Thursday, December 12, 2013

በጅዳ ቆንስል በር ውላ የምታድረው እህት ክራሞት …(ነቢዩ ሲራክ)

December 11/2013

ይህችን እህት በጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት በር ተቀምጣ ካየኋት ሳምንት አልፏል። አልፎ አልፎ ላነጋግራት ብሞክርም መልስ አትሰጥም። መጀመሪያ የየኋት ቀን አካባቢ ከስራ ለተፈናቀሉ እህቶች አነሰም በዛ መጠለያ እያለ ፣ ለምን በር ላይ ትሆናለች? ብየ የጠየቅኳቸው የቆንስሉ ጸጥታ አስከባሪ " አንተየ የዚህች እህት ጉዳይ አስቸጋሪ ነው ። ከመጠለያው ብዙ ቆይታለች ፣ አሁን በር  ላይ የሆነችው ሃገር ቤት ለመሄድ ወረቀቷ አልቆ እያለ " ሃገር ቤት አልሄድም!" በማለቷ እነረደሆነ ተነግሮኛል ። " በመጠለያው የነበሩት ሰነዳቸው ባሳር በመከራ አልቆ ሲሸኙ ወደ ሃገር ቤት አልሸኝም ብላ ረብሻ ከማንሳት አልፎ ከተዘጋጀው መኪና ወርዳ ይህን የምታየው ሚኒባስ መስታውት ሰብራዋለች!  ከዚያን ቀን ወዲህ አትበላም አትጠጣም ፣ እኛንም የገረመን ይሄ ነው!  ሚን ታደርጋለህ! " ነበር ያሉኝ ... 
       ይህ ከተነገረኝም "ወዲህ ሃገር ቤት አልገባም!" ያለችው እህት ለቀናት  በቆንስሉ በር አልጠፋችም። ከተቀመጠችበት ወንበር ጀርባ ባለው ግድግዳ " ህጋዊ ሰነድ የሌላችሁ እና የወጣውን የሳውዲ ህግ መስፈርት የማታሟሉ ወደ ሃገር ግቡ !" የሚለው የቆንስል ማስታወቂያ ይታያል ። ከአጠገቧ በፕላስቲክ ኪስ የታጨቀ ጓዟን አስቀምጣ ፣  በሆዷ ቁርአን ታቅፋ አንገቷን ከመድፋት ባለፈ በአካባቢው አዛን ስትሰማ የዘወትር ጸሎቷን (ሰላቷን) ወንበሯን ፈቀቅ አድርጋ እንደምትሰግድ አንድ ዘወትር እንቅስቃሴዋን የሚከታተል ወዳጀ አጫውቶኛል... እንዲህ ሆና ኮርመት ብላ ውላ ታድራለች! ቀን ጸሃይ ሲወቃት ፣ ማታ ወበቁ ይፈራረቅባታል ! ካየኋት ቀን ጀምሮ ወደ መጠለያው እንድትገባ ብዙ ሁነን ብንማጸናትም አልተሳካልንም ...
       ከሃገሯ በጤና የመጣችው እህት ችግር ውጋቷን እንድንጋራ ስንጠይቃት አትመልስም  !  ወደ ሃገር ቤት እንድትገባ በጅዳ ቆንስል ልትሸኝ ቢሞከርም አልተሳካም። የ"ሃገር ቤት ግቢ!" " አልገባም!" አለ መግባባት  ፍርሻ ከመምጣቱ በፊት አንዳንዴ ኦሮምኛና ብዙ ጊዜ ግን የተሰባበረ  አረብኛ እየቀላቀለች መናገር ይቀናት እንደነበር አንድ " በመጠለያው እያለች አውቃታለሁ!" ያሉ ወንድም አጫውተውኛል። ያን ሰሞን ወደ መጠለያው እንድትገባ ተለምና ብትገባም በመጠለያው ውስጥ ካሉ ግፉአን ጋር ግብ ግብ ፈጥራ መውጣቷን ሰምቻለሁ  !
     ይዚህች ግፉዕ እህት ሰላም የነሳና አዕሮዋን ያወከ የውስጥ ህመም ሚስጥር አይታወቅም! ትሰማለች ፣ ለመናገር አልፈቀደችም!  ባሳለፍናቸው የበር ላይ ውሎዋ ትንፍሽ ብላ ስትናገር ቢያን እኔ እስከ ዛሬ አልሰማኋትም ! ውስጧ እንጅ ውጭ አካሏ የተጎዳ አይመስልም! ከሁሉም የሚገርመው ይህች እህት ጤናዋ ታውኮ እንኳ ሃገር ቤት ከወገኖቿ ጋር መቀናቀል ሞት መስሏታል  ! ሌላው አስገራሚ ሂደት  የዚህችን መልከ መልካም እጣ ፈንታ የምንመለከትም ህጋዊ ሰነድ የሌለን ብዙዎች የሳውዲን መንግስት የምህረት ቀቢጸ-ተስፋ ሰንቀን ጤናችን ተጠብቆ እያለ" በሰላም ሃገር ቤት ግቡ !" የሚለውን የመንግስትና የወገን ምክር መቀበል አቅቶናል !  እንዴት ነው ነገሩ ...?
አንድየ ይታረቀን ከማለት ባሻገር ምን ይባላል :) ብቻ እሱ ያቅልለው እንጅ የሚሰማ የሚታየው ይከብዳል ! ... ያማል ... ያማል  !
ነቢዩ ሲራክ 

No comments: