Monday, February 17, 2014

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተጠለፈ፤ ጠላፊው ምክትል አብራሪው ነው ተባለ

February 17/2014

ዘ-ሐበሻ  እንደዘገበው  ከአዲስ አበባ ተነስቶ በካርቱም በኩል አቋርጦ ወደ ጣሊያን ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠልፎ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ እንዲያርፍ መደረጉ ታወቀ። ጠላፊው ምክትል አብራሪው እንደነበርም የስዊዘርላንድ ፖሊስ አስታወቀ።


193 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ይጓዝ እንደነበር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረገጽ ዘ-ሐበሻ የተረዳች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 140 የሚሆኑት የጣሊያን ዜጎች እንደነበሩ መረጃው ያመለክታል። እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ ገጽ ገለጻ አውሮፕላኑ ቢጠለፍም ምንም ዓይነት ጉዳት በሰዎች ላይ ባለመድረሱ በተለዋጭ በረራ ሰዎችን ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ከገለጸ በኋላ መረጃውን ከድረገጹ ላይ አንስቶታል።

ቦይንግ 767-300 አውሮፕላንን ጠለፈ የተባለው ምክትል አብራሪው ምንም አይነት የጦር መሣሪያ አለመታጠቁን የዘገቡት የስዊዘርላንድ ሚድያዎች ዋናው አብራሪ (ፓይለት) ወደ መጸዳጃ ቤት ሲያመራ በሩን ቆልፎ ወደ ስዊዘርላንድ እንዲበር አድርጓል ሲሉ ዘግበዋል። ረዳት ፓይለቱ አውሮፕላኑን ጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ ካሳረፈ በኋላ ከአውሮፕላኑ በመስኮት በገመድ ተንጠላጥሎ በመውጣት እጁን ለፖሊስ በመስጠት ጥገኝነት እንደጠየቀ ተገልጿል፡፡ ጠላፊውም ጥገኝነት ለመጠየቅ ሲል አውሮፕላኑን አቅጣጫ በማስቀየር ለመጠልፍ መገደዱን ከታሰረ በኋላ ለፖሊስ ተናግሯል ሲሉ ሚዲያዎቹ ዘግበዋል።

                                 
                                           (የስዊዘርላንድ ፖሊሶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፋሪዎችን ከአውሮፕላኑ ሲያስወጡ)  
የኢትዮጵያ አየር መንገዱ አብራሪ በሃገሩ ላይ የሚደርስበት ስቃይ ይህን ድርጊት ለመፈጸም እንዳነሳሳው መግለጹን የስዊዘርላንድ ኤርፖርት ቃል አቀባይ የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ እስር ላይ እንደሚገኝም አስታወቀዋል።

አውሮፕላኑ ወደ ስዊዘርላንድ እየበረረ ባለበት ወቅት ነዳጅ እየጨረሰ የነበረ መሆኑን የገለጹት ሚድያዎቹ ምናልባትም በቶሎ ጄነቭ ላይ ባያርፍ ኖሮ ከ10 ደቂቃ በላይ የሚያስኬድ ነዳጅ አልነበረውም።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ኃላፊነት ለማግኘት የግድ የአንድ ዘር አካል፤ አልያም ደግሞ የኢሕአዴግ አባል መሆን እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ከድርጅቱ የሚለቁ ወገኖች መግለጻቸውን የሚያስታውሱ የፖለቲካ ተንታኞች ምክትል አብራሪው ይደርስበታል ወይም ደርሶበታል ተብሎ ከሚገመተው በደል አኳያ እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰዱ ላያስገርም ይችላል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የኢሕአዴግ መንግስት በዘር ላይ የሚያደርገውን አድልዎ፣ በደል እንዲሁም “እኔን ካልደገፋችሁኝ ምንም አታገኙም” የሚለውን አካሄዱን እንዲያቆም ይህኛው ትምህርት ሊሆነው ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በሚሰራው አድሏዊ ሥራ የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያውያን ፓይለቶች ድርጅቱን በመልቀቅ ለሌሎች ሃገራት አየር መንገዶች እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም።


No comments: