Tuesday, March 25, 2014

ሰበር ዜና የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተፈናቃዩች ተጥለቀለቀ

March 25/2014

1510357_10201735795417514_1563874087_n
ተፈናቃዩቹ ከጎንደር አካባቢ ተነስተው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ዳኖ ወረዳ በመውረድ በእርሻ ስራ የተሰማሩ ገበሬዎች ናቸው፡፡ከ1996ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ‹‹ክልላችንን ለቅቃችሁ ውጡ››ሲባሉ ቆይተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማስፈራሪያው ወደ ግድያ፣ድብደባና ወከባ በማደጉ ለአቤቱታ አካባቢያቸውን ጥለው አዲስ አበባ ለመግባት ተገደዋል፡፡ከተፈናቃዩቹ መካከል የተወሰኑት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተ/ብርሃን ጽ/ቤት በማምራት አፈ ጉባኤውን ለማናገር ቢሞክሩም ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡የአፈ ጉባኤው ጸሐፊ ጉዳያችሁ ታይቷል ወደ መጣችሁበት ተመለሱ››ያለቻቸው ቢሆንም ተፈናቃዩቹ ‹‹ብንመለስ ሊገድሉን ስለሚችሉ አንመለስም››የሚል አቋም ይዘዋል፡፡

ከ26 የሚልቁ ሰዎች በአደባባይ ድብደባ ደርሶባቸው እጅና እግራቸው እንደተሰበረ የሚናገሩት ተፈናቃዩቹ‹‹አቶ ጌጡ ክብረት የተባለ ግለሰብ በገበያ ቦታ በገጀራ ተቆራርጦ ህይወቱ ማለፉን በሀዘን ስሜት ተውጠው ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ማረፊያ ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን የሚገልጹት ተፈናቃዩቹ ወደ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ጽ/ቤት በመምጣት ‹‹ፍትህ እንድናገኝ ለኢትዩጵያ ህዝብ ሰቆቃችንን አሰሙልን››በማለት ተማጽነዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ ‹‹ህገ መንግስቱ በግልጽ እያንዳንዱ ዜጋ በፈለገው ክልል በመሄድ ንብረት ማፍራት እንደሚችል ቢደነግግም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ህገ ወጥና አስቸጋሪ ነው››ብለዋል፡፡

No comments: