Sunday, March 23, 2014

ወላይታ ሶዶ ነፃነት አልባዋ የማፊያ ካድሬዎች ከተማ!!!

March 23/2014

ከወላይታ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የእስርና እንግልት ማብራሪያ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ድርጅት ጉዳይ ም/ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ በደቡብ ቀጠና በወላይታ ዞንና በሲዳማ ዞን አዋሳ ከተማ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የፓርቲውን የትግል ስትራቴጅክ ዕቅዶች ላይ ማብራሪያ፣ ደንብና ፕሮግራም ለመስጠት እንዲሁም የስራ ጉብኝት ለማድረግ በ 12/07/06 ወደ ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡ በ13/07/06 ደግሞ ከሶዶ ከተማ ስራ አስፈፃሚና ከወረዳ አመራር አባላት ጋር የፓርቲያችንን ደንብ፣ ፕሮግራምና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ አስመልክቶ የተሰናዳው ውይይት ላይ ለመታደም ከ32 በላይ አመራሮችም ተገኝተው ነበር፡፡

ቅዳሜ በ 13/07/06 ዓ.ም ከአባላት ጋር ባለው ዕቅድ መሰረት የፓርቲያችንን ህጋዊ ሰነዶችን ለወረዳና ለዞን አመራሮች ለመስጠት፣ ቀጣዩን ሀገራቀፍ ምርጫ አስመልክቶ መረጃ ለመለዋወጥ ምርጫችን የነበረው የፓርቲያችን አባል የሆነውና ወጣ ብሎ ፀጥታ የሰፈነበት ግቢ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት ነበረን፡፡ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የፖለቲካ ደንብና ፕሮግራማቸውን ለዞንና ለወረዳ አመራሮች ለማስጨበጥ ፈቃድ እንደማያስፈልግ ጠንቅቀን እናውቅም ነበር፡፡

በተለይም ሃለማሪያም ደሳለኝ በሞግዚትነት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወላይታ ሶዶ ነፃነት አልባ ከተማ እንደሆነች ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ወላይታ በካድሬ ተወጥራለች፡፡ ዝርዝሩን በቀጣይ እንደምናቀርብ ቃል እየገባን ለአሁን በእኛ ላይ የደረሰውን በቅንጭቡ እንደሚከተለው ለኢትዮጵያ ህዝብና ለታሪክ እናቀርባለን፡፡

1. 32 የሚሆኑ አንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራሮች የተሰባሰቡት ከላይ በገለፅነው አላማና ህገ መንግስታዊ መብታችንን ተጠቅመን ቢሆንም ለውይይት ቅድመ ዝግጅት ስናደርግና ውይይቱን ለመጀመር ስንዘጋጅ መታወቂያ የሌላቸው ከ 8-10 የሚሆኑ ጡንቻቸው የፈረጠመ ግለሰቦች እንደ ኮማንዶ ለውይይት የተገናኝበትን የአባላችንን ጊቢ ሰብረው በመግባት የያዝናቸውን የፓርቲ ሰነዶች፣ ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮችና ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው ሂደዋል፤ አመራሮችን ደብድበዋል፡፡

2. እነዚሁ ደብዳቢዎች ታርጋ ቁጥር በሌላቸው ሞተሮች በመታጀብ ፖሊስ ይዘው በመምጣት ፕሮግራማችንን ለማደናቀፍ በሃይልና በጉልበት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውናል፡፡

3. ፖሊስ ጣቢያውም እኛን የደበደቡንንና ንብረታችንን የቀሙንን ሲቢል ለባሽ ካድሬዎች በመልቀቅ የአንድነት ፓርቲ 20 አመራሮችን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ላሊሼ ኦሌ ቢሯቸው አስገብተው ችግሩን እንደሚቀርፍ አመራር ካነጋገሩንና ቃላችንን ከተቀበሉ በኋላ ሞባይሎቻችንን በመንጠቅ እንድንታሰር አድርገዋል፡፡

4. የእስሩ ሰዓት ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ ነው፡፡ እንድ ቀፋፊና አስቀያሚ ማጎሪያ ውስጥ ካስቀመጡን በኋላ ከምሽቱ 2፡00 ላይ ህገወጥ ስብሰባ አድርጋችኋል በማለት ቃል ስጡ የሚል ምዝገባና ህገ ወጥ ስብሰባ እንዳደረግን እንድንመሰክር ለማስገደድ ቢሞክሩም እኛ መብታችንን እንደተጠቀምን እንጂ እነሱ እንደተረጎሙት ህገ ወጥ ስብሰባ እንዳላደረግን ሀቁን ስንነግራቸው እንዲሁም ሀሰትን ከመቀበል መታሰር እንደሚቻል የአንድነት አባላት ቁርጠኛ እንደሆንን ሲያውቁ ግራ ተጋብተው የበላይ አካል እስከሚያረጋግጥላቸው ጠብቀው ከእኩለ ለሊት በኋላ (ከምሽቱ 6፡30) በኋላ በእስር ላይ የቆዩ ከ20 በላይ ከፍተኛ አመራሮች እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይሄ የሆነው ለመፍታት ታስቦ ሳይሆን ከወረዳ የመጡ አባላት ማደሪያ ቦታ እንዲያጡና ለአደጋ እንዲጋለጡ በማሰብ ነው፡፡

5. ስንታሰር ከተዘረፉ ሞባይሎች ውጭ በፖሊስ ጣቢያ አዛዡ ተይዞ የነበረው የታሳሪዎች ሞባይል ባልታወቀ ነገር ተነክሮ ከአገልግሎት ውጭ ተደርጓል፡፡ ሞባይላችን የተነከረውና ከጥቅም ውጭ የተደረገው በኬሚካል ይሁን በሌላ ነገር አልተረጋገጠም፡፡ የማንኛችንም ሞባይል ግን ከጥቅም ውጭ ሁኗል፡፡ ይሄ የሆነው የፖሊስ አዛዡ አቶ ላሊሼ ቢሮ የታሰረ ሞባይላችን ነው፡፡

ነገ ምን እንደሚገጥመን ማወቅ አይቻልም፡፡ ያረጋገጥነው ነገር ቢኖር ወላይታ ሶዶ ነፃነቷን የተነፈገች፣ በታርጋ አልባ ሞተሮች የምትታመስና ምንም ዋስትናና ህግ የሌለባት ከተማ መሆኗን ነው፡፡ ስለዚህ ነፃነት አልባዋ ወላይታ ነፃ መውጣት አለባት!!!
የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራር አባላት ከምሽቱ 9፡00 ሠዓት



ሶዶ ከተማ

No comments: