Tuesday, December 24, 2013

በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ አባላት በእስር ቤት ስቃይ እንደተፈጸመባቸው ገለጹ

December 23/2013

በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስነልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ አድርሰውብናል የሚሉት በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ የደረሱባቸውን በደሎች ዘርዝርው አቅርበዋል።  ” ከአስራ አራት ሰአት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን ሰንበር እስኪያወጣ እና እስኪገሸለጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና አይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ፣ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና ድብደባ እንቅልፍ በመንሳት፣ ሃይማኖታችንንና ክብራችንን በመንካት፣ ጺማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ እንዲሁም ሶላት በመከልከል፣ ቤተሰብ፣ ጠበቃ ፣ሀኪምና ሀይማኖት አባት እንዳናገኝ በማድረግ፣ ከአቅም በላይ የሆነን ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ ” ልጅህን እንገለዋለን! ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ ሀይላንድ በማንጠልጠል ማሀን እናደርግሀለን” ሲሉ በማስፈራራት ከፍተኛ ስቃይ አድርሰውብናል ብለዋል።

በህገመንግስቱ አንቀጽ 18 ንኡስ አንቀጽ 1 ” ማንኛውም ጭካሄ ከተሞላበት፣ ኢሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” ቢልም፣ እኛ ግን ” ዜጎች መሆናችንን ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት መልኩ ከያዙን በሁዋላ በማእከላዊ በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳን ቅዝቃዜው በማይቻለው ” ሳይቤሪያ” ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል ለ3 ዋር አገሩው መቋቋም የሚአዳግተውን የማሰቃያ ስልታቸውን በመጠቀም አላሰብነውንና ያልሰራነውን ” እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ! ብለው አስገድደውናል”  ሲሉ በመግለጫቸው ጠቀስዋል።

ፍርድ ቤት ስቃዩን እንዲያስቆምልን ብንጠይቅም፣ ያገኘነው ውጤት ግን ወደ ማእከላዊ ስንመለስ ከመርማሪዎቹ በቀልና ተጨማሪ ስቃይ ነበር፣ የሚሉት ኮሚቴዎቹ፣ አሰቃዮቻችን ስለህገመንግስቱ እና መብት ስንናገር ” ህገ-መንግስቱን ቀደህ ጣለው፣ እኛ መስዋትንት ከፍለን ነው እዚህ የመታነው በማለት ለህግም ሆነ ለሰው ክብር ዴንታ እንደሌላቸው አሳይተውናል” ሲሉ አክለዋል።
ከቤተሰብ፣ ከጠበቃና ከሀኪም ጋር እንዳንገናኝ አድረገው የፈጸሙብን የህግ ጥሰት እና አስገድደው በማስፈረም እና ድምጽና ምስላችንን በመቅረጽ የፈጸሙብን በደል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 424 መሰረት እስከ አስር አመት የ አስቀጣ ኢ-ሰብአዊ ተግባር ቢሆንም የፖሊሱም፣ አቃቢህጉም ፣ የፍርድ ቤቱም አለቃ በሆነውና የፍትህ ስርአቱን ሰብስቦ በያዘው ገዢው ፓርቲ አምባገነንነት በተቃራኒው እኛ ተከሳሽ ሆነን ጉዳያችን በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት በአግባቡ ሊተውነው ያልቻለውን አሳፋሪ የፍርድ ቤት ድራማውን ህዝብ እንዳያይበት ለመሸሸግ በመገደዱ የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በሁዋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመስማት መብት አላቸው የሚለውን ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ ችሎቱ ዝግ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል የሚሉት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣  በዝግ ችሎቱ የምስክር መስሚያ ጊዜ ብዙ አስገራሚ ድራማዎችን አይተናል፣ አቃቢ ህግ ዳኞች የሚሰጡትን ብይን እንደማይቀበሉ እስከመግለጽ የደረሱበትን እና ምስክሮችን ማለት ያለባቸውን አሰልጥነዋቸው እንደሚያመጡ አምልጧቸው የተናገሩበትን አጋጣሚ ” መታዘባቸውን ይገልጻሉ።

የኮሚቲው አባላት ” በሙስሊሞች መካከል እና በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል የታየውን አንድነትና መከባበር በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።  በጽናት ሰላማዊ የመብት ትግሉን የሚቀጥሉ መሆናቸውንና የሚያስከፍለውን መስዋትንት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ለቀጣዩ ሰላማዊ የመብት ትግል እርከንም  በሙሉ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን” ገልጸው፣ መንግስት በማእከላዊ እስር ቤቶች የሚፈጸሙትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዲያስቆምና የህሊና እስረኞችን እንዲለቅ ጠይቀዋል።

ኢሳት ዜና

No comments: