Wednesday, March 5, 2014

በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስትን በጎዳና ነውጥ መናድ፤ አዲሱ የኃይል ፍጥጫ

March 5/2014
የዓለም መገናኛን ብዙሃንን ተቆጣጥረው የሚገኙ ሶስት ሀገሮች አሉ። እነሱም ሶሪያ፣ ቬኑዝዌላ እና ዩክሬን ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በተለይ የምዕራቡ ዓለም የዕለት ዕለት የዜና መረጃ ፎጆታዎች ናቸው። በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት የነውጥ እርምጃዎች የሚዘገቡት ወደ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ምስረታ የሚደረጉ የለውጥ ጉዞዎች ተደርገው ነው። ለዚህ ማረጋገጫ ለማቅረብ፣ ይህን ጽሁፍ እያነበበ ያለ ማንኛውም አካል አልጀዚራን፣ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ፎክስ ወይም የዩሮ ቻናሎችን በመከታተል ማረጋገጥ ይችላል።
እነዚህ የሚዲያ አውታሮች ለምን ማንኛውንም በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ የሚደረጉ የጎዳና ነውጥ እንቅስቃሴዎችን ከዴሞክራሲያዊ ይዘት ጋር አስተጋብረው ይዘግባሉ? የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ አካል መልሱ ብዙም አስቸጋሪ ወይም ውስብስብ አይደለም። ምክንያቱም ሚዲያውን በባለቤትነትና በቁጥጥር በያዙ አካሎች እንዲሁም የሚዲያ ተቋማቱን በገንዘብ ምንጮችነት በሚያሳድሩት አካሎች የሚደረግባቸው የዜና አደረጃጀት እና አዘጋገብ መመሪያዎች ጫና አማካኝነት የሚፈጠር መሆኑን ከግንዛቤ ስለሚወሰድ ነው።
EDWARD S. HERMAN and NOAM CHOMSKY “The Political Economy of the Mass Media” በሚል በፃፉት መጽሃፍ ላይ በአንድ የሚዲያ ተቋም ውስጥ መዋቅራዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ምክንያቶችን አስፍረዋል። ይህም ሲባል፣ “Structural factors are those such as ownership and control, dependence on other major funding sources (notably, advertisers), and mutual interests and relationships between the media and those who make the news and have the power to define it and explain what it means.”
ከላይ ከሰፈረው ፍሬ ነገር አንፃር መዋቅራዊ ተፅዕኖ በአንድ ሚዲያ ላይ ማሳረፍ ለምን አስፈለገ? የሚዲያ ተቋምን መቆጣጠር፣ የዜና አደረጃጀትና አዘጋገብን ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንዲሁም የሚዲያ ተቋሙን በልሂቃን ትንታኔ የሚዘውሩ ባለሙያዎችን በየቦታው መፍጠር ለምንስ አስፈለገ? የዜና አደረጃጀትና አዘጋገብ ለምንስ በሶስተኛ ወገኖች ፍላጎት ይቀረፃል? የሚዲያ ተቋም በመርህ ደረጃ ለጋዜጠኝነት መርህ ወገንተኛ መሆን ሲገባው ለምንስ ለሶስተኛ ወገኖች ያድራል? ሕገመንግስታዊ ስርዓት በጎዳ ነውጥ እንዲፈርስ ለምን ሚዲያ አይነተኛ ሚና ሲጫወት ይስተዋላል? ሌሎችም ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል።
ለተነሱትና ሌሎች ለሚነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ለማቅረብ ጥልቅ ጥናት ያደረጉ ብዙ የምርመራ ተቋሞች አሉ። ከተደረጉት ጥናቶች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በአንድ ሚዲያ ተቋም ውስጥ መዋቅራዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚያስፈልገው ሚዲያ ተቋሙ በወጥነት በሚፈበርከው የመረጃ ፍሰት ሕብረተሰብ ውስጥ የሚፈለገውን አስተሳሰብ ለማስረፅ እና ሃሳቡም ቅቡልነት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው። ወይም በግርድፉ ናዖም ቾሞይስኪ እንደሚለው “MANUFACTURING CONSENT” ለመፍጠር ነው።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው፣ የምዕራቡ ዓለም እና ሩሲያ ፌዴሬሽን በዩክሬን ውስጣዊ ፖለቲካ የያዙት አቋም እና የዓለም ዓቀፉ አውራ የመገናኛ ብዙሃን የዘገባ አፈበራረክን መመልከት ተገቢ ነው። ሩሲያ ከምታነሳው የብሔራዊ ጥቅም አንፃር የተፈጠረውን ሁኔታ ብንመለከተው የዘገባዎችን ውስጣዊ የታሸ እምቅ ይዘት ለመረዳት ቀላል ያደርገዋል። ከዴሞክራሲያዊ መርህ አንፃር ስንመለከተው የምዕራቡ ዓለም የሚከተለውን የመንታ መንገድ ፖለቲካ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ለምሳሌ የግብፅ መንግስት በሱዳን ወይም በኤርትራ መንግስታት ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ የስርዓት ለውጥ በመዘርጋት ለግብፅ ብሔራዊ ጥቅም ያደረ የአሻንጉሊት መንግስት በእነዚህ ሁለት ሀገሮች ውስጥ ቢመሰርት የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ አቋም ምን ሊሆን ይችላል? የሚመሰረቱት የአሻንጉሊት መንግስታት ዋና ስራቸው ሊሆን የሚችለው፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ ነው። ይህን ተልዕኮ እንዲፈጽሙ የግብፅ መንግስት የመጀመሪያው ስራ የሚሆነው፣ በሕገወጥ መንገድ የተመሰረቱትን መንግስታትን ሕጋዊ ሽፋን በማልበስ የሕዝብ ውክልና ያላቸው መንግስት ማድረግ ነው። ይህም ሲባል በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በሁለቱ ሀገሮች የተደረገውን የስርዓት ለውጥ የሀገሮቹ የዴሞክራሲ ሂደት የመጀመሪያው መጨረሻው መሆኑን በስፋት ማዘገብና ቅቡልነት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው።
በተነፃፃሪነት ለመመልከት የምዕራቡ ዓለም በተለይ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ በፊት ኢራንን ለማንበርከክ የመጀመሪያ ስራቸው የነበረው በሶሪያ ውስጥ የስርዓት ለውጥ ማምጣት ነበር። ይህን ፍላጎታቸውን በፈለጉት መልኩ ማስኬድ ባይችሉም አብዛኛውን የሶሪያ ክፍለ ግዛት መሰረተ ልማቶች ወደ ነበር ቀይረውታል። ሁለተኛ እቅዳቸው ሊባኖስን በማፈራረስ የሶሪያና የኢራን አጋር የሆነውን ሂዝቦላን ማዳከም ከተቻለ በማያባራ የነውጥ መረብ ውስጥ መጨመር ነው። ይህን ሁለተኛው እቅዳቸውን በአጥፍቶ ጠፊዎች በኩል በተገቢው መልኩ እየተገበሩት ይገኛሉ። ይህን መሰል ኢ-ዴሞክራሲዊ አማራጮች የሚጠቀሙት የዓለም ዓቀፍን ኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ፍላጎት ለማስፈጸም መሆኑ ቢታወቅም፣ ዓለምን በተቆጣጠሩበት የኮርፖሬት ሚዲያ አማካኝነት የሶሪያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ መንግስት ምስረታ የሚያደርገው ዴምክራሲያዊ ትግል ተደርጎ በስፋት ተዘግቧል፤ እየተዘገበም ይገኛል። በዚህም ሳያበቁ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የአልቃይዳ ክንፍ በሆነው የሽብር ቡድን አማካኝነት የሶሪያ ሕፃናት በኬሚካል ጦር መሳሪያ እንዲረግፉ እና የበሽር አል አሳድ መንግስት አለም አቀፍ ውግዘት እንዲደርስበት ተጠቅመውበታል።
የሶሪያ የስርዓት ለውጥ ውጥናቸው መቋጫ ሳያገኝ ባሳለፍነው ሳምንታት ውስጥ ደግሞ በዩክሬኗ ኬቨ ከተማ በኩል ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን የሚያደርሳቸውን መንገድ ጀምረዋል። ይህን መንገድ ልዩ የሚያደርገው እንደሌሎቹ በእጅ አዙር (proxy war) የሚደረግ ጦርነት ሳይሆን ከሩሲያ ፌዴሬሽን ቀጥተኛ የጦርነት አደጋ የተጋረጠበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው። ከዚህ የጦርነት ፍጥጫ በላይ የምዕራቡ ዓለም የመንታ መንገድ አካሄድ ግምት ውስጥ የጣለው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የዩክሬን መንግስትን በጎዳና ነውጠኞች በአደባባይ ሲፈርስ እያዩ አለማውገዛቸው እንዲሁም ይህን የነውጥ ቡድን ሕጋዊ መንግስት መሆኑን በይፋ ማወጃቸውና ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት መፍጠራቸው ነበር።
እንደውም አንዳንድ ፀሃፍት ይህን የምዕራቡ ዓለም ያሰናዳው የጎዳ ነውጥ አብዮትን “ኒዮ የብርቱካን አብዮት” እያሉ ይጠሩታል። ይህም ሲባል፣ በሕገ መንግስታዊ ስርዓት ስልጣን የያዘ መንግስትን በጎዳና ነውጥ በማፍረስ የሕዝብን ስልጣን በተወሰኑ ቡድኖች ውክልና መቆጣጠር ነው። በተለይ የምዕራቡ ዓለም “ዕሴቶች” ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል ሕገ መንግስታዊ ስርዓት፣ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት በኬቭ አደባባይ ብትንትናቸው እንዲወጣ ዋነኛ ተዋናዮቹ ምዕራቦቹ ሆነው መቅረባቸው ቀጣዩን የዩክሬን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ አድርጎታል።
ከዚህ የምዕራቡ ዓለም የመንታ መንገድ የፖለቲካ እርምጃ መረዳት የሚቻለው የኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ሃይሎች ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ የሚሄዱበት ርቀት አደገኛነትን ነው። በተለይ ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ያላቸውን፣ ጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑ ቦታዎችን እንዲሁም ዲያመንድ ዩራኒየም የመሳሰሉ የሃይል ሚዛን የሚያዛቡ የተፈጥሮ ማዕድናት በሚገኙበት ቦታዎች ላይ በማንኛውም ዋጋ ክፍያ ለመቆጣጠር እንደሚሰሩ ነው።
ለምሳሌ ኢትዮጵያን እንውሰድ፤ በኦሞ፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ እንዲሁም በወሎ አካባቢ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ቢገኝ አሁን በእጃችን ላይ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ ይቻለን ይሆን? የብሔር ብሔረሰቦች መብት ከእውቅና በላይ በኢኮኖሚ የተሳሰረ እንዲሆን ስራዎች እየተሰሩ ባለበት ሁኔታ የኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ሃይሎች በር ቢያንኳኩ እንዴት ፍላጎታቸውን ማስታረቅ ይቻላል? በተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የፖለቲካ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ የይዘት ማዕቀፍ ውስጥ ባልተቀመጡበት ሁኔታ የኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ፍላጎትን በቀላሉ ማስተናገድ ይቻላል ይሆን? በተለያዩ ፍላጎቶች የታጨቀው የሚዲያው ምህዳርስ የኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም መጠቀሚያ እንዳይሆን ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች ምንድን ናቸው?
      ከላይ የተቀመጡት ነጥቦችን ማንሳት ያስፈለገው በዩክሬን ግዛት ውስጥ የሚደረጉ የስርዓት ለውጦች ፍጥጫ ከዩክሬን ሕዝብ ፍላጎት በላይ የምዕራቡና የሩሲያ ፌደሬሽን የጥቅም ግጭት መሆኑን ለሚገነዘብ አካል የቤት ስራውን ቀድሞ ነው መስራት ያለበት። ተራራ ሲቃጠል መሬት ይስቃል እንደሚባለው፤ ከእያንዳንዱ ዓለም ዓቀፋዊ ክስተቶች ውስጥ የነገዋን ኢትዮጵያ እያሰቡ መሄድ ካልተቻለ የኮርፖሬት ኢምፔሪያሊዝም ፍላጎትን መቼና እንዴት እንደሚመጣ ለመገመት አስቸጋሪ ነው።
ንደቅ የተወሰደ

No comments: