Friday, December 6, 2013

ከሳውድ አረቢያ ከሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የመንግስት እንቅስቃሴ እየተተቸ ነው

December 5/2013
ህዳር (ሃያ ስድስ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የላችሁም በሚል ከሳዑዲዓረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ቁጥሩ መንግስት አስቀድሞ ካሰበው እጅግ አሻቅቧል፡፡ በዚህ ም ምክንያት ተመላሾቹን ለመቀበልና ለማቋቋም  መንግስት በቂ በጀት አለመያዙ እንደ አገር አሳፋሪ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
መንግስት የተመላሾቹ ቁጥር 23 ሺ ገደማ መሆኑንና እነዚህም ወገኖች ለመመለስ መመዝገባቸውን በመግለጽ ለተመላሾቹ 50 ሚሊየን ብር እንደመበ መግለጹ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ የተመላሾቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ከታወቀ በሁዋላ እንደገና መረጃውን በማሻሻል ተመላሾቹ ከ50 እስከ 80 ሺ እንደሚገመቱ ይፋ አደርጎአል፡፡ ይሁን እንጅ እስትናንት ድረስ ከ100 ሺ በላይ ሰዎች መመለሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ከነዚህ መካከል 8 ሺህ የሚሆኑት ነፍሰ ጡር መሆናቸው ተገልጿል ፡፡
መንግስት ለተመላሾቹ 50 ሚሊየን ብር መመደቡን ከመግለጽ ውጪ መልሶ ለማቋቋም ምንም ያሰበው
ነገር አለመኖሩን የጠቀሱት ምንጮቹ  ተመላሾቹን ተቀብሎ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ማረፊያ ካቆየ በኃላ ክልሎች ስራ ይሰጡዋቹሃል በማለት እያባበለ ወደትውልድ አካባቢቸው እንዲሄዱ እያደረገ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡ተመላሾቹ  በሰው አገር መከራና ስቃይን ከማሳለፍ ባሻገር  ያፈሩትን ሐብትና ገንዘብ ይዘው መመለስ አለመቻላቸውን ያስታወሱት እነዚሁ ምንጮች በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉትንና  በተስፋ መቁረጥ የተጎዱትን ወገኖች በባዶ እጅ ወደ ቤተሰብ መስደድ እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል ፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት መሰረት መከላከያና ሌሎች መንግስታዊ መ/ቤቶች  በ2004 የበጀት አመት 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ያለበቂ ሰነድና ተጠያቂነት በባከኑበት አገር፤ በአንጻሩ ከስደት ተመላሽ ዜጎች በበቂ ሁኔታ እንኩዋን መረዳት የሚችሉበት ሁኔታ አለመመቻቸቱ፣ ጉዳያቸውም ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ብቻ መዋሉ ያስቆጫል ብለዋል᎗ የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ ያነጋገራቸው ወገኖች፡፡
መንግስት ለተመላሽ ወገኞች ህዝቡ እርዳታ እንዲደርግ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ባላሃብቶች ሰባት ሚሊየን ብር ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሁለት ሚሊየን ብሩ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የለገሰችው ነው፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ያለው የዕርዳታ ጥያቄ ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በመንግስት በኩልም ተጨማሪ በጀት መድቦ ሰዎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ፍላጎት አለመታየቱ አሳዛኝ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እየገለጹ ነው ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀመውን ግፍ በመቃወም በስዊዘርላንድ ለሁለተኛ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል።
ከሳምንት በፊት በስዊዘርላንድ-በርን በሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመውጣት ተቃውሟቸውን የገለጹት ኢትዮጵያውያን፤ በጀኔቭ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት ሰልፍ በወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ እየተፈፀመ ያለውንና ሊያባራ ያልቻለውን ግፍና ሰቆቃ አውግዘዋል።
በጀኔቭ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጽህፈት ቤት  በተደረገው ሰልፍ ኢትዮጵያውያኑ በዜጎቻቸው ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ከማሰማታቸውም ባሻገር የቪዲዮ ማስረጃዎቸን  በ አንድ ላይ አሰባስበው በማደራጀት ለጽህፈት ቤቱ እንዲደርስ አድርገዋል።
ከቀኑ 14 ሰዓት እስከ 17 ሰዓት በቆየው በዚሁ ሰልፍ ላይ ፓርቲያቸውን በውጭ ሃገራት የማስተዋወቅ ተግባር እያከናወኑ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ተሳትፈዋል።
ከአስተባባሪዎቹ -አንዱ የሆነው ወጣት አክቲቪስት ጴጥሮስ አሸናፊ ሰልፉን አስመልክቶ ከኢሳት ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ፤የወገኖቻችን ሰቆቃ እስኪያባራ ድረስ ያለድካምና መታከት ጩኸታችንን  ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ማሰማታችንን እንቀጥላለን ብሏል።
በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያውያኑን ስሜት የነካ ግጥም ያቀረበችው ወጣት ነጃት በበኩሏ-ከሁሉም በተለየ መልኩ ግፉና መከራው ኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ማየሉ እረፍት እንደነሳት ትናገራለች።
ለሰልፈኞቹ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የሰማያዊነፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ ለወገኖቻቸው ድምፃቸውን ለማሰማት ባልቻሉበት ወቅት ወደ  ወጪ አገር መጥተው  ለመሰለፍ  መብቃታቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።

No comments: