Wednesday, February 12, 2014

‹‹ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ስለሚባለው ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ


February 12/2014



የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የሥልጣን ዘመናቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታትን ማስታረቅ እንደሚፈልጉ የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሆነው ኢቴቪ በይፋ ገልጸው መስመር የያዘላቸው መሆኑንም አሳውቀው ነበር፡፡

በቅርቡ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ምንም ዓይነት የዕርቅ ፍላጐት እንደሌላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሮፓጋንዳ ብልጫ እየተጠቀመበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄ የሰጧቸው ምላሾች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

‹‹የሕዝብ ግንኙነት ብልጫ ለማግኘት ነው››

ሁለት የኤርትራ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች አንዳንድ የአገር ውስጥና የአካባቢ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄዎችን ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አንስተውላቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ ግንኙነት ላይ የሰጡት አስተያየት አነጋጋሪ ነው፡፡

በመግለጫው ከተገኙ የመንግሥት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እንዲህ ብሎ ፕሬዚዳንቱን ይጠይቃቸዋል፤ ‹‹ኤርትራና ኢትዮጵያን ለማስታረቅ አንዳንድ ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነ በሚዲያዎች እየተነገረ ነው፡፡ ይኼ የሚወራው ነገር እውነት ነው ወይ?›› ይላቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለጥያቄው መልስ መስጠት ሲጀምሩ ፊታቸውን ጨለም አድርገዋል፡፡ የሆነ ከውስጥ የሚሰማ የቁጣ ስሜት እንዳለ ያሳብቅባቸዋል፡፡ መልስ መስጠት ቀጠሉ፡፡ ‹‹ከምኡ ዝበሃል ነገር የለን›› [እንደዚያ ብሎ ነገር የለም] በሚል በእምቢተኝነትና በእልኸኝነት ውስጥ ሆነው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡

‹‹እንደዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ ወያኔ እስኪጠፋ ዕለት እንደዚህ ብሎ ማውራቱ ይቀጥላል፡፡ ዓላማውም የሕዝብ ግንኙነት (PR) ብልጫ ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ በማድረጉ የፕሮፓጋንዳ ትርፍ ያገኝ ይሆናል፡፡ ወያኔ ያላንኳኳው በር የለም፡፡ የልጆች ሥራ ነው የሚመስለው፣›› ኢሳያስ ምላሻቸው በዚህ አላበቃም፡፡

‹‹ምናልባት ቀደም ሲል እንዲህ ተባለ እንዲህ ሆነ እያሉ ሊያታልሉን ሞክረው ይሆናል፡፡ እኔ የሚገርመኝ ጊዜያቸውን በዚህ ለምን እንደሚያጠፉ ነው፡፡ የአዞ እምባ ነው፡፡ እኛን ለማሰይጠን እነሱን መልዓክ ለማስመሰል፡፡ ምንም ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ፡፡ በአገር ውስጥም በውጭም ያለው የኤርትራ ሕዝብ ፈጽሞ ስለዚህ ማሰብ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ምላሻቸው እየተባለ ያለው የዕርቅ ጥያቄ የውሸት መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፈጠራ ወሬ መሆኑንና ኤርትራዊያንን ለማሞኘት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕርቅ ለመፍጠር ‹‹ያላንኳኳው በር የለም›› ካሉ በኋላ ዓላማው እውነት ዕርቅ ፍለጋ ሳይሆን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላም ወዳድ መስሎ ለመታየት ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከዚሁ ቀጥሎ የቀረበላቸው ተከታይ ጥያቄም ከዚሁ ጉዳይ ጋር ቅርበት ያለው ነው፡፡

‹‹ከዚህ ጋር በተያያዘ [የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ምክትል ኃላፊ የነበሩት] ኸርማን ኮኸን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ አለበት በሚል የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይኼና ሌሎች ጽሑፎች የአሜሪካ መንግሥት አቋም ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻል ይሆን?›› የሚል ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምላሾች በአብዛኛው በንቀት የተሞሉ የሚመስሉ ነበሩ፡፡ ‹‹አምባሳደሩ ኤርትራን ከብርድ እንታደጋታለን ነው የሚሉት፡፡ የምን ብርድ ነው እኛ ዘንድ ያለው ኤርትራ ገዳም ወጥታለችና ወደ ቤቷ እንመልሳት ነው እኮ የሚሉት፤›› የሚል ምላሽ ፕሬዚዳንቱ ሲሰጡ የቁጭት ስሜት ይነበብባቸዋል፡፡

አምባሳደር ኸርማን ኮኸን የቀድሞ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የአሜሪካን መንግሥት በውጭ ፖሊሲ ከሚያማክሩ መካከል ናቸው፡፡ ‹‹ኤርትራን መታደግ አሁን ነው›› በሚል በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በጻፉት የመፍትሔ ሐሳብ፤ ኢትዮጵያ አወዛጋቢውን የባድመ ግዛት ለኤርትራ እንድትሰጥ፣ በሁለቱም አገሮች መካከል ዕርቅ እንዲወርድ፣ ይኼም በአንድ ገለልተኛ የአውሮፓ አገር [ማን እንደሆነ ያልተገለጸ] አነሳሽነት እንዲጀመር የሚሉ ናቸው፡፡ የእሳቸው የዕርቅ ሐሳብ መነሻ ሁለቱም መንግሥታት (ኢትዮጵያና ኤርትራ) በድንበር አካባቢ ባለው ሰላምና ጦርነት አልባ ሁኔታ ተሰላችተዋል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት የዕርቅ ፍላጎት አሳይተዋል የሚል ነው፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተለያዩ ሚዲያዎች የሰጡዋቸው የተለሳለሱ አስተያየቶችን መታዘባቸውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ኸርማን ኮኸን፣ በተጨማሪ ያነሱት ጉዳይ ኤርትራ በሶማሊያ በምታደርገው አፍራሽ እንቅስቃሴ ምክንያት በፀጥታው ምክር ቤት የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ የሚል ነው፡፡ ለዚህም እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ኤርትራ አደብ መግዛቷንና አልሸባብን ስለመደገፏ አንድም ማስረጃ አልተገኘም የሚል ነበር፡፡ አምባሳደሩ ጽሑፋቸውን ባወጡበት ወቅት ይኼ አስተያየት ተመድና የአሜሪካ መንግሥት ካቀረቧቸው ሪፖርቶች ጋር የሚቃረን መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹ከብርድ ሊገላግሉን ነው?›› በሚል ፌዝ መሰል ንግግር የጀመሩት ፕሬዚዳንቱ የአምባሳደሩን ሐሳብ አጣጥለዋል፡፡

‹‹በ[ሸባብ] ምክንያት በኤርትራ ሕዝብ ላይ ከሳሽ ራሳቸው ፈራጅ ራሳቸው ሆነው ቀጥተውናል፡፡ በፈጠራ ታሪክ ነበር ማዕቀብ ያስጣሉብን፡፡ አሁን ደግሞ ከ2009 ጀምሮ ምንም የሉበትም ይላሉ፤›› በማለት ቀደም ሲል ከ2009 በኋላ በኤርትራ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት የጣለው ማዕቀብ ድሮም፣ በተፈበረከ ውንጀላ ነው የሚለውን ንግግራቸውን አምባሳደሩ ያረጋገጡላቸው በሚመስል ስሜት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው ብሎኛል፤›› በማለት አምባሳደሩ ያቀረቡትን አስተያየት ያጣጣሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹ቆይ ከየት የመጣ ነገር ነው? መቼ የት ነው እንዲህ ያልኩት?›› የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበው፣ ‹‹ይኼ ማለት’ኮ ኤርትራ ያለ ኢትዮጵያ የለችም እንደማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የኸርማን ኮኸን የዕርቅ ሐሳብ በተመለከተ ግን ሌላ ቀደም ሲል የተገመተ መላምት ሰጥተዋል፡፡ የኤርትራና የአሜሪካ ግንኙነትን ለማዳስ ያለመ እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ‹‹ሐሳቡ የቀረበበትን ጊዜ፣ ይዘቱን፣ ቋንቋውንና አቀራረቡን ስትመለከተው ይኼው ነው፡፡ ኤርትራ ግን አትፈልገውም፡፡ ከአሜሪካ ጋር የሚሻሻል ዝምድና ምንድን ነው? መጀመሪያ ራሳቸው በራሳቸው በፈጠሩት ውሸት የኤርትራን ሕዝብ ለመቅጣት ከጀሉ፡፡ ‹‹እናዳክማቸዋለን፣ እንቀጣቸዋለን፤›› በማለት ምላሻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ አሜሪካውያን ስለኤርትራ ሕዝብ መወሰንም አለመወሰንም መብት እንደሌላቸው በማተኮር፡፡

የወያኔ ሴራ በሚለው ተደጋጋሚ አገላለጻቸው፣ ‹‹በኤርትራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥፋት ከፈጸሙ በኋላ የኤርትራ ወጣቶች ከአገር እንዲኮበልሉ ካደረጉ በኋላ አሁን የምን ዕርቅ ነው?›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቅርቡ በሱዳን ፕሬዚዳንት አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የዕርቅ ሐሳብ የያዘ ደብዳቤ መላካቸውን አንዳንድ ሚዲያዎች ዲፕሎማቶችን ዋቢ በማድረግ የዘገቡ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ግን የዕርቅ ጥያቄው ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርብ መሆኑን፣ እሱም ቢሆን እውነትነት እንደሌለው ነው በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቃለ ምልልስ ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የተባለው ከእሳቸው የማይጠበቅ መሆኑንና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው መንግሥት አስመራ እስካለ ድረስ ምንም አዲስ ነገር እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአሁኑ ንግግራቸው በመስከረም ወር አካባቢ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ሙልጭ አድርገው የካዱት ይመስላሉ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ያለው የልማት እንቅስቃሴና ሌሎች የመንግሥት አውታሮች በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦት ምክንያት መቆሙን፣ እንዲሁም የአሰብ ወደብ ምንም ጥቅም እየሰጠ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት፣ ወደቡም ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በማዘጋጀው ለኢትዮጵያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡

ይህም በሁለቱም አገሮች መካከል ለሚዲያ ይፋ ያልሆነ የዕርቅ ጥረት ስለመኖሩ፣ እንዲሁም እንደ አምባሳደር ኸርማን ኮኸን የመሳሰሉ ሰዎች ፕሬዚዳንቱ ዕርቅ ማድረግ ይፈልጋሉ የሚል አመለካከት እንዲኖራቸው ሳያደርግ አልቀረም፡፡ የአሁኑ የኢሳያስ አስተያየት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡  

በአሁኑ ንግግራቸው ግን የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በመግዛት ላይ ከምትገኘው ከሱዳን እንገዛለን ብለዋል፡፡ ይህ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሳበ ቢሆንም፤ ምን ማለት እንደሆነ ለብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡ ቀደም ሲል በጂቡቲ በኩል ወደ ኤርትራ በሚገቡ የቡናና የጤፍ ምርቶች ምክንያት ኤርትራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ቡና አቅራቢዎች ግንባር ቀደም አድርጓት እንደነበር አንዳንዶች ያስታውሳሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከአገር ውስጥ ጉዳዮች በተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እ.ኤ.አ. በ2014 ምን ዕቅድ እንዳላቸው ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ ‹‹አሁን አላወራውም እንጂ በክልሉ ጉዳዮች ቀጥተኛ ተሳታፊ ለመሆን ዕቅድ አለን፤›› ብለዋል፡፡ በአካባቢው እየመጣ ያለው ለውጥ የኤርትራን ቀጥተኛ ተሳታፊነት እንደሚጠይቅ የገለጹት ኢሳያስ፣ በአካባቢው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከዚህ በፊት በተለየ ሁኔታ ለለውጦች ምላሽ መስጠት ሳይሆን፣ ቀድሞ ዕርምጃ በመውሰድ የለውጡ አካል ለመሆን የኤርትራ መንግሥት ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ወዴት እንደሚያመራ ግን አመላካች የለም፡፡ ከዚህ በፊት ጎረቤት አገሮችን በመውረርና በመተንኮስ እንዲሁም በሶማሊያ ጣልቃ በመግባት የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተያዘው አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ግን ሊገልጹ ያልፈለጉት ጉዳይ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ ሪፖርተር

No comments: