Friday, February 7, 2014

የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ!!!

February 7/2014

“የግብርና ሚኒስትር” በሚል “የሆድ ሲያውቅ፤ ዶሮ ማታ” ስያሜ የወያኔ የመሬት ሽያጭ ጉዳይ አስፈፃሚው የሆነው የሥርዓቱ ቀንደኛ አገልጋይ “መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም” ብሎ ሲናገር የሰማነው እና ያነበብነው በከፍተኛ ትዝብት ነው።
ለመሆኑ የመሬት ቅርምት ከኢትዮጵያ በላይ ማንን ሊመለከት ነው? ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ሳውዲን፣ ቻይናን፣ ህንድን ወይስ አሜሪካን? ከራሱ ከወያኔ ሹማምንት የተራረፈው መሬት ለአረብ አገራትና ለእስያ ቱጃሮች በነፃ የሚታደለው ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? ባዕዳን የሚረከቡት መሬት ስፋት በሄክታር መለካት ሲሰለቻቸው “ቤልጂየምን የሚያክል” እያሉ በስጦታ ያገኙትን መሬት በአገር ስፋት የሚለኩት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለምን? የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን ካልተመለከተ ከቶ ማንን ሊመለከት ነው?
ወያኔ ለም መሬት ለራሱ ማግበስበሱ ሳያንስ “ልማታዊ ባለሀብቶች” እያለ ለሚያሞካሻቸው ለቅርብም ለሩቅም አገራት ቱጃሮች ሰጥቶ ባለሀገሩን አርሶ አደር ሜዳ ላይ በተነ። መጤው ቱጃር ባለመሬት ሆኖ ባለሀገሩ ለስደት አሊያም ለቀን ሠራተኝነት ተዳረገ። ይህ ግፍ የሚፈጥረው ስቃይ የማይበቃ ይመስል “በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ መሬት ሻጩ “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆኑ ነፃ መሬቶችን ብቻ ነው ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የምንሰጠው። ማንም ከቀዬው አልተፈናቀለም” እያለ ይዘባበትብናል። “የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት” የሚባለው መሬት የወያኔ የግል ሀብት ከሆነ ሃያ ሶስት ዓመታት መቆጠራቸው እኛ ብቻ ሳንሆን እሱም ያውቀዋል።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ለብናኝ አፈር በመሰሰት ጎብኚዎችን እግር አሳጥበው ሲሸኙ እንዳልነበር ዛሬ በልማት ስም ከጋምቤላ እስከ መተማ፣ ከባሌ እስከ ሰላሌ፣ ከከፋ እስከ አፋር ያለው መሬታችን በሙሉ ወይ በወያኔ ሹማምንት አሊያም በባዕዳን ቱዳሮች ይዞታ ሥር ሆኗል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሳዎችና ወጣቶች፣ ሕፃናት ሳይቀር የአዳዲሶቹ ባለመሬቶች ተቀጣሪዎች ሆነዋል። ጉልተኛው ሥርዓት ከቀድሞው በባሰ መልኩ ተመልሶ መጥቷል።
ወያኔ እንደሚያወራው ሰፋፊ መሬቶችን የመስጠት ዓላማው ግብርናችንን ለማዘመን ከሆነ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ጠፍተው ነው እሩቅ ምስራቅ እስያ ድረስ የተጓዘው? እነሱስ ለምንድነው ለሊዝ የሚጠየቁትን እዚህ ግባ የማይባለውን ገንዘብ እንኳን ከራሷ ከኢትዮጵያ ተበድረው የሚከፍሉት? ይህ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው? ከዛሬ አርባና አምሳ አመታት በፊት በሁመራ፣ ተንዳሆና ስምጥ ሸለቆዎች ውስጥ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች የነበሯቸው ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ያኔ ኖረው ዛሬ እንደምን ላይኖሩ ቻሉ? የመሬት ባለቤት የመሆን መብት ያለው ኢትዮጵያዊ ወያኔ ብቻ እንዲሆን የተደረገው ለምንድነው? ኢትዮጵያ፣ ወያኔ ወይም የወያኔ አሽከር ላልሆነ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነች? ባለሃገሩን መሬት አልባ፤ ባዕዳንን ደግሞ ባለመሬት ማድረግ ምን ያስከትላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ግብዓት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ከግብዓትም በላይ የፓለቲካ ሥልጣን ምንጭም ነው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ፓለቲካ የመሬት ጥያቄ ቁልፍ የፓለቲካ ጥያቄ ሆኖ የቆየው። ደርግ መሬትን ከጉልተኞችም ከአርሶ አደሮችም በአዋጅ ቀምቶ የመንግሥት በማድረግ መንግሥትን አሳብጦ ገበሬውን አዳከመው። ወያኔ ይኸንኑ መሬት ያለአዋጅ ከመንግሥት ቀምቶ የራሱ በማድረግ ራሱን አሳብጦ ገበሬውን ከቀደሞው በባሰ አዳከመው። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ይህንኑ መሬት ለባዕዳን በመስጠት ገበሬውን በአጠቃላይ ከመሬት ነጥሎ የቀን ሠራተኛ እያደረገው ነው። ይህ ከጪሰኝነት እጅግ የባሰ ባርነት ነው።
በወያኔ እና ታማኝ ተላላኪዎቹ እየተፈፀመ ያለው የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያዊያንን አገር የሚያሳጣ፤ ስብዕናችንን የሚያዋርድ፤ ክብራችንን የሚገፍ፤ ሀብታችንን የሚያዘርፍ በመሆኑ በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል።
ሰው ባገሩ ሰው በወንዙ
ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ
ይታወቅ የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ
ግንቦት7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለባዕዳን መሬታችንን፣ አገራችንን፣ ነፃነታችንን ሰጥተን ከሚገኘው ጥቅም … ባለቅኔው እንዳለው … ሰውነታችን ታውቆ፣ ክብራችን ተጠብቆ ሳርም ይሁን መቅመቆ መብላት እንመርጣለን። የመሬት ቅርምት በአስቸኳይ ይገታ። አገራችንን ለማዳን ቆርጠን እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments: