Wednesday, March 19, 2014

የአባይ ግድብ መዋጮ መቀዝቀዙ መንግስትን ስጋት ላይ ጥሎታል

march 18/2014

ኢሳት ዜና :- በያዝነው ወር የሶስተኛ ዓመት የምስረታ ልደቱ የሚከበርለት የአባይ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከወጣው ወጪ በሕዝብ መዋጮ መሸፈን የተቻለው 26 በመቶ ያህሉን ብቻ መሆኑና ሕዝቡ ለግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ መቀዛቀዝ ማሳየቱ ታውቋል።

ግድቡ በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ በይፋ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በወቅቱም የገንዘብ ምንጩ ሕዝቡ እንደሚሆን በተናገሩት መሰረት በተለይ የመንግስት ሠራተኛውና ባለሃብቱ ሳይወድ በግድ እንዲያዋጣ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ለግድቡ ግንባታ በጠቅላላው ከ80 ቢሊየን ብር በላይ የሚያስፈልግ መሆኑንና እስካሁን ለግድቡ ግንባታ 27 ቢሊየን ብር ገደማ ከመንግስት ካዝና መውጣቱን ተነግሮአል፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሕዝቡ ቦንድ ለመግዛት ቃል የተገባው 11.5 ቢሊየን ብር ሲሆን መሰብሰብ የተቻለው ግን 7.1 ቢሊየን ብር ብቻ ነው፡፡

መዋጮው የመንግስትና አንዳንድ የግል ድርጅት ሠራተኞች ሳይወዱ በግድ ከፔሮላቸው በየወሩ እየተቆረጠ ገቢ የሚሆን በመሆኑ አብዛኛው መዋጮ የተሰበሰበው ከወርሃዊ ደመወዝተኛው መሆኑ ከግንባታው ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቶአል፡፡

አብዛኛው ባለሃብትና ነጋዴዎች ከንግድ ሰርዓቱ መዛባትና ከስርዓቱ ኢ-ፍትሐዊ እርምጃዎችጋር በተያያዘ እንዲሁም የቦንድ ሰርተፍኬቱን ለባንክ ብድር ማስያዝ ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ የገቡትን ቃል መፈጸም እንደተሳናቸው ታውቆአል፡፡

የቦንድ ሸያጩን በውጪ አገር የሚኖረው ዲያስፖራ እና በገጠር የሚኖረው አርሶአደርና አርብቶአደር የህብረተሰብ ክፍልን በማሳመን ለማስፋት ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ቢደረግም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱና በተለይ የአርሶአደሩ ገቢ ከእጅ ወደአፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሳካት አለመቻሉ ታውቆአል፡፡በውጪ አገር የሚኖረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መቅደም ያለበት የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው በሚል አገዛዙ ከኢሰብዓዊ ድርጊቶቹ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ መጠየቁ የስርኣቱን ከፍተኛ አመራሮች ባለማስደሰቱ ከገቢ ማሰባሰቡ ስራ እንዲያፈገፍጉ ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

በአገር ውስጥ በተለይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የግድቡ ግንባታ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተጠቀመበት በመሆኑና ስለጉዳዩም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማሳተፍ ፍላጎት አለማሳየቱ በብዙዎቹ ዘንድ ጉዳዩ በአሉታ እንዲነሳ እያደረገው ይገኛል፡፡  በዚህም ምክንያት ለግድቡ መዋጮ የህዝቡ መነሳሳት እንዲቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ከግብጽ መንግስትና ፖለቲከኞች ጠንካራ ተቃውሞ እየቀረበበት የሚገኘውን የአባይ ግድብ ዓለምአቀፍ ጋዜጠኞችን ለማስጎብኘት የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ማቅረቡ ተሰማ፡፡በዚሁ መሠረት 13 ያህል ዓለም አቀፍ የፕሬስ ተቋማት ፍላጎት ማሳየታቸውንና በቅርቡ ጉብኝቱ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

በአቶ ሬድዋን ሁሴን የሚመራው የመንግስት የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ጉብኝቱን ያዘጋጀው ግንባታውን አስመልክቶ ጋዜጠኞች የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ እንዲኖራቸው ታስቦ ነው ተብሎአል፡፡

ሆኖም በዚህ ጉብኝት የሚሳተፉ ሚዲዎች ዝርዝር እና ጉብኝቱ መቼ እንደሚካሄድ የተነገረ ነገር የለም

No comments: