Tuesday, February 4, 2014

አራተኛው ሰው ጉድ አፈሉ!

Feb.4/2014

ጋዜጠኛ መስፍን ኣብርሃ - ጀርመን

p leayh



ኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከጀመሩ ዘንድሮ 111ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ምንሊክና በአሜሪካው አቻቸው ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ልዑካን መካከል ለዘጠኝ ቀናት ድርድር ከተካሄደ በሁዋላ ነበር ግንኙነቱ በይፋ የተጀመረው። ከአንድ ክፍለ-ዘመን በላይ ያስቆጠረው የአገራቱን ግንኙነት በመጠቀም ኢትዮጵያ ጠቀም ያለ እርዳታዎችን ተቀብላለች።በአሁኑ  ወቅትም በየዓመቱ ከ500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የልማትና የወታደራዊ እርዳታ ተጠቃሚ ናት። አሜሪካም ብትሆን ፖለቲካዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከአገራችን ታገኛለች።ሆኖም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አሜሪካ በኢትዮጵያ ባሉ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዙሪያ ቅር መሰኘቷን ደጋግማ ስትገልፅ ቆይታለች። በየዓመቱ በአሜሪካ መንግስት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚወጣው የአገራት የሰብዓዊ መብት ሪፖርትም ኢትዮጵያ ባላት ሪከርድ በአሜሪካ ክፉኛ ስትተች ነበር።
ይህን ተከትሎም ይመስላል የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት/ኮንግረንስ ጥር 7/2006 ዓ.ም ባወጣው ዓመታዊ የበጀት ድልድል ቀመር ለኢትዮጵያ በሚሰጠው የልማትና ወታደራዊ ድጋፍ ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን ያዘለ አንቀጽ ያካተተ ሕግ አፅድቋል።
ሕጉ የአገሪቱን ዓመታዊ የ2014 በጀት አሜሪካ እርዳታ የምትሰጣቸውን አገሮች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የገንዘብ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የመሳሰሉትን በጀት ያካተተ ነው። በዚህ ዳጎስ ያለ ሕግ ላይ በአንቀጽ 70ሺ42 ገፅ 1ሺ294 ላይ የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ወታደራዊና የልማት እርዳታዎች የሚመለከት ሆኖ እናገኘዋለን።
ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከምክትሉ ጆ ባይደን ከአሜሪካ የህግ አውጪ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጆን ቤይነር ቀጥሎ የሴኔቱ ፕሬዚዳንት በስልጣን ተዋረዳቸው ደግሞ አራተኛው ሰው በመባል የሚታወቁት ከፍተኛ ሴናተርና ዴሞክራቱ ፓትሪክ ሌሂ አማካኝነት አንቀፁ እንዲካተት መደረጉ የሚገለፀው ይኸው ህግ እንደ ኦክላንድ ኢንስቲትዩት የማህበረሰብ ተቋም የፖሊሲ ዳይሬክተር ፍሬድሪክ ሙሶ ታሪካዊ ህግ ተብሎ እየተወደሰ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስትን አስተዳደር የሚቃወሙትና ኤችአር 2003 በመባል የሚታወቀውን ህግ ያረቀቁት እንደራሴዎች ዶናልድ ፔይንና ክሪስ ስሚዝ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት እውቀት ሳይኖራቸው በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት አግባቢዎች/ሎቢስት እንዲሁም በአምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመራው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ህግ አነፍናፊ አታሼዎች እውቅና በላይ ሳይታሰብ በድንገት ህግ ሆኖ የወጣው ይኸው አንቀጽ የሁለቱን አገራት መንግስታት ግንኙነት ሊፈታተነው እንደሚችልም ከወዲሁ ተገምቷል።
የህጉ አንቀጽ እንደሚያስገድደው የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ በትክክል ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይና የገንዘብ ሚኒስትሮቹ ማረጋገጥ አለባቸው። በጀቱ በስራ ላይ ከመዋሉም በተጨማሪ በጀቱን በቀጣይ ለመልቀቅ፤
  1. ገለልተኛ ዳኝነት መኖሩን ማረጋገጥ ወይም ወደ ገለልተኛ ዳኝነት ለማምራት ጥረት እንደሚደረግ ውጤታማ እቅዶች በስራ ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ
  2. የኢትዮጵያ መንግስት የመናገር ራስን የመግለፅ መብት መጠበቁን ሰላማዊ ስብሰባዎች ማካሄድን በእምነት ተቋማት ላይ ተፅዕኖ ያለማ ድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲሰሩ ዜጎች ከህግ ውጭ የማይታሰሩና ማዋከብ የሌለ መሆኑን ማረጋገጥ
  3. የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመጎብኘት ዕድል እንዳይነፈጉ፤ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፈፀሙ የፖሊስና የመከላከያ ሃይሎች ላይ ክስ እንዲመሰረት
  4. በኦሞ ሸለቆና በጋምቤላ ክልል አካባቢዎች በሰፈራ ስም ዜጎች ከመሬታቸው እንዳይፈናቀሉና እንዳይሰደዱ ማረጋገጥ
  5. ከአሜሪካ ህዝብ ቀረጥ ከፋዮች ተሰብስቦ ለኢትዮጵያ እርዳታ የሚውለው ገንዘብ የዜጎቹን ህይወት የሚያሻሽል እንጂ ድህነቱን የሚያባብስ እንዳይሆን ሁለቱም ሚኒስትሮች አረጋግጠው ለበጀት ኮሚቴው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው የህጉ አንቀጽ ያስገድዳል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓቱ መሻሻልና የመልካም አስተዳደር መስፈንን በቅድመ ሁኔታነት የሚያስቀምጥ ህግ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ቀደም በሚሰጡ እርዳታዎች ላይ እርዳታውን ከመስጠት የዘለለ የቁጥጥር ነገር ስለማይደረግ ከፍተኛ ንብረትና ሃብት ተመዝብሯል የሚል ክስ የሚደመጥበት የኢትዮጵያ መንግስት ከአሁን በሁዋላ እያንዳንዷ ዶላር የት እንደዋለች የማሳመን ሃላፊነት ተጥሎበታል።
ሴናተር ሌሂ በተደጋጋሚ ጊዚያት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች አያያዝ ላይ የተለያዩ ሪፖርቶችን አቅርበዋል። በተለይ በቅንጅት አመራሮችና በእስክንድር ነጋ መታሰር በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሰፊ ንግግር አድርገዋል። እኝህ ሰው ታዲያ ያላቸውን የካበተ ልምድና የ40 ዓመት የሴናተርነት አገልግሎታቸውን በመጠቀም አንቀፁ እንዲካተት በማድረጋቸው በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በማህበረሰብ ተቋማት በኢትዮጵያውያን አክቲቪስቶችና በዲያስፖራ በሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምሁራን ምስጋና እየተቸራቸው ይገኛል።
የህጉ አንደምታ
ህጉ የዜጎች መብት እስካልተጣሰ ድረስ እርዳታ መሰጠቱን አይቃወምም። ድንጋጌው በሐምሌ 2013 ተጠንስሶ በቅርቡ ህግ ሆኖ የወጣው ይኸው አስገዳጅ አንቀጽ ለኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የቤት ስራ የሰጠ ሆኗል። ተጠያቂነት አስቀምጧል። ይሄ ካልተፈፀመ እርዳታውን በቀጣይ ዓመት ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ከአሜሪካ መንግስት በእርዳታ የምታገኝ በመሆኑ ይህን ርዳታ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታዎቹን ቢያንስ በአጭር ጊዜ የማሟላት ግዴታ ይኖርበታል። እንዲህ በቀላሉ ከማንም የማታገኘው እርዳታ ስለሆነም የኢትዮጵያን መንግስት ቢያንስ የተወሰነ የፖሊሲ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ያስገድደዋል። በቅርቡ አቶ በረከት ስምኦን እንዳሉት ገበሬው ተኛ ስንለው ይተኛል ሩጥ ስንለው ይሮጣል ምንም ብናደርገው ተሸክሞን ይዞራል ያሉት ነገር የሚሆን አልመሰለኝም።ህዝቡን እንደፈለክ በተለይ በእኛ ገንዘብ ልታሽከረክር ከአሁን በሁዋላ አትችልም እየተባለ ነውና። ያው ገበሬውም ቢሆን የሚያገኘው የእርዳታ እህል በአብዛኛው የሚገኘው ከዚቹ ከአሜሪካ አይደል? ስለዚህ ቀደም ብሎ ነበር እንጂ አሁን እንኳን የአሜሪካ መንገድ የካሮትና የዱላው አማራጭ ይመስላል።meles and obama
የኦባማ አስተዳደር   
የሕጉን አንቀጽ የኦባማ አስተዳደር እንዴት ሊያልፈው ቻለ? የሚለው ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በጣም አነጋጋሪ ሆኗል። የአብዛኞቹ ምሁራን ሃሳብ ወደ አንድ ያዘነበለ ነው። እሱም አንቀጹ የተካተተው በአንድ በሺዎች በሚቆጠሩ ገፆች ባሉት የበጀት ህግ ውስጥ በመሆኑና በዴሞክራቶቹና በሪፐብሊካኖቹ መካከል በርካታ አጨቃጫቂ አንቀፆች የነበሩ በመሆናቸው ብዙ ትኩረት ሳይሰጡበት ሾልኮ አምልጧል የሚል ነው። ምክንያቱም የኦባማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለው ጥብቅ ግንኙነት በዚህ ሁኔታ እንዲሻክር አይፈልግምና። የህጉን አንቀጽ አስተዳደሩ አውቆት ቢሆን ኖሮ ህግ ሆኖ እንዳይወጣ ያደርገው እንደነበርም መገመት ተገቢ ነው። የአሜሪካ መንግስት አቋሙ ምን እንደሆነ እስካሁን በይፋ የገለፀው ነገር የለም። ለህጉ ከመገዛት ግን ሌላ የተሻለ አማራጭ አይኖረውም። መንግስቱ ለፓርላማው ተገዥ ነውና።
የህጉ ተግባራዊነት
የህጉ ተግባራዊነት የግድ ይላል። ምክንያቱም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንቀጹ በህጉ ተካቶ ፀድቋል። ይህን የህግ አንቀጽ ይዘው ማንኛቸውም የኮንግረንሱ አባላት ይመለከተኛል የሚልም ዜጋና ተቋም የአሜሪካ ባለስልጣናትን ፍርድ ቤት አቁሞ ለተግባራዊነቱ ሊሞግታቸው ይችላልና።የኦባማ አስተዳደር በዚህ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ባይፈልግም የፓርላማውን ውሳኔ የማስፈፀም ሃላፊነት ስላለበት አዎንታዊ ጫና ሊያሳድር ይችላል።
የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ/ስጋት
በእርግጥ በጉዳዩ ላይ መንግስት እስካሁን ያለው ነገር የለም። ከነበረው ሪከርዱ መረዳት እንደሚቻለው ግን የአሜሪካ መንግስት የሚሰጠው እርዳታ አነስተኛ ነው። ከአሜሪካ የምናገኘውን እርዳታ ጨምራ ቻይና ትሰጠናለች።መንገዳቸውን ጨርቅ ያድርግላቸው። የሚሉ ምላሾች እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ነፍሳቸውን ይማርና የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍበት በአንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ በሶማሊያ የተካሄደውን ጦርነት አስመልክተው ስለ አሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ተጠይቀው አሜሪካ ኮንዶም ነው የምትረዳን በኮንዶም ነው ወይ ሶማሊያ የምንዋጋው? ብለው መናገራቸውን አስታውሳለሁ። ከዚህ በመነሳት የራዕያቸው ተረካቢዎችም ቃላት ለዋውጠው ወይ ይህንኑ ወርሰው ሊናገሩ ይችላሉ። አንዳንዶቹም አሜሪካ ሉዓላዊነታችንን ትነካለች ስለዚህ እርዳታው ይቅርብን ሊሉም ይችላሉ። የኦባማ አስተዳደርም አንቀጹ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን የመከላከል በአንዳንድ ጉዳዮችም ላይ የተለየ አቋም ሊይዝ ይችላል።
በእኔ የህግ እውቀት ከሆነ ይህ ህግ ሆኖ የጸደቀው አንቀጽ ራሱን ችሎ ያልወጣ በመሆኑና በበጀት ህጉ ውስጥ ተካቶ በመፅደቁ ብሎም ከህጉ በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው የ2014 የዩናይትድ ስቴትስ የበጀት ህግ በመሆኑ የኦባማ አስተዳደር ካላመነበት ከአንድ ዓመት የዘለለ እድሜ ስለማይኖረው የተደረጉት ጥረቶች በድል ተጠናቀዋል /mission accomplished/ ማለት አያስችልም።
መልካም እድሎች
የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ እርዳታ ይቅርብኝ ቻይና አለችልኝ የሚል ምላሽ መስጠት አያዋጣውም። ምክንያቱም ቻይና የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን ረገጠም በህዝቡ ተረገጠም ጉዳዬ ብላ አትከታተልም። ንግዷን እስካጧጧፈች ድረስ መስጠት የምትፈልገውን ትሰጣለች። ስለዚህ የአሜሪካ እርዳታ መቅረት ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር በመረዳትና ወደአላስፈላጊ ግጭት እንዳይሄድ በመፍራት የኢትዮጵያ መንግስት በአፈቀላጤዎቹ/ሎቢስት ጭምር ሳይቀር ለመደራደር የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል። ብሎም የአውሮፓ ህብረት ከአሜሪካ በላይ ለኢትዮጵያ ገንዘብ የሚረዳ ተቋም ነውና እሱም የአሜሪካ መንግስትን አቋም ደግፎ ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ከደረሰ የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚገባው። ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ለፕሮፓጋንዳ እምቢኝ ዘራፍ ቢልም ቀስ በቀስ ጉዳዩን እኛም በትራንስፎርሜሽኑ እቅዳችን ይዘነው ነበር በማለት ፖሊሲዎቹን የማስተካከል እርምጃ እንደሚወስድ መገመት ይቻላል።
መደምደሚያ
ያም ሆነ ይህ ይሄ ሸንቋጭ ህግ በኮንግረንሱ ፀድቆ ወጥቷል።አሜሪካም ከመግለጫ ያለፈ እርምጃ እንድትወስድ ሲጨቀጭቋት ለነበሩት አካላት መጠነኛ እፎይታ እንዲያገኙ አድርጋለች። እሰጣ ገባው የሚወሰነው ግን በዋነኝነት የኢትዮጵያ መንግስት በሚይዘው አቋም ላይ ይሆናል።
በአሜሪካ ኮንግረንስ የፀደቀው የህግ አንቀፅ እመራዋለሁ አስተዳድረዋለሁ አገሬ ነው ዜጋዬ ነው ለሚል ስርዓት አጋዥ እንጂ ፀሩ የሚሆንበት ሁኔታ ስለማይኖር የኢትዮጵያ መንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት ተረክቦ ለህዝቡም ለአገሪቱም የሚበጀውን ይሄን ውሳኔ ያስተግብር!አራት ነጥብ። (ፎቶ: KAREN BLEIER/AFP/Getty Images)
ጎልጉል

No comments: