Tuesday, March 25, 2014

ሕወሃቶች አሰብን እናስመልሳልን እያሉ ነው !

March 24/2014
በሕዝብ ብዛት ቁጥር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከአለም ደግሞ አሥራ አምስተኛ ናት። ወደ ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖራት፣ ያን ያህል ሕዝብ ኖሯት የባህር በር የሌላት ብቸኛ አገር ናት። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ብዙ ሕዝብ ኖርቷት የባህር በር የሌላት አገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆን ሕዝብ ያላት ዩጋንዳ ናት። የቀድሞ ጥቅላ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በባህር ወደብ ዙሪያ ሲጠየቁ «ለእድገት ይባህር ወደብ የገድ አያስፈልግም። ስዊዘርላንድን ናታም እንዴ ? ያደገች አገር ናት ፤ ግን ወደብ ይላት» ይሉ ነበር። ስዊዘርላን በሕዝብ ብዛት ከአለም ዘጠና አራተኛ ስትሆን ወደ 7 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ብቻ ነው ያላት።
ሕወሃቶች፣ በአንድ በኩል «ከኤርትራ ጋር ታብራላችሁ» እያሉ ዜጎችን በሽብርተኝነት ተራ ክስ እያሰሩ፣ በሌላ በኩል እራሳቸው የሻእቢያ ጥቅም የሚያስጠብቅ ፖሊሲን አጥብቀው በመያዝ «አሰብ የኤርትራ ናት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም» እያሉ ሲከራከሩ እንደነበረ በስፋት የሚታወቅ ነው።
የአረና ፓርቲ አመራሮች፣ በተለያዩ በትግራይ የሚገኙ ከተሞች በሚያደርጓቸው ዘመቻዎች በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን የተረዱት ሕወሃቶች ከዚህ በፎኢት በሚያራምዷቸውና በሕዝብ ዘንድ ተቃዉሞ ባስነሳባቸው ፖሊሶዎቻቸው ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ እየተናገሩ መሆናቸው የሚገልጹ መረጃዎች እየቀረቡ ነው።
በዋናናት አሰብ የኢትዮጵያ እንደሆነ በመግልጽ አረና ያቀረባቸው ቅስቀሳዎች በሕዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘታቸው ሕወሃቶች « እኛም አሰብን እናስመልሳለን» እያሉ ነው። አብርሃ ደስታ በዚህ ጉዳይ ላይ የዘገበዉን ለማንበብ ከታች ያለውን ይመልከቱ!
=============================================================
ህወሓቶች ሰግተዋል “ህወሓት ካልተመረጠ የትግራይ ማንነት ይጠፋል” እያሉ ነው – አብርሃ ደስታ
ህወሓቶች በዓረና እንቅስቃሴና በትግራይ ህዝብ የተቃውሞ መንፈስ በጣም ደንግጠዋል። የዓረና ተከታታይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ተከትሎ ህወሓትም ተከታታይ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ለማድረግ ወስኗል፤ ጀምሯልም። የህዝብ ተወካዮች ተብለው የተመረጡ የየአከባቢያቸው ህዝብ እንዲሰበስቡ መመርያ ተሰጥቷል። ይቅርታ የህዝብ ተወካዮች ሳይሆኑ የፓርቲ ተወካዮች መባል አለባቸው፤ ምክንያቱም የተመረጡት በህዝብ ሳይሆን በህወሓት ነው። የሚያገለግሉትም ለህዝብ ሳይሆን ለህወሓት ነው። ምክንያቱም በህዝብ ተመርጠው ተብለው የህዝብ ችግር ከመናገር ይልቅ የህወሓትአጀንዳ ደግፈው የሚያጨበጭቡ ናቸው። እስካሁን የመረጠውን ህዝብ ችግር የተናገረ የህዝብ ተወካይ የህወሓት አባል አላገኘሁም። በህወሓት የፖለቲካ ፍልስፍና የተማእከለ ዴሞክራሲ መሰረት አንድ አባል ከፓርቲው አስተሳሰብ ወጥቶ የፓርቲው ብልሹ አሰራሮች ባደባብይ ወይ በፓርላማ ማጋለጥ አይችልም። ካጋለጠ ከፓርቲው ይባረራል። ለዚህም ነው የህዝብ ተወካዮች ተብለው ፓርላማ ይገቡና የፓርቲው ተወካዮች ሁነው የሚቀሩ።
የህዝብ ወይም የህወሓት ተወካዮች ህዝብ ሲሰበስቡ ፈተና እያጋጠማቸው ነው። የሽረ ተወካይ ህዝቡ ሰድቦ አባሯታል። ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ በዓድዋ ህዝብ ተሰድባለች። የዓድዋ ህዝብ ለቅዱሳን “እናንተ ቤተሰቦቻቹ ለመርዳት እንጂ መቼ ለህዝብ ደህንነት ሰርታቹ ታውቃላቹ?” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። በመቐለም አዲሳለም ባሌማ ህዝብ (ይቅርታ በመቐለ ህዝብ ተብለው የተሰበሰቡ ካድሬዎች ነበሩ) ሰብስቦ እርዱን ማለቱ ታውቋል። የመቐለ ዉሃ በ2007 ዓም ፕሮጀክት ቀርፀን እንፈተዋለን፤ ብቻ እኛን ምረጡ ብሎ ተማፅኗል። የመቐለ ነጋዴዎች ሰብስቦ ችግሮቻቹ ለመፍታት ተዘጋጅተናል ብሎዋል።
አጠቃላይ የህወሓት ስትራተጂ ህዝብን ለመሸወድ ያለመ ሲሆን የሚያጠነጥነውም “ህወሓት ካልተመረጠ የትግራይ ማንነት ይጠፋል” የሚል ነው። “ጠላቶቻችን እየመጡ ናቸው፤ ከህወሓት ጎን ተሰለፉ! ጦርነት ሊከፈትና ልጆቻችሁ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ” እያሉ ይገኛሉ።
ግን የትግራይ ማንነት በህወሓት ህልውና የተንጠለጠለ አይደለም። እንኳን የህዝብ ማንነት የአንድ ግለሰብ ማንነትም ሊጠፋ አይችልም። ምክንያቱም የህዝብ ማንነት ቀርቶ የአንድ ሰው ማንነት ከጠፋ የሰውየው መብትና ነፃነት ተጥሷል ማለት ነው። መብቱ ወይ ነፃነቱ ከተጣሰ ደግሞ አዲስ የመጣ ስርዓት ልክ እንደ ህወሓት አምባገነናዊ ስርዓት ነው ማለት ነው። የህውሓትን ያህል አምባገነን ስርዓት ከመሰረትን ደግሞ ህወሓት አልተቀየረም ማለት ነው። ህወሓት ካልተቀየረ የፖለቲካ ለውጥ አልመጣም ማለት ነው። የፖለቲካ ለውጥ ካልመጣ ደግሞ ትግላችን ይቀጥላል (ለውጥ እስኪመጣ ድረስ)። ስለዚህ እኛ የምንታገለው ከህወሓት የተሻለ ስርዓት ለመመስረት እንጂ ህወሓትን በሌላ አምባገነን ስርዓት ለመተካት አይደለም። ስለዚህ ላረጋግጥላቹ የምፈልገው ነገር ቢኖር የማንም ህዝብ ወይ ግለሰብ ማንነት ይከበራል እንጂ አይጠፋም።
“ጠላቶቻችን እየመጡ ነው” የሚለው ዉንጀላ ግዜው ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ነው። የህዝብ ጠላት ጨቋኝ ስርዓት ነው። ህዝብ ከጨቋኝ ስርዓት ዉጭ ሌላ ጠላት የለውም። ጨቋኝ ስርዓት የህዝብ ጠላት እስከሆነ ድረስ እንታገለዋለን። ጨቋኝ ስርዓት ምን ግዜም አንቀበልም። ጨቋኝ ስርዓት ስለማንቀበል ነው አሁን ህወሓትን የምንቃወመው። ስለዚህ ዓላማችን የስርዓት ለውጥ ማምጣት እስከሆነ ድረስ ለጨቋኞች ቦታ የለንም፤ ህወሓትም ሌሎችም። እኛ የምንቀበለው ዴሞክራሲያዊ የህዝብ መንግስት ብቻ ነው።
ህወሓቶች በዓረና አጀንዳዎች በመስጋታቸው ምክንያት የዓረና ሐሳቦችን ለመቀበል እየተገደዱ ነው። በቅርቡ በህዝብ ፊት እየቀረቡ የመሬት ይዞታ ጉዳይ በዓረና እየቀረበ ያለውን ሐሳብ እንደሚደግፉ እየገለፁ ነው። (የዓረና ሐሳብ እንደግፋለን እያሉ ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት እንሞክራለን በሚል ነው። የህዝቡ ፍላጎት ደግሞ የዓረና የመሬት ፖሊሲ ነው)። የዓሰብ ወደብም በሰለማዊ መንገድ ለማስመለስ እንሞክራለን በማለት እየተመፃደቁ ነው። ለነጋዴዎችም ግብር እንቀንሳለን በሚል ምክንያት ለመጀንጀን እየሞከሩ ነው።
አሁን ግራ ሲገባቸው ስራ የሌላቸው ወጣቶች ለውትድርና ለመመልመል እየሞከሩ ሲሆን ማንም ወጣት ፍቃደኛ ሊሆን አልቻለም። በወጣቶቹ ዉሳኔ የተደናገጡ ህወሓቶች የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ህፃናት ልጆች አታለው (ስራ እንሰጣቸዋለን በሚል ምክንያት) ለዉትድርና መመልመላቸው ታውቋል። ለምሳሌ በመቐለ ከተማ የነበሩ ብዙ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ተወስደዋል (ማረጋገጥ ይቻላል፤ አሁን በመቐለ ከነበሩ ህፃናት አንድ የቀረ የለም)። ግን አብዛኞቹ ህፃናት ከ16 ዓመት በታች ናቸው። ከ16 ዓመት በታች ህፃናት ለውትድርና የሚመለምል የቸኛ ሕገወጥ መንግስት ኢህአዴግ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም በማንኛውም ሕግ ከ16 ዓመት በታች ህፃናት ለውትድርና መመልመል ሕጋዊ ሊሆን አይችልም። ጉዳዩ የሚከታተለው ካገኘ በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ሊሆን ይችላል።
በዓዲግራት የፈፀሙብንን ድብደባ በጣም አክስሮባቸዋል። የትግራይ ህዝብ ሙሉበሙሉ እንዲጠላቸው ሁነዋል። እናም በጣም ሰግተዋል። በቅርቡ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊጀምሩ ይችላሉ። በወታድሩም ቢሆን ህወሓቶች ድጋፍ የላቸውም።
ፓርቲዎች መዋሃድ ያለባቸው በያዙት ፕሮግራም፣ ስትራተጂና የፖለቲካ አቅጣጫ መሰረት ነው። የፕሮግራም፣ ስትራተጂና የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም አጠቃላይ ርእዮተ ዓለም ልዩነት ካላቸው ብቻ ነው ተለያይተው መቀጠል ያለባቸው። አሁን ፓርቲዎች እንደተለያዩ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን የተለያዩበት (የማይዋሃዱበት) ምክንያት የፕሮግራም፣ ስትራተጂ፣ የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም ርእዮተ ዓለም ልዩነት ስላለባቸው አይደለም። የማይዋሃዱበት ምክንያት የፖለቲከኞቹ የባህሪይ ወይ የአመለካከት አለመጣጣም ስላለ ብቻ ነው። ይህንን የፖለቲከኞች ችግር የሚፈታው ህዝብን በማስተማር ነው። ህዝብን አስተምረን በፖለቲከኞቹ ተፅዕኖ እንዲያሳድር እናደርጋለን። እናም ፖለቲከኞቹ ከሰውኛ አመለካከት ወጥተው መርህ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ በማራመድ ተመሳሳይ አይዲዮሎጂ የሚያራምዱ ፓርቲዎች እንዲወሃዱ ይሆናል። ተዋህደውም ለህዝብና ሀገር አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ ይዘው ይቀርባሉ።

No comments: