Wednesday, February 26, 2014

በሚኒስትሯ የትዊተር ገጽ ላይ የሰፈረው መልዕክት አነጋጋሪ ሆኗል

February 26/2014

















-መንግሥት አካውንታቸው ተጠልፏል እያለ ነው

የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በትዊተር ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ፣ ‹‹በተወዳጇ አፍሪካዬ ውስጥ ጥላቻና መገለል ቦታ የላቸውም፡፡

የአለባበስ ሥርዓት ወይም የፀረ ግብረ ሰዶማዊ ሕጐችን ማውጣት የመንግሥታት ሥራ አይደለም፤›› በሚል የወጣው መልዕክት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ መንግሥት ግን የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መጠለፉን ገልጾ፣ ይህ መልዕክት የሚኒስትሯንም ሆነ የመንግሥትን አቋም አይወክልም ሲል አስተባብሏል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኡጋንዳ የፀደቀውን ፀረ ግብረ ሰዶማዊያን ሕግ በመቃወም በሚኒስትሯ የትዊተር ገጽ ላይ የተጻፈው ይህ መልዕክት፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ የግብረሰዶማዊ መብቶች አቀንቃኞች አድናቆት ተችሮታል፡፡ ሆኖም ግን የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዓብይ ኤፍሬም፣ ‹‹መልዕክቱ በማይታወቁ ሰዎች የተጻፈ ሲሆን፣ የእሳቸውንም ሆነ የመንግሥትን አቋም የማይገልጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዓብይ አክለው፣ ‹‹ሚኒስትሯ ይህን የማኅበረሰብ ሚዲያ የሚጠቀሙት ሕዝቡ በቀጥታ ሊያገኛቸው የሚገቡ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ አዋጭ ሚዲያ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የትዊተር ገጻቸውን የሚያንቀሳቅሱት ራሳቸው ወይዘሮ ዘነቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዓብይ፣ በገጻቸው ላይ በጠላፊዎች በተላለፈው መልዕክት ሚኒስትሯ ማዘናቸውን አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መጠለፉን አረጋግጠው፣ ‹‹የሚኒስትሯን አካውንት ጠልፈው በመግባት የእሳቸውንና የመንግሥትን አቋም የማይገልጽ መልዕክት ያስተላለፉት ግለሰቦች ጉዳይ ከተጣራ በኋላ፣ አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡

የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መቼ እንደተጠለፈ በውል ባይታወቅም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ግብረ ሰዶማዊያን እኩል መብት ይኑራቸው የሚል መልዕክታቸው፣ ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በአካውንታቸው በድጋሚ ትዊት ተደርጓል፡፡ ሚኒስትሯ በዚህ የትዊተር ገጻቸው የተላለፉት መልዕክቶች በእሳቸው እንዳልተጻፉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 629 እስከ 631 ድረስ በሰፈረው መሠረት የግብረ ሰዶም ወንጀል አሥራ አምስት ዓመት ድረስ በእስራት ያስቀጣል፡፡

ሚኒስትሯን በትዊተር ገጽ ላይ የሚከተሏቸው 1,600 ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ማክሰኞ ምሽት ላይ ይህ ቁጥር 1,837 ደርሶ ነበር፡፡ እሳቸው ደግሞ የሚከተሏቸው 99 አካውንቶች ሲኖሩ፣ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ 672 የትዊተር መልዕክቶችን በገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡


No comments: