Tuesday, December 3, 2013

ሳውዲ አረቢያ ጎዳና ላይ የኢትዮጵያውያን ደም ብቻ ነው የሚፈሰው

December 3/2013

ሳውዲ አረቢያ ጎዳና ላይ የኢትዮጵያውያን ደም ብቻ ነው የሚፈሰው፡፡ የሚያለቅሱትም ኢትዮጵያውያን ሆነዋል፡፡ ኦጋዴን ታነባለች፤ ጋንቤላ ውስጥ ተወላጆቹ ለአረቦቹ እትብታቸው የተቀበረበትን መሬት ትተው እየሸሹ ነው፡፡ በኦነግ ስም መታሰር አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ቀድሞ የታሰሩትንም ማዕከላዊ፣ ዝዋይ፣ቃሊቲ….እየማቀቁ ነው፡፡ ከየ አካባቢው ኢትዮጵያውያን መሬታችሁ አይደለም ተብለው ያፈሩትን ተነጥቀው እየተባረሩ ነው፡፡ ሙስሊሞቹ ታስረዋል፡፡ መስጊድ ውስጥ ፖሊስ ገብቷል፡፡ ገዳማት ለሸንኮር አገዳ ተከልለዋል፡፡ ወጣቱ ስራ አጥቷል፡፡ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ‹‹አሸባሪዎች›› ተብለው እየተሰቃዩ ነው፡፡ ህገ መንግስቱን ጠቅሶ መብትን ማስከበር ያስደበድባል፡፡ ያሳስራል፡፡
ኢትዮጵያ እንዲህ ሆነች፡፡ እምነት ምኑም ባይሆን በኢኮኖሚው ያስለቅሱታል፡፡ ከእነሱው ተጠግቶ ለኢኮኖሚው ግድ ባይኖረው በእምነቱ ይመጡበታል፡፡ ይህንም ቢሆን ‹‹ዝም›› ብሎ ቢያልፍ እህቱ ሳውዲ ውስጥ ተደፍራ ስትሞት ‹‹ህገ ወጥ ስለነበረች ነው›› ይሉታል፡፡ ለዚህ ሰቆቃ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ይደበደባል፡፡ ይታሰራል፡፡ ብቻ በአንድም ሆነ በሌላ ኢትዮጵያ ታነባለች፡፡ የሚያሳዝነው ግን እንዲህ እያነባች መጨፈሯ ነው፡፡
አንድ የአማርኛ ፊልም ላይ ነው፡፡ ተዋናዮቹ ‹‹ጥሮ ግሮ›› የሚለውን ቃል ወደ እንግሊዘኛ ለመተርጎም ሞክረው መጣር መጋር በኢትዮጵያ እንጅ ሌላ አገር እንደሌለ አምነው ይተውታል፡፡ እንደ እኔ ኢትዮጵያ እያነባች የምትዳንስ ብቸኛዋ አገር ትመስለኛለች፡፡ እያነቡ እስክስታ የእኛው ብቻ መገለጫ ይመስለኛል፡፡ ሰቆቃ ተለይቷት የማታውቀው አገር እያረረች ትስቃለች፣ እያነባች እስክስታውን ታስነካዋለች፡፡ ይህ የሚደረገው በገዥዎቿ ትዕዛዝ ቢሆንም የሚያለቅሱትም የሚዳንሱትም ግን ምስኪኖቹ ህዝቦቿ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› ለህዳር 29 ዳንስ እየተለማመዱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በሆነበት ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› የሚባሉት በተድላና በደስታ እንደሚኖሩ ሲነገር ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን እየራጠራለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ህቡዕ ይሆኑብኛል፡፡ መቼም ብሄር ብረሰቦችና ህዝቦች የሚባሉት ሳውዲ፣ ኦጋዴን፣ ጉራፈርዳ፣ ነቀምት፣ አዲስ አበባ……ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰቃዩትን ውጭ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሳውዲ ውስጥ እህቱ የሞተችበት እንባውን በቅጡ ሳይጠራርግ ይጨፍራል፡፡ መሬቱን የተነጠቀው፣ ወንዱሙ የታሰረበት፣ ከክልል የተባረረ…..እርር ድብን እያለም ቢሆን በትዕዛዝ እስክስታውን ይመታል፡፡ እያረረ ይስቃል፡፡
ህዳር 29ኝም ሆኑ ሌሎቹ በዓላት ለእኔ እንደዚህ ናቸው፡፡ ቋንቋህ ተከብሮልሃል ተብሎ መብቱን በአፍ መፍቻው መናገር ሳይጀምር ሰቆቃ የደረሰበት ህዝብ፣ የብሄርን መብት ተከብሮልሃል ተብሎ ከስም ያላለፈ ጥቅም ያላገኘ ‹‹ብሄርና ብሄረሰብ›› ከልቡ የሚያከብረው በዓል ሊሆን አይችልም፡፡ አዎ ህዳር 29 መብገኛ፣ እያረሩ የሚጨፈርበት፣ ህገ መንግስታዊ መብት ከጭፈራና ማስመሰል ያለለፈበት እያረሩ የሚስቁበት ቀን ነው፡፡

No comments: