Saturday, December 14, 2013

ፍትሕ የሚያስፈልጋቸው የሕገወጥ ስደት ሰለባዎች

December 14/2013

በአሁኑ ጊዜ ሳዑዲ ዓረቢያ በስደት የነበሩ ከ 100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን አገራቸው ለመግባት በቅተዋል . አሁንም በርካታ ወገኖች የመሄጃ ጊዜያቸውን በማጎሪያ ጣቢያዎች ወይም በቤታቸው ሆነው እየተጠባበቁ ነው ::

ሰሞኑንም የሳዑዲ መንግሥት ኢትዮጵያዊያኑን << ለጊዜው ማቆያ ቦታዎቻችን ከመጠን በላይ ስለተጨናነቁና ሁላችሁንም ልናስተናግድ ስለማንችል በየቤታችሁ ሆናችሁ ድጋሚ ጥሪ እስክናደርግ ተጠባበቁ ; >> የሚል መልዕክት << ወደ አገራችን አሳፍሩን >> ለሚሉት ኢትዮጵያዊያን እያስተላለፈ ነው . በዜና ዘገባዎች ላይ የተጠቀሰው ቁጥር እነዚህን በቤታቸው ሆነው የሚጠባበቁትንም ያጠቃልል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አልቻልንም ::

ይሁንና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ , የተጠቀሰው ቁጥር አሁንም ገና የሚቀረው ማረጋገጥ ይቻላል . በቅርቡ በጅዳ አካባቢ ማረፊያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊን ቁጥር በጥቂቱ ከ 20,000 በላይ እንደሆነ ተገምቷል . ከሃምሳ በሚበልጡ የተለያዩ ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰበሰበው ሕዝብ ደግሞ ቢያንስ 20,000 ይሆናል . በየቤቱ የሳዑዲ መንግሥትን ዳግም ጥሪ የሚጠባበቀው በሪያድ , በጅዳ , በመካ , በደማምና በሌሎች ከተሞች የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለመቁጠር እጅግ የሚያስቸግር ነው ::

ከላይ የዘረዘርኩት እንግዲህ ይተልቅም ይነስም በከተሞች አካባቢ የሚኖረው መሆኑ ነው . በሌላው በኩል ደግሞ በየበረሃው በበግ , በፍየልና በግመል ጥበቃ ወይም በሌሎች ሥራዎች የተሰማራውና ለመገናኛ ብዙኃን ቅርበት የሌለው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም . ሁሉም ለማለት ይቻላል ; የየመንን ድንበሮች በመከራና በስቃይ ሕይወታቸውን , አካላቸውን , ሴትነታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸውን እየገበሩ , ካንዱ ቦታ የሚቀጥለው ቦታ የሚያደርሳቸውን የኮንትሮባንድ ትራንስፖርት ገንዘብ እስኪያሟሉ ይቆዩና ወደ ሚቀጥለው መዳረሻቸው ጉዞ የሚጀምሩ እንዳሉ በደንብ ይታወቃል . በሳዑዲ እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከየመን ከምትዋሰነው የሳዑዲ ድንበር ከተማ ጀዛን አንስቶ በቀጥታ ሪያድ ወይንም ጅዳ ለመግባት ቢያንስ 1000 የአሜሪካ ዶላር ስለሚፈጅ , በድንብር ከተሞች ያለው ፍተሻም ከረር ያለ በመሆኑ ማንም ስደተኛ በድንበር ከተሞች መቆየት አይፈልግም .

በዋና ዋና ከተሞች የሚኖር ሌላ አጋዥ ኢትዮጵያዊ ወገን ከሌለው ሁሉም አቆራርጦ መድረስ ነው የሚፈልገው . ይህም ከድንበር ከተማዋ ጀዛን ወደ ዋና ከተሞች ለመድረስ የሚፈጀውን ገንዘብ ለማሟላት ጉዞውን እያቆራረጡ ማድረግ የግድ ይላል . ለምሳሌ ከጀዛን ሪያድ ርቀቱ ወደ 1800 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው . ስለዚህ በዋና ከተሞች ወጪውን የሚሸፍንለት ወገን የሌለው ስደተኛ ይህንን 1800 ኪሎ ሜትር ለመሸፈን ቢያንስ ቢያንስ ከስምንት ወር እስከ አንድ ዓመት ይፈጅበታል . አንድ ቦታ አንድ ወር ይሠራና ባገኘው ገንዘብ የተወሰኑ መቶ ኪሎ ሜትሮችን ይቀንስና ገንዘቡ ባደረሰው ቦታ ሌላ የእረኝነት ሥራ ይጀምራል . ከዚያም እንደመጀመሪያው እያደረገና እያቆራረጠ ዋና ከተሞች ይደርሳል ::

ስደተኞች ዋና ከተሞችን የሚመርጡበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ; አነስተኛ ፍተሻና በርከት ያለ አቅርቦት ስላለ ነው . ለምሳሌ በጀዛን አካባቢ መንደሮች ለአንድ የጉልበት ሠራተኛ እረኛ የሚከፈለው ገንዘብ ከ 100 ዶላር በታች ሲሆን , በሪያድ አካባቢ ደግሞ ላንድ ሙያ ለሌለው የጉልበት ሠራተኛ የሚከፈለው 500 ዶላር ይደርሳል . ታዲያ ጉዞውን ከጀዛን ከዓመት ወይም ከስድስት ወር በፊት የጀመረው ስደተኛ አሁንም መንገድ ላይ ነው ማለት ነው . እንዲያውም ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ባብዛኛው ለሥርዓት አልበኞች ​​ጥቃት አብልጦ ሲጋለጥ የነበረው ስደተኛ እንዲህ ዓይነቱ ነበር . ካለፈው ዓመት አንስቶ በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲሰነዘር የተስተዋለውና በየማኀበራዊ ድረ ገጾች ሲለቀቅ የነበረው ፎቶና ቪዲዮም ላይ የተመለከትናቸው ኢትዮጵያዊያን የመከራ ገፈት ቀማሾች እኚሁ መንገደኞች ናቸው ::

ምንም እንኳን በመንግሥታችን በኩል እየተደረገ ያለው ወገኖችን ወደ አገራቸው የማስገባት ጥረት የሚበረታታና የሚያስደስት ቢሆንም , ተደራሽነቱ አሁንም ለኔ እጅግ በጣም አጠያያቂ ነው . እንደ አገር ያሉትን ወገኖች በተቻለ መጠን ጠቅልለን እስካላወጣን ድረስ መሞታቸውን እንኳን የማናውቃቸው ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ የሚያውቀው አገር ቤት ያለው ቤተሰባቸው ብቻ ነው የሚሆነው ::

ለመሆኑ ይኼን ያህል ኢትዮጵያዊ ወገን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጣ ለምን ተመልካች አልነበረም ? በአፋር በረሃዎች ለግመል እረኞች የዒላማ መለማመጃ ሆኖ ሕይወቱ ያለፈውን , በጂቡቲ በረሃዎችና የባህር ዳርቻዎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ቱጃሮች ወንድና ሴት ሳይለይ ጾታዊና ​​አካላዊ ጉዳት እየደረሰባቸው , የሚላስና የሚቀመስ እያጡ በረሃ ወድቀው የቀሩት , በሶማሊላንድ በረሃዎች እስከ ቦሳሶ ወደብ ድረስ እየተደበደቡ , እየተዘረፉ , እየተደፈሩና ክብራቸው እየተዋረደ ሕይወታቸው ያለፈው , ቀይ ባህር ሰጥመው ለአሳነባሪ እራት የሆነው , ዕድል ቀንቶአቸው የመን ደርሰው በየመን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከባህር ጀምሮ እንደ ሽቀጥ ካንዱ አዘዋዋሪ ወደሚቀጥለው አዘዋዋሪ ሲቸበቸቡ , በሳዑዲ ከተሞች የሚኖር አንድ ወገን በችግር ሠርቶ ያጠራቀመውን ገንዘብ ከፍሎ አለዚያም አገር ቤት የሚኖር ቤተሰብ መሬቱን ሸጦ ወይንም አከራይቶ በሚልከው ገንዘብ ነፍሱ ያልተዋጀችለትና በሚነድ ፌስታል ተለብልቦ , በሚስማር ተቸነካክሮ , በስለት ተተልትሎ , በብረት በትር እንደ እባብ ተቀጥቅጦ , በፕላስቲክ ገመድ ደሙ እስኪቆም ድረስ ብልቱና የዘር ፍሬውን ታስሮ እየተንጠለጠለና እጆቹን የፊጥኝ ተጠፍሮ , በጥይት አረር አሮ , ያውም በገዛ ወገኖቹ ኢትዮጵያዊያን ከየመን በረሃዎች እስከ መንፊሃና ነሲም በተዘረጋው የደም ንግድ ደሙ ደመ ከልብ የሆነበትን ኢትዮጵያዊ ከቶ ማን ሊቆጥረው ይችላል ? በጀማ እየተደፈሩ ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያዊያት እህቶችንስ ማን ይቆጥራቸዋል ?

መቼም አንዱን ካንዱ ማበላለጥ ቢያስቸግርም እንደ ከብት ኢትዮጵያዊያን የተቸበቸቡባቸውና የታረዱባቸው የስደተኛ ንግድ ሸሪኮች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ማወቅ ደግሞ ሐዘኑን የከፋ ያደርገዋል . ከየመን በረሃዎች አንስቶ በሳዑዲ ዋና ዋና ከተሞች ድረስ የተዘረጋው የግፍ ንግድ ምንም እንኳን በየመናውያኑና በሳዑዲያውያኑ ቢመራም በየመን በረሃዎች ውስጥ የነበሩት ገራፊዎችና በየከተሞቹ የሚገኙት ገንዘብ አቀባባዮች ግን በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ ::

ምን ይኼ ብቻ ? በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎችስ እነኚህን ተስፈኞች እየደለሉና እያባበሉ ወደ ሞት የነዷቸውስ እነማን ነበሩ ? << የሌላ አገር ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በየመንደሩ ገብቶ ዜጎችን ለስደት መለመለ >> ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም . በዚህ የምልመላ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ደግሞ የግድ ባይሆንም የተመልማዩ ወገን አካባቢ ነዋሪ መሆን ያስፈልጋል . ከዚያ ባሻገር ደግሞ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ለዘመናት ተለጥፈው ስናነባቸው የከረምናቸው << ወደ ዓረብ አገር በነፃ እንልካለን >> የሚሉት ማስታወቂያዎች እማኞች ናቸው ::

በዚህ ጹሑፌ ትኩረት ላደርግበት የፈለግኩት እነዚህን የዚህን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነፍስ የበሉትንና ለዚሁ ሁሉ መከራ የዳረጉትን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው . እንዲያውም ከወር በፊት አዲስ አበባ ሄጄ የታዘብኩት ነገር ቢኖር , አንዳንድ ኤጀንሲዎች ቢሯቸውን ወደ ካርቱም ማዛወራቸውን ነው . ዜጎችን በመመርያ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ዓረብ አገር ኤክስፖርት ለማድረግ !
አይግረማችሁና በሳዑዲ የዚህ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈውንና ስንቶችን የአካል ጉዳተኛና የአዕምሮ በሽተኛ ያደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ገንዘብ አስተላላፊዎች , ሱቆቻቸውን እየዘጉና ሚኒባሶቻቸውን እያቆሙ ከነዚሁ መከረኞች ጋር ወደ አዲስ አበባ እየተሳፈሩና የመሳፈሪያ ጊዜያቸውን እየጠበቁ ነው . በየመንም ያሉት ኢትዮጵያዊያኑን ሲያሰቃዩ የነበሩት ኢትዮጵያዊያንም እንዲሁ . አገር ቤት ያሉት ደላሎችና ኤጀንሲዎች ባለ በርካታ ፎቆችና መኪኖች ባለቤት መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው ::

ታዲያ እነዚህን ሁሉ ወንጀለኞች እያወቅናቸውና በመካከላችን አቅፈናቸው እየኖርን , ወገንን ለባርነትና እንደ መኪና መለዋለጫ አካላቸውን እየተተለተሉ በመቸብቸብ ንግድ ሀብትና ንብረት ያለማንም ከልካይ አፍርተው በእነዚህ ተበዳዮች አገር ሲንፈላሰሱ እያስተዋልን << ይኼ ነገር ገነ አይቀጥልም >> ብለን የምናስብ ከሆነ መቼም ምን እንደምንባል አላውቅም . እስኪ ለመሆኑ የትኛው ደላላ ወይም ኤጀንሲ ነው ለኮፍ ለኮፍ ሳይሆን ለተከሰተው የሕይወት መጥፋት , ያአካል መጉደልና ያአዕምሮ መታወክ ተመጣጣኝ ቅጣት የተቀጣና ተመጣጣኝ ካሳ የካሰ ?

ተበዳዮች ደማቸውንና የሚያስመልስላቸውና በደላቸውን የበላይ አካል በጠፋ ጊዜ ራሳቸው በራሳቸው ፍትሕ ማግኘታቸውን ትናንት ወይም ዛሬ የተጀመረ ሀቅ አይደለም . ለዘመናት የኖረና አሁንም የሚኖር ነው . ዘመናችን በከሰተው በዚህ የባሪያ ፍንገላና የሰው ልጅን ለዕርድ የማቅረብ አሰቃቂ ወንጀል በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸውና በዚሁ ኢሰብዓዊ ወንጀል እጃቸውን በንፁኃን ደም ያጠቡ ደላሎች , የሕክምና ተቋማት , ኤጀንሲዎች , በየመን የነበሩ አሰቃዮችና በሳዑዲ የነበሩና የሚገኙ ገንዘብ አስተላላፊ ግለሰቦች ከያሉበት ታድነው የሚገባቸውን ፍርድ እስካላገኙና ወደፊትም በዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ የደም ንግድ ለመግባት ላሰቡ ሰዎች መቀጣጫ የሚሆንና በቂ ቅጣት ካልተቀጡ በቀር , አሁን ያየነው ዓይነት አሰቃቂ ክስተት ላለመከሰቱ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም . እዚህ ላይ በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊቷን ልጅ እስርበው ለሞት አብቅተዋታል በሚል ወንጀል የተከሰሱት አሜሪካውያን ባልና ሚስት , ሦስት ሴቶችን ለዓመታት እቤቱ አግቶ የወሲብ ጥቃት ሲፈጽም ነበረ የተባለው አሜሪካዊ ላይ የተበየኑትን ብይኖች ስናስታውስ << መቼ ይሆን በኛስ አገር ተበዳይ ፍትሕ የሚያገኘው ? >> ብዬ እንድጠይቅ ብቻ እገደዳለሁ .

 ጸሐፊው ነዋሪነታቸው በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከተማ ነው . ( ምንሊክ ሳልሳዊ )

No comments: