሆኑም በተጨማሪ ግንባሩ በአሁኑ ሰዓት የአካባቢውን ማሕበረሰብ የማንቃት፣ የማደራጀትና የመቀስቀስ ተግባር ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ሲሆን የደርጅቱን ዓላማና ፕሮግራም ያነገቡ በራሪ ወረቀቶችንም በብዛት በማዘጋጀት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲደርሱ ተግቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በመጋቢት 20 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ዓላማና ፕሮግራም ያነገቡ በራሪ ወረቀቶች በብዛት የተበተነ ሲሆን በአካባቢው ነዋሪ የማሕበረሰብ ክፍሎች እነዚህ በራሪ ወረቀቶች በብዛት የተሰራጩ ከመሆኑም ባሻገር ወረቀቶቹ ባልተዳረሱበት አካባቢ ለማሰራጨት ነዋሪዎች ተግተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርተራችን ከስፍራው ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ይህንኑ በራሪ ወረቀት ወደ ሕብረተሰቡ በፍጥነት እንዲሰራጩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል በሚልና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ባለው ጉዳይ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በገዢው ቡድን ታጣቂ ሃይሎች እየታደኑ ለእስር መዳረጋቸውን እንዲሁም በትክል ድንጋይና አካባቢዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን መረጃው ጨምሮ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ አካባቢ የተበተነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በራሪ ወረቀት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሰፊው እንዲሰራጩ የአካባቢው ወጣቶች በራሪ ወረቀቶቹን እያባዙ በመበተን ላይ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ግ) የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳትና ተጨባጭ የወያኔ እንቅስቃሴዎችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለበለጠ የፀረ- ወያኔ ትግል የሚያነሳሱ በራሪ ወረቀቶች በማሰራጨትና የትጥቅ ትግሉ የደረሰበትን የዕድገት አቅጣጫና አናሳው የወያኔ ቡድን በሕዝብ እና በሀገር ላይ እየፈጸመ ያለውን ስውር ደባ በማጋለጥ በኩል ጉልህ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ በመሆን ሕዝብን ወደ ትጥቅ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀሉ ተነሳሽነትን የፈጠረ መሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ማሕበረሰብ መናገራቸውን የሪፖርተራችን መረጃ ያስረዳል።

በመጨራሻም በራሪ ወረቀቶቹ በተሰራጩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፍራው ለሚገኘው ሪፖርተራችን እንደገለጹለት ከሆነ በራሪ ወረቀቶቹ ወቅታቸውን የጠበቁ የሁሉንም ሕብረተሰብ ብሶትና ምሬት ገላጭ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸው ለግንባሩ የሀገር አድን ጥሪ ምላሽ የምንሰጥበት ወቅት ላይ በመሆናችን የግንባሩን ሠራዊት በመቀላቀል የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments: