Saturday, March 29, 2014

የወያኔን ከፋፋይ አገዛዝ እናምክን

March 29/2014

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ ሊከበርላቸውና ሊያሳድጋቸው የሚገቡ የተለያዩ የባህልና የታሪክ ቅርሶች ያሏቸውን ያህል በብዙ መንገድ የሚያይዝ የጋራ ታሪክ ቅርስና ዝምድና አላቸው። ልዩነቶቹ ራሳቸው ተጠቃቃሚ ለሆነ የእርስበርስ ግንኙነታቸው ጠቃሚ እንጂ ከአንድ ሀገር ማህበረሰብነታቸውና ከጋራ ህልማቸው ጋር የሚጋጩ የጠብና የግጭት መንስኤዎች አይደሉም። ከጠብና ግጭት ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ተጠቃሚ አይደለም። ከጠብና ግጭት ጥቅም ይገኛል ብለው የሚያስቡ “ግርግር ለሌባ ይመቻል” የሚለውን የወሮ በላ ፍልስፍና የሚከተሉ የቀን ጅቦች እንጂ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች አይደሉም። በወያኔ የግዛት ዘመን የደረሱትን ግጭቶች መፈናቅሎችና የተፈጠሩትን የእርስበርስ ጥርጣሬዎችን ልብ ብሎ ለተመለከተ ሁሉም በአገዛዙ እና በሎሌ የበታች ሹማምንቱ የተፈጠሩ እንጂ አንድም ጊዜ እንኳን ከህዝብ የመነጩ አይደሉም።
የወያኔ ጉጅሌ በአገዛዝ ዘመኑ ሁሉ ብሄር ብሄረሰቦችን ከሚያይዟቸው የጋራ ማህበራዊ ቅርሶችና ህልሞች ይልቅ ካለመታከት ልዩነቶቻችን ላይ ያተኮረ ፖለቲካ እያካሄደ እንዳለ ግልጽ ነው። ከዚህ አልፎም አዳዲስ የእርስበርስ ግጭቶችን እና ጠቦች እንዲፈጠሩ ተግቶ የሚሰራ ከፋፋይ ቡድን ነው። እርስበርሱ መጠራጠርና መፈራራት እንዲሰፍን ልዩ ልዩ ስልቶችን ይቀይሳል። ከአንዱ ብሄረሰብ ተንኳሽ አዘጋጅቶ ሌላው ብሄረሰብ ላይ አደጋ እንዲደርስ ከዚያም ተጠቃሁ የሚለው አጸፋ እንዲመልስ ያደርጋል። የአንዱን ብሄረሰብ መንደርና ንeበረት በእሳት ለኩሶ በሌላው ብሄረሰብ እንዲመካኝ ያድርጋል። አንዱ በአንዱ ላይ እንዲያማርር ከንፈሩን እንዲነክስ ማድረግ ለወያኔ ጉጅሌዎችና ለሎሌዎቻቸው እንደፖለቲካ ጥበብ ከታየ ሁለት አስርት አመታት አልፈዋል። በየትኛውም የሀገራችን አካባቢዎች የተቀሰቀሱ የርስበርስ ጥርጣሬዎችና ግጭቶችን ያሸተተ ሁሉ ወያኔ፣ ወያኔ እንደሚገሙ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው።
ወያኔዎች የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ከፋፍለውና ከቻሉም አጋጭተው ካልሆነ በስተቀር የዝርፊየ ኢኮኖሚያቸውን መቀጠል እንደማይችሉ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የጋራ ጥቅማቸውንና ህልማቸውን ይዘው የተነሱ እለት ወያኔ ያከተመለት መሆኑን ያውቃል። ለዚህም ነው በየክልሉ እና ዞኑ በፍጹም ከሆዳቸውና ጥቅማቸው በላይ ማሰብ የማይችሉ ግለሰቦችን ከየብሄረሰቡ እየመረጠ የሚሾምልን። ወያኔ ነጻ የህዝብ ምርጫ የሚፈራው ለዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡
የወያኔ ጉጅሌዎች ከጊዚያዊ ጥቅም በዘለለ ማሰብ ስለተሳናቸው እንጂ ይህ አካሄዳቸው ለራሳቸውም ለዘለቄታው የማይጠቅም መሆኑን ዘንግተውታል። በልዩነታችን ላይ መጫወት ማለት በእሳት እንደ መጫወት የማይመስላቸው ለዚህም ነው። ይህ የተጀመረው እሳት ራሳቸውንም አይምርም።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ መላው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች የጋራ ግብና የተሻለው የነገ ነጻነት ተስፋቸው የሚረጋገጠው በጋራና እጅ ለእጅ ተያይዘው በሚያደርጉት ትግል ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ የወያኔ መሰሪ የከፋፍለህና አጋጭተህ ግዛ ተንኮል ራሳችንን እንዳናመቻች የገዛ መከራችንን ማራዘሚያ እድል ለዘራፊ ገዥዎቻችን እንዳንሰጥና ለጋራ ህልማችን እንድንቆም ጥሪውን ያቀርባል።
የወያኔ ጉጅሌ ሆን ብሎ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እንዲጋጩ፣ እርስበርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩና እንዲፈራሩ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ድርጊቱ በእሳት መጫወት መሆኑን አውቆ ከዚህ እኩይ ተግባር እንዲታቀብ ግንቦት 7 እያሳሰበ በማንኛውም ሁኔታ በማህበረሰቦች መካከል ለሚደርስ ግጭትና ጉዳት ሙሉ ሀላፊነቱ የወያኔና የወያኔ ብቻ መሆኑን አጥብቆ ያስገነዝባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments: