Monday, March 24, 2014

የአንድነት እና መኢአድ ዉህድ ፓርቲ የመድረክ አባል አይሆንም ተባለ

March  24/2014

መኢአድ እና አንድነት መጋቢት 11 ቀን የቅድመ ዉህደት ፊርማ ይፈረማሉ ተብሎ ሲጠበቅ ፣ ከመኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ አበባው መሃሪ በተጻፈ ደብዳቤ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ፊርማው እንዲዘገይ መደረጉ በስፋት ተዘግቧል። አቶ አበባዉ የቅደመ ዉህደቱን ፊርማ ላለመፈረም ሶስት ያልተፈቱ ነጥቦች የሚሏቸውን ያቀርባሉ። ነጥቦቹም የዉህድ ፓርቲው ስያሜን፣ የመሪዎች መመዘኛን እና አንድነት ከመድረክ ጋር ያለዉን ግንኙነት የሚመለከቱ ናቸው።
አቶ አበባዉ ባቀረቧቸው ነጥቦች ዙሪያ ምላሽ የሰጡት የአንድነት ዋና ጸህፊ አቶ ስዩም መንገሻ ፣ የቀረቡት ነጥቦች ንግግር ተደርጎባቸው ምላሽ የተሰጣቸውና ስምምነት የተደረሰባቸው መሆኑን፣ ወደ 800 ታዳሚዎች በነበሩበት የደብተራዉ ፓላቶክ ክፍል ቀርበው፣ መጋቢት 13 ቀ 2006 ዓ.ም በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።
አቶ ስዮም የመድረክና የአንድነት ግንኙነት እንደ ነጥብ መነሳቱ እንዳስገረማቸው ይናገራሉ። «አንድነት እና መኢአድ ሲዋሃዱ አንድነት እንደ ፓርቲ አይኖርም። ይፈርሳል። ምርጫ ቦርድም ከመድረክ ውስጥ ሆነ፣ እንደ ደርጅት ይሰርዘዋል። ዉህዱ ፓርቲ አዲስ ፓርቲ ነው የሚሆነው። መድረክ ዉስጥ መግባት ካስፈለገም እንደ ገና ሀ ተብሎ ለመድረክ ማመልከቻ ገብቶ፣ ለምርጫ ቦርድ አሳዉቆ ነው የሚሆነው» ሲሉ የአንድነት እና የመኢአድ ዉህድ ፓርቲ የመድረክ አባል እንደማይሆን በግልጽ አስቀምጠዋል። «ይሄንንም የመኢአዱ ሊቀመንበር ጠንቀቀው ያወቁታል» ያሉት አቶ ስዩም በዚህ ረገድ ጥያቄ መነሳቱ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ይናገራሉ።
የዉህዱን ፓርቲ የሚመሩ መሪዎች መመዘኛ ሊኖር እንደሚገባ በአቶ አበባዉ የቀረበውን ነጥብ በተመለከተ አቶ ስዩም አንድነት በዚህ ጉዳይ እንደተስማማ ገልጸዋል። የዉህድ ፓርቲዉን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመናብርት የሚመርጠዉ ከሁለቱን ድርጅቶች እኩል የተወጣጣ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነ የገለጹት አቶ ስዩም ፣ «በቅድመ ስምምነት የድርጅቱን መሪዎች አይወሰኑም። የዉህዱን ፓርቲ የሚመሩት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በጠቅላላ ጉባኤዉ የተመረጡ ናቸው» ሲሉ ስምምነት የተደረስበትን የመሪዎች የመሪዎችን አመራረጥ ሁኔታ አስረድተዋል።
የዉህዱ ፓርቲ ስም ምን ይሁን በሚለው ዙሪያ ስምምነት እንደተደረሰ አቶ ስዩም ይናገራሉ። «እነርሱ መኢአድ/አንድነት የሚል ስም፣ አንዴ ደግሞ የመላዉ ኢትዮጵያ አድነት ፓርቲ (መኢዴፓ) የሚል ስም አቀረቡ። እኛ መኢአድ/አንድነት የሚለው መዋሃዳን አያሳይም በሚል አስልተስማማንም። መኢአፓ የሚለዉን በግማሹ ተቀብለነው «መላው» የሚለው ቃል ወጥቶ «የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ» ይሁን አልናቸውም» ያሉ አቶ ስዩም በስሙ ዙሪያ የነበረዉን ዉይይት ይዘረዝራሉ። ሲያክሉም «እና ፓርቲ ከሚባል ትግሉ የሕዝብን ጥያቄ ያዘለና ሕዝባዊ በመሆኑ ፓርቲ ከሚለው ቃል ይልቅ ንቅናቄ የሚል እንዲገባበት ፈለግን። በኋላ ግን ሁለተቻንም ሁለት ሁለት ስሞችን እንድናቀርብ፣ አባላትና ደጋፊዎች ደግሞ ስም እንዲያቀርቡ በመጠየቅ፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በድምጽ ብልጫ ስሙን ይወስን በሚለው ተስማምተን ጨርሰናል» ሲሉ አቶ ስዩም የዉህዱ ፓርቲ ስም ምን ይሁን የሚለዉም ጉዳይ እልባት የተግኘለት እንደሆነ ይናገራሉ።
በአቶ አበባዉ የቀረቡ ሶስቱም ነጥቦች በስፋት ንግግር የተደረገባቸውና እልባት የተገኝላቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ስዮም፣ ሌሎች ንግግር ያልተደረገባቸው፣ ያልተፈቱ ጉዳዮች ካሉ፣ አንድነት ለመነጋገር ምን ጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል። «ከአሁን በኋላ እኛ የምናደርገው ነገር የለም። በአንድ እጅ አይጨበጨብም። እኛ አልተፈቱም የምንላቸው ነጥቦች አሉ ብለን አናስብም። ከነርሱ ጋር ከሁለት አመታት በላይ ነው የተነጋገርነው። አይ ይሄ ችግር አለ የሚሉት ነገር ካለ ያቅርቡና እንነጋገራለን» ሲሉ በአቶ አበባዉ የቀረቡት ሶስት ነጥቦ ምላሽ ያገኙ እንደመሆናቸው፣ ሌሎች በአቶ አበባዉ ደብዳቤ ያልተካተቱ፣ ከዚህ በፊት ስምምነት አልተደረሰባቸው የሚባሉና በአንድነት ዘንድ ያልታወቁ፣ ነጥቦች ከቀረቡ አንድነት ለመወያየት ሁሉጊዜ ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ ስዩም «ኳሷ መኢአድ ሜዳ ላይ ነዉ ያለቸው» ሲሉ አንድነት ከመኢአድ አዎንታዊ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የመኢአድን ፋይል ሳጥን ዉስጥ ለጊዜው ከቶ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል።
መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም የአንድነት እና የመኢአድ ላእላይ ምክር ቤቶች ዉህደቱ በአንድ ወር ጊዜያት እንዲጠናቀቅ፣ የቅደም ዉህደቱም ስምምነት መጋቢት 11 ቀን እንዲፈረም በሙሉ ድምጽ መወሰናቸው ይታወቃል። አቶ አበባዉ የመኢአድ ላእላይ ምክር ቤት ዉሳኔን ቀልብሰው ፣ በግላቸው ስምምነቱን ላልተወሰን ጊዜ እንዳይፈረም የማድረግ መብት እንደሌላቸው፣ ከመኢአድ አመራር አባላት በኩል የሚነሱ አስተያየቶች እየተሰሙ እንደሆነም ለማረጋገጥ ችለናል። የአዲስ አበባ የመኢአድ ምክር ቤትን ጨምሮ፣ በየክልሉ ያሉ የመኢአድ አስተባባሪዎችና መዋቅሮች ፣ ምክር ቤቱ ወስኖ ስምምነቱ ለምን እንዳልተደረገ እየጠየቁ መሆናቸውንም ለማረጋገጥ ችለናል።
በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ የመኢአድ እና የአንድነት የቅድመ ዉህደት ፊርማ ለጊዜው አለመፈረሙ ጊዜያዊ ስቅታ እንጂ እንደ ትልቅ ችግር የሚታይ እንዳልሆነ ይናገራሉ። «በአንድነት ዘንድ በሩ ክፍት ነው። አቶ አበባዉ ባነሷቸው ነጥቦች ዙሪያ ስምምነት ተደርሷል። የመኢአድ አባላትና ደጋፊዎች ፣ ምክር ቤቱም ዉህደቱን ይፈልጉታል። የዉህደቱ ንግግሩ በችኮላ ወይም ለምርጫ ሲባል የተደረገ ሳይሆን ከሁለት አመታት በላይ የፈጀ ነው። የዉህደቱ እንቅስቃሴ 98% ተጠናቋል» ሲሉ ያስረዱት እኝሁ ተንታኝ የቀረው 2% ፣ አቶ አበባው እንዳይፈርሙ ያደረጋቸው ሌላ ምክንያት ካለ፣ ግልጽ በሆነ መንገድ አቅርበው፣ ውይይት በማድረግ ስምምነቱን ማጠናቀቅ እንደሆነ ይናገራሉ።


No comments: