Friday, February 14, 2014

የአንድነት አባል በመሆኔ ከስራ ልባረር ነው” መምህር አማኑኤል መንግስቱ

February 13/2014

የአንድነት አባል በመሆኑ በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት አስተዳደር የተለያዩ ዛቻዎችና ማስጠንቀቂያዎች እየደረሱበት እንደሆነ የሚናገረው መምህር አማኑኤል መንግስቱ “ከዚህ በፊትም ያለምንም ምክንያት ከማስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስተው ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አውርደውኛል፡፡” በማለት በመንግስት ኃላፊዎች የደረሰበትን በደል ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ ተደጋጋሚ ዛቻ እየደረሰበት መሆኑንና በቅርቡም ከስራው ሊያፈናቅሉት እንዳቀዱ ጨምሮ አስረድቷል፡፡
መምህር አማኑኤል ላይ እየደረሰ ስላለው ዛቻ የተጠየቁት የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሀብቶም “በስልክ መረጃ አልሰጥም” በማለት መምህር አማኑኤል ወንጀለኛ ነው የሚል ምላሽ ለፍኖተ ነፃነት ሰጥተዋል፡፡
ለመምህር አማኑኤል መንግስቱ በማዝገበ ብርሀን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተመስገን ወ/ጊዮርጊስ ፊርማ በተሰጠው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው፡- የመንግስት ፖሊሲና ተግባሮች በተለያዩ አጋጣሚዎችና ድርጊት ማጥላላትና ሌሎችም እንዲያጥላሉ ተፅዕኖ ማሳደርና በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየሰራ ያለውን ሰራተኛመብት ተረግጧል መብትህን ለምንድነው የማታስከብረው በማለት ሽብር የመንዛት ሙከራዎችን ማድረግ የሚሉ ሀይለቃሎች ይገኙበታል፡፡
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የማዝገበ ብርሀን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤት ሃላፊዎችን በስልክ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

No comments: