Sunday, March 30, 2014

ኤርትራ በደቡብ ሱዳን ቀውስ ጣልቃ መግባቷን መንግሥት ወነጀለ

March 30/2014

ኤርትራ በደቡብ ሱዳን ቀውስ ጣልቃ መግባቷን መንግሥት ወነጀለ
-‹‹የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ወታደራዊ ስምምነት ለሦስተኛ አገር ኪሳራ አለመሆኑን እያጠናን ነው›› መንግሥት
የኤርትራ መንግሥት በወቅታዊው የደቡብ ሱዳን ቀውስ ውስጥ ጣልቃ መግባቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ወነጀለ፡፡ 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ሐሙስ ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የኤርትራ መንግሥት ከዚህ በፊት በሶማሊያ ያደርገው የነበረውን አፍራሽ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ግጭት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ለማተራመስ እየሞከረ እንደሆነ መንግሥት በቂ ማስረጃ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፂዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለመቀልበስ በኢጋድ አማካይነት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የተጀመረው ድርድር ከሦስት ሳምንት ዕረፍት በኋላ በዚሁ ሳምንት መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግሥት የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት ለመጣል ተቃርቦ የነበረውን የሶማሊያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት፣ ቀጥሎ ደግሞ አልሸባብ የተባለውን የሽብር ቡድን መደገፉንና የአገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ ማባባሱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድኖች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን እልባት ያላገኘ የድንበር ግጭት ወደ ሶማሊያ አዘዋውሮታል በሚል እያነጋገረ ነበር፡፡

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው፣ የትኛውን ወገን እየደገፈ እንደሆነ ለጊዜው ይፋ ባይደረግም፣ በደቡብ ሱዳን ቀውስ ጣልቃ ገብቶ ለማተራመስ እየሠራ እንደሆነ በቂ ማረጋገጫ ተገኝቷል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የሶማሊያ ጣልቃ ገብነቱን የሚያስተባብል ሲሆን፣ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ ጣልቃ ስለመግባቱ ከኢትዮጵያ ለቀረበበት ውንጀላ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡

በተያያዘ ዜና በቅርቡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከግብፅ መንግሥት ጋር ካይሮ ውስጥ የሁለትዮሽ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ስምምነቱ የተደረገው ግብፅና ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት በሚወዛጉበት ወቅት መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጅ ተደርጎ የሚታየው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ማድረጉን አስመልክተው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፀጥታ ጉዳይ ተመራማሪዎች፣ ጉዳዩን በተመለከተ በቅርበት ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የኃይል ዕርምጃ እንወስዳለው ከሚለው ተደጋጋሚ ዛቻ አንፃር ይኼ ስምምነት ውዝግቡን እንዳያከረውም ተሰግቷል፡፡

አምባሳደር ዲና ወታደራዊ ስምምነቱን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሁለት ሉዓላዊ አገሮች ማናቸውንም ስምምነት የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ይኼው ወታደራዊ ስምምነት ግን በሦስተኛ ወገን ኪሳራ አለመሆኑን እናጠናለን፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት የደቡብ ሱዳን መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአማፂዎቹ ምክንያት ሥጋት ውስጥ ነው፡፡ አማፂዎቹን የሚያዳክምለት ከሆነ ከማንኛውም አካል ጋር ለመስማማት ዝግጁ ነው ብለው፣ ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የፈለገችበትን ዋነኛ ምክንያት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርበት እንደሚከታተለው ገልጸዋል፡፡

የግብፅ መንግሥት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቋረጥ የተለያዩ ዲፕሊማሲያዊ ጥረቶች በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደረገው ስምምነት የዚሁ አካል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ መንግሥት ጉዳዩን በትኩረት ሊከታተለው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

No comments: