Friday, February 14, 2014

አዲስ አበባ የሚገኙ የዓረና ፓርቲ ወጣት አባላት በአሰብ ወደብ ዙሪያ ጥልቅ ፖለቲካዊ ውይይት አደረጉ

February 13/2014
በአዲስ አበባ የሚገኙ የዓረና ፓርቲ አባል ወጣቶች የአሰብ የባህር በርን በተመለከተ በየካቲት 2/2006 ዓ.ም ፓርቲው በከፈተው አዲስ ጽ/ቤት ጥልቀት ያለው ፖለቲካዊ ውይይት አድርጓል፡፡
በእለቱ ሰፊ ትንተና ያቀረበው ደራሲ እና ፖለቲከኛ ወጣት አስራት አብረሃም ሲሆን በውይይቱ ጊዜም ወጣቶቹ የጦፈ ክርክር አካሄደዋል፡፡ ወጣት ፖለቲከኛው ስለ አሰብ ጉዳይ ሲያብራራ ንጉስ ሐይለሥላሴ በአንድ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ወይይት ቀርበው መመለስ ያለበት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የኤርትራዊያን የዜግነት (የኢትዮጵያዊነት) ጥያቄም የአለም አቀፍ ተቋሙ በአግባቡ አጢኖ መመለስ እንዳለበት ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከር የኢትዮጵያ አንድነት ሲያጸኑ በህወሀት የአገዛዝ ዘመን ግን የተገላቢጦሽ ድርጊት መፈጸሙ ምን ያህል ኃላፊነት በማይሰማው ግድየለሽ መንግስት እየተመራን መሆኑን ጠቅሶ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን እያልን ያለነው «አሰብ ይገባናል» ብቻ ሳይሆን “የኛ ነው” ሲል ሀሳቡን አንጸባርቆዋል፡፡

ቀጥሎም በውይይቱ ወቅት የአልጀርሱ ስምምነት በሁለቱም መንግስታት ስላልተከበረና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ሉዓላዊነት የሚጻረር ስለሆነ መከበርም እንደሌለበት በመጥቀስ ኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ ድርድር አድርገው የኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባህር በር ባለቤትነትም የሚያረጋግጥና ሉዓላዊነታችን የሚያከብር ስምምነት መደረግ እንዳለበት አንስቶዋል፡፡
ኤርትራ በሪፈረንደም (ሪፈረንደም ከሆነ -ምክንያቱም “ነጻነት ወይስ ባርነት” ተብሎ ሕዝባዊ መደረጉ እጅግ አከራካሪ ሆኖ ሳለ) ከእናት አገርዋ ስትገነጠል የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ከየት ወዴት እንደሆነ በውል ሳይካለል የተደረገ ችኩል ፍቺ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ወጣቶቹ በውይይታቸው ኢትዮጵያ አለአግባብ (በኢህአዲግ ችኩል ውሳኔ የተነሳ) በአመት ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጅቡቲ ወደብ ላይ ኪራይ በመክፈል ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከመዳረጓ ባሻገር የባህር በር አለመኖር ከብሔራዊ ጸጥታ እና ደህንነታችን በቀጥታ የተቆራኘ በመሆኑ የአጋራችን ሰላም አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን በአጽንኦት ገልጾዋል፡፡
እናት አገር ኢትዮጵያ ልጇ ሳትክድ ከአፍንጫው አርቆ ማየት የተሳነው አምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ እናት አገሩን በመክዳት አልፎ ተርፎም የሻእቢያ ሎሌ የሆኑት የህወሀት መሪዎች «ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ፤ አሰብም የኤርትራዊያን ነው» በማለት ኤርትራ የማታውቀውንና የማይመለከታትን የባህር በር እንድታገኝ ማድረጋቸው፣ በኢህዲግ ዘመን ከተፈጸሙ ታሪክ ይቅር የማይላቸው ከባድ ስህተቶች ቀዳሚ መሆኑ ወጣቶቹ በክርክራቸው ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም አጼ ዮሐንስ የባህር በር አስፈላጊነትን በተመለከተ “እንበለ ባህር በር መንግስት አይጸናም” በማለት ወደር የማይገኝለት የላቀ የአገር ፍቅር እንደነበራቸው፤ ጨፍጫፊው ኮሌኔል መንግስቱ ሀይለማርያምም ቢሆን በአገር አንድነት እና ሉዓላዊነት ጉዳይን በተመለከተ ድርድር እንደማያውቅ እና ጠንካራ አቋም እንደነበረው፣ በአንጻሩ ሁሌ ለኤርትራዊያን የሚያደላው መለስ ዜናዊ እና ፓርቲው «የባህር በር የኛ አይደለም። አመጣለሁ የሚል ካለም ብረት አንስተንም እንታገለዋለን» ማለቱ ከኢትዮጵያ መሪ የማይጠበቅ ንግግር መናገሩ በታሪክ ተዘግቧል፡፡
ዓረና ፓርቲም የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባህር በር በመሆኑ እና የአለም አቀፍ ህጎችም (International Law) ስለሚደግፋት አገራችን ህጎችን ተንተርሳ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን ማስከበር እንዳለባት የሚያምን ፓርቲ መሆኑ ይህንኑ ለማስፈጸምም በጽናት እንደሚታገል በፕሮግራሙ አስፍሮት ይገኛል፡፡
በመጨረሻም ወጣቶቹም አሰብም ሆነ ቀይባህር በጠቅላላው ከኤርትራዊያን በፊት የትግራይ ነገስታት እንደሚያውቁት እና የባህር በሩን ላለማጣት አባቶቻችን ከባድ ተጋድሎ አድርገው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ቀይ ባህርን የአረብ ባህር ለማድረግና አባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር የነበራቸው ህልም በጽናት መክተው ያስረከቡን በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ ድርብ አደራ እንደተጣለበት እና ይህንን ጥያቄ የመመለስ ታሪካዊ አደራም እንዳለበት በመጥቀስ ውይይቱ ተደምድሞዋል፡፡ ወይይቱ በተለያየ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ እንደምንቀጥልም ተረጋግጦዋል፡፡
ኪዳነ አመነ

No comments: