Thursday, January 9, 2014

ሰራተኛውና መንግስት የተፋጠጡበት መድረክ

January9/2014

ባለፈው ቅዳሜ (ታህሳስ 26 ቀን 2006 ዓ.ም) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አንድ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ስብሰባው በሀገሪቱ ሰራተኞች፣ አሰሪዎችና መንግስት መካከል ስላለው ግንኙነት ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ በዋናነትም የስብሰባው አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ነበር።
በስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ኮሚሽነሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር የተገኙበት ነበር። በሰራተኛው በኩል ሰራተኛውን ይወክላሉ የተባሉ በየሴክተሩ የተቋቋሙ የሰራተኛ ማኅበራትና በመጠኑም ቢሆን የአሰሪዎች ተወካዮች ተገኝተው ነበር።
የመደራጀት መብት አለመከበር፣ የኑሮ ውድነትና
የታክስ መደራረብ
የዕለቱ ስብሰባ ተጀምሮ የነበረው ሰራተኛውን የሚወክሉ የማኅበራት መሪዎች በዘርፍ በዘርፉ ተከፋፍለው በሰራተኛው የሚነሱ አሉ የተባሉ ጥያቄዎችን አንስተው ነበር። ጥያቄዎቹ በርካታ ቢሆኑም በዋናነት የሰራተኛው የመደራጀት መብት አለመከበር፣ የኑሮ ውድነት፣ በአሰሪና ሰራተኛ ወቅት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት አግባብ ያለው ፍርድ አለማግኘት፣ ሙስና የሚያጋልጡ ጠቋሚ ሰራተኞች ጥበቃ አለማድረግ ተደራራቢ የደመወዝ ገቢ ግብር ታክስና ሌሎች ጥያቄዎች ናቸው።
በሰራተኞቹ ተወካዮች በኩል በመረረ መንገድ ተደጋግሞ የተነሳው የሰራተኛው የመደራጀት መብት አለመከበሩ ብቻ ሳይሆን በአደባባይ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው መጣሱን ነው። ይህ የሰራተኛው የመደራጀት መብት ሲጣስም በመንግስት በኩል አርኪ ምላሽ አለመገኘቱ በስፋት አወያይቷል። ከዚሁ የመደራጀት መብት መጣስ ጎን ለጎን የኑሮ ውድነት ጥያቄውም የዕለቱን መድረክ የተቆጣጠረ ጉዳይ ነበር። “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር” በሚል ተማፅኖ በተደጋጋሚ ጊዜአት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ማስገንዘቢያ የሚመስሉ ጥያቄዎች ከሰራተኛው ተወካዮች ተወርውረዋል።
የሰራተኛው ተወካዮቹ በአሁኑ ወቅት በወር በሚከፈለው ደመወዝ እየኖረ አለመሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ኑሮ ከአቅም በላይ መሆኑንና ሰራተኛው የኑሮ ውድነቱን መሸከም እንዳልቻለ ገልፀዋል። ስለሆነም የኑሮ ውድነት ማሻሻያ ድጎማ እንዲደረግ ሲሉ ጠይቀዋል። በተመሳሳይ ሰራተኛው ላይ ተደራራቢ ታክስ መበራከቱ የሰራተኛውን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እየከተተው በመሆኑ የገቢ ግብርና የቫት ታክስ ማሻሻያ ጥያቄ አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት ታማኝ ታክስ ከፋይ ሰራተኛው ቢሆንም በሰራተኛው ላይ የተጫነው ተደራራቢ ታክስ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ተጠይቋል። በተለይ በአንዳንድ የግል ድርጅቶችና በመንግስት የልማት ድርጅቶች አካባቢ “እጅግ በጣም አሳዛኝ” በሚል አገላለፅ የመደራጀት መብት መምከኑን የገለፁ የሰራተኛ ወኪሎች ነበሩ። ግዙፉ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ በርካታ የልማት ድርጅቶች የሰራተኛው ሕገ-መንግስታዊ የመደራጀት መብት መጣሳቸውን ተናግረዋል። በእነዚህ በተጠቀሱ ተቋማት አዳዲስ የሰራተኛ ማኅበርን ለማቋቋም የሚጥሩ ሰራተኞችን ከስራ ማባረር የዕለት ተዕለት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 31 እና 42 በአደባባይ መጣሳቸውን በይፋ ተናግረዋል። ከሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ባሻገር ሀገሪቱ ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር በፊት ግንባር ቀደም ሆና የፈረመቻቸው የዓለም የስራ ድርጅት (ILO) ድንጋጌዎች ጭምር እየተጣሱ፣ ሰራተኞች እንዳይደራጁ ከተደራጁም በኋላ ምክንያት እየተፈለገ ሥራ ፈት እንዲሆኑ፣ ሰራተኞቹና ቤተሰቦቻቸው ለረሃብ እንዲጋለጡ መደረጉን አስረድተዋል።
አንዳንድ የግል አሰሪዎችና የመንግስት ኃላፊዎች የሀገሪቱን ሕገ-መንግስት እየጣሱ ነው በማለት “ማን ሃይ ይበላቸው” ሲሉ የተማፀኑት የማኅበራት መሪዎቹ “በነፃ መደራጀት አቅቶናል” ሲሉ አምርረው ገልፀዋል። “ሕገ-መንግስቱን የሚያስከብረው ማነው?” ሲሉ መሰረታዊ ጥያቄ አንስተዋል።
ከመደራጀት መብት እና ከሙያ ደህንነት ጋር በተያያዘ ተገቢ ጥንቃቄ ባለመወሰዱ በኮንስትራክሽን አካባቢ በኬሚካል መመረዝን ጨምሮ በርካታ ጉዳቶች ስለሚደርሱ ሰራተኛው ለጊዜያዊና ዘላቂ ችግሮች እየተጋለጠ እንደሆነም ተናግረዋል። ለሰው ልጅ ጤንነት አደገኛ የሆኑ መራዥ ኬሚካሎች የሰራተኛውን ዓይን እንዲያጣ፣ በቆዳው እና በመራቢያ አካላቱ ላይ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
ከመብት ማስከበር አንፃር የሰራተኛ ማኅበር መሪዎች አለአግባብ ከስራ እንደሚሰናበቱና በፍርድ ቤት ተከራክረው ሲመለሱ የፍርድ ቤት ውሳኔ በመጣስ ለኢንዱስትሪ ሰላም ሲባል ካሳ ተከፍሎአቸው እንዲባረሩ ይደረጋል ብለዋል። በሁለት ወር ማለቅ ይገባው የነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር እስከ አንድ ዓመት ተኩል ስለሚራዘም ፍትህ እየተዛባ መሆኑን ተናግረዋል። የመንግስት ሰራተኞችም እንደሌሎቹ ሰራተኞች የመደራጀት መብታቸው በሕገመንግስቱ መሠረት እንዲከበር ጠይቀዋል። በዚህ በኩል በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 የተቀመጠው ገደብ እንዲነሳም አሳስበዋል።
ሌላው ሀገሪቱ የአስተዳደር ሕግ (administrative law) የሌላት በመሆኑ በኃላፊዎችና በባለስልጣናት በርካታ ችግሮች መፈጠሩን የሰራተኞቹ ተወካዮች ሳይገልፁ አላለፉም። አንዳንድ የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ከስራ ካሰናበቱ በኋላ ወደ ስራ ሲመለሱ ወጪውን የሚሸፍነው የልማት ድርጅቱ በመሆኑ ኃላፊዎች እንዳሻቸው ሰራተኛውን እያጉላሉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አንዳንድ አሰሪዎች ሰራተኛውን የሚያስሩበት የራሳቸው እስር ቤት ያላቸው መሆኑን በምሬት የገለፁት የሰራተኛ ማኅበራት ወኪሎቹ፤ ከስራና ሰራተኛ አገናኝ ጋር በተያያዘ ከአረብ አገር በባሰ መልኩ በሰራተኞች እየተነገደ መሆኑንም አስረድተዋል። በዚህ ረገድ በአንዳንድ የውጪ ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የጉልበት ብዝበዛ እየተፈፀመ ነው ብለዋል። ከአንድ ሰራተኛ በነፍስ ወከፍ እስከ 4ሺህ ብር እየተቀበሉ በተጨባጭ ለሰራተኛው ጥቂት መቶ ብሮች በመክፈል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሚፈፅሙ ደላላዎች ቢኖሩም መንግስት በቸልታ እየተመለከታቸው ነው ብለዋል። በጥቅሉ ከአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ጋር በተያያዘ ከአረብ አገር የባሰ የጉልበት ብዝበዛ እየተካሄደ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
“ሰራተኛው አንድ ጫማ ከቀየረ ይበቃዋል። በዚያው መጠን አምስትና ስድስት መኪና የሚቀያይሩ ቀጫጭን ባለሀብቶች ተፈጥረዋል” ሲሉ ቅሬታ ያቀረቡት የሰራተኞቹ ተወካዮች፤ “በአሰሪውና በሰራተኛው የጨቋኝና ተጨቋኝ መደባዊ ግንኙነት እየተፈጠረ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። “ድሮ የምናውቀው ወፍራም ባለሀብት ነበር፤ የዛሬ ባለሀብቶች ግን ቀጫጭን ናቸው። የጋራ ሀገራችን በጋራ ማልማት አለብን። ሕገ-መንግስቱ ለድርድር መቅረብ የለበትም። አሁን ያለው ሰራተኛ ከሁለት ሚሊዮን ላይበልጥ ይችላል። በቀጣይ ዓመታት ሃያና ሰላሳ ሚሊዮን ሰራተኛ ሲፈጠር በዚህ መንገድ መቆጣጠር አይቻልም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
አንዳንድ አሰሪዎች የሰራተኛ መደራጀትን የኮሚኒዝምና የሶሻሊዝም ፍልስፍና ርዕዮተ ዓለም አድርገው የሚያስቡ አሉ በማለት የመደራጀት መብትን ከሕገ-መንግስቱ የተገኘ አድርጎ ያለማሰብ ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል። በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ የመንግስት ኃላፊዎችም ሳይቀሩ እንዳሉበት አስረድተዋል። ከዚያ ባለፈ የውጪ ባለሃብቶች በሀገራቸው የሰራተኛ ማኅበርን እያከበሩ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሰራተኛውን መብት እንደሚጥሱ ገልፀዋል። አንዳንድ የውጩ ሰራተኞች የቀን ሰራተኛ ከመሆን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን መሰማራት በሚገባቸው የስራ ዘርፍ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ተሰማርተው እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የመንግስት ባለስልጣናቱ ምላሽ
በሰራተኞች ማኅበራት ተወካዮች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ጨምሮ የመንግስት ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ላይ በመሆኑ የሰራተኛው ሚና ጉልህ መሆኑን ደጋግመው ገልፀዋል። ለዚህ ደግሞ የሰራተኛው የመደራጀት መብት ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት አስምረውበታል። ሰራተኞች በማኅበር የሚደራጁት ለውዝግብ ሳይሆን የጋራ ሀገራዊ ራዕይን ለማሳካት፣ ለምርታማነት መሆን እንዳለበት ገልፀዋል። በመሆኑም መንግስት፣ አሰሪና ሰራተኛ በጋራ በመሆን ለምርታማነት እድገት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው አሰሪዎች የሚፈፅሙትን ችግር የሁሉም አሰሪ አድርጎ ማቅረብ ግን ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈ በሕግና በመደራጀት በኩል ስላሉ ችግሮች የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩና የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመንግስት በኩል ያሉ ክፍተቶችን በመዝጋት በኩል የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ አምነው የፖሊሲና የሕግ አፈፃፀሞች ላይ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የታክስና የኑሮ ውድነትን በተመለከተም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ለታክስ መሻሻሉም ሆነ ለደመወዝ ጭማሪ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ማደግን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጠዋል። በአጭር አገላለፅ “ኬኩ ካላደገ” የታክስ ማሻሻያውም ሆነ ድጎማና የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ እንደሚያስቸግር ነው የገለፁት። “ትልቁን ስዕል ማየት አለብን” ያሉት አቶ ሶፊያን የደመወዝ ጭማሪም ሆነ ሌሎች ድጎማዎች ከሀገሪቱ እድገት ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል። ከደመወዝ ገቢ ግብር ጋር በተያያዘም የገቢ ግብር ታክሱን ለማሻሻል ጥናት እየተከናወነ መሆኑን በመጥቀስ በገቢ ግብር አዋጁ ሲሻሻል ዝቅተኛ ደመወዝ ላይ የገቢ ታክስ ማሻሻያ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተዋል። በተለይ የገቢ ግብር አዋጁ ሲሻሻል የተወሰኑ አሰሪዎች ለሰራተኞች ምግብ የሚመግቡ ከሆነ ከገቢ ግብር ነፃ እንደሚደረጉም ከወዲሁ አብስረዋል። የመኖሪያ ቤት ሰርተው የሚሰጡ አሰሪዎች ካሉም በዚሁ ማሻሻያ የሚታዩ እንደሆነም አስረድተዋል።
ምግብ ላይ የተጣለው ተደራራቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት)ን በተመለከተ መንግስት አሁንም በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ከቫት ነፃ ማድረጉን የገለፁት አቶ ሶፊያን፤ ነገር ግን በምግብ ስም በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች የሚቀርቡ ምግብ ላይ ታክስ ማንሳት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው በማለት ለጊዜው ቫት የሚነሳበት ዕድል እንደሌለ ነው የጠቀሱት።
የኑሮ ወድነትን በተመለከተ መንግሰት ደመወዝ ከመጨመር አንስቶ ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይትና ዳቦ በከፍተኛ ድጎማ እያከፋፈለ መሆኑን። በዋናነት የኑሮ ውድነቱ ችግር ሊፈታ የሚችለው ኬኩ ሲያድግ ነው ብለዋል። ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ መንግስትም፣ ባለሃብቱም ጥሩ ደመወዝ የሚከፍሉት ኬኩ ሲያድግ ነው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንቱ አቶ ተገኔ ጌታነህ በበኩላቸው በፍ/ቤቶች በኩል በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ስላለው የፍትህ መጓደል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ችግሩን ለመፍታት የፍርድ ቤቶችን ቁጥርና የዳኞችን ቁጥር ለመጨመር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በሕጉ በተቀመጠው የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር ችሎቶች በሁለት ወር ማለቅ ሚኖርበትም ከ2000 የስራ ክርክር መዝገቦች ወደ መቶ የሚሆኑ መዝገቦች በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ መዘግየታቸውን አምነዋል። አንዳንዶቹ መዝገቦች ሰራተኞች ጉዳያቸውን በድርድርና በፍርድ አፈፃፀም የሚዘገዩ ናቸው ብለዋል።
ሙስና በማጋለጥ ረገድ ለሰራተኞች ተገቢውን ከለላ አይደረግም ለሚለው የሰራተኞቹ አቤቱታ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን ምላሽ ሰጥተው ነበር። ኮሚሽነሩ፤ “ከለላ የጠየቀን ሰራተኛ የለም” ቢሉም በሰራተኞቹ በኩል ሙስናን በማጋለጥ ረገድ በሰራተኞች ላይ በርካታ በደል እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል። ከበደሉ የተነሳ “ሰራተኛውን ሙስናን ከመታገል ውጪ አድርጉት ወይም ጥበቃ አድርጉለት” እስከማለት ደርሰው ነበር። የፌዴራል የሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን ግን በዚህ ረገድ የቀረበውን አቤቱታ ቀዝቀዝ ያለ መልስ ነበር የሰጡት። ኮሚሽኑ ከሰራተኛው ጋር በንቃት እየሰራ ከመሆን ባለፈ ቅሬታው የጎላ አለመሆኑን ጠቅሰው አልፈውታል። በተለይ የስነ-ምግባር መኮንኖች ተጠሪነት ለስራ አስኪያጁ መሆናቸው ጋር በተያያዘ ለተነሳው ቅሬታ “የስነ-ምግባር መኮንኖቹ ስራ አስኪያጅን ለመሰለል የተቀመጡ አይደሉም” ብለዋል። በአንፃሩ የስነ-ምግባር መኮንኖቹ ግን በቀጥታ ከኮሚሽኑ ጋር የሚገናኙበት መስመር መኖሩን ጠቅሰዋል።
ሌላው በሰራተኞች ቀርቦ የነበረው ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሸን ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ ሰራተኞች እንዳይቀነሱ የሚለውን ስጋት በተመለከተም ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል በኮርፖሬሽኑ ለሁለት መከፈል የሚቀነስ ሰራተኛ እንደሌለና ይልቁንም ተጨማሪ 4 ሺህ ሰራተኛ ይቀጠራል ብለዋል። የመስሪያ ቤቱ ለውጥ ሰራተኛ ለመቀነስ ሳይሆን የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ ነው ብለዋል። ለውጡም ከሰራተኛው ጋር በሚደረግ ውይይትና ምክክር መሆኑንም አስረድተዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስሞኦን በበኩላቸው ሰራተኛው በሀገሪቱ ፈጣን የእድገት ሂደት ውስጥ ዋና ተዋናይና ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል። የሰራተኛ የመደራጀት መብት በተመለከተ ያለው ችግር የቆየ መሆኑን፣ እንቅፋቶቹም ትንሽ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በእድገት ላይ በመሆኑና ብዙ ስራ አጥ በመኖሩ ባለሃብቱ ሰራተኛውን እንደፈለገው ሊያደርግ ይችላል ብለዋል። መሠረታዊ መፍትሄው የኢኮኖሚ እድገቱን ማፋጠንና ሰራተኛውን ተጠቃሚ እንዲሆን እና የመደራጀት መብት የሕግ ከለላ መስጠት እንደሚገባም ገልፀዋል። በዋናነት መንግስት በሰራተኛው ብቃትና የግዜ አጠቃቀም ላይ የራሱ ስጋቶች ቢኖሩም፤ በሰራተኛው መብትና ጥቅም ክልል ውስጥ ሆኖ በነፃ የሚገኝ የመደራጀት መብት አለመኖሩን አውቆ ሰራተኛው ትግሉን እንዲቀጥል ብለዋል።
የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ላይ ለተነሳው ቅሬታ ብርጋዴል ጀነራል ክንፈ ዳኘው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል በልማት ድርጅትነት ተቋቁመው በሚሰሩ ድርጅቶች የቆመ ድርጅት መሆኑን በማስታወስ የሰራተኛ ማኅበራት መፍረሳቸውን ገልፀዋል። ሆኖም ግን እንደ ኮርፖሬሽን የራሱ ሰራተኛ ማኅበር መቋቋም እንዳለበት ኮርፖሬሽኑ ያምናል ብለዋል። በጀነራሉ አገላለፅ ተቋሙ ዴሞክራሲያዊ ህይወት እንዲኖረው ይፈልጋል። ዴሞክራሲያዊ ህይወት የሌለው ድርጅት ምርታማ አይሆንም ብለዋል። ስለሆነም ማደራጀት ላይ ችግር የለውም። ነገር ግን 15 ሺህ ሰራተኛ እንዴት ይደራጅ የሚለው ላይ መዘግየት መኖሩን ጠቅሰዋል። ለመዘግየቱም የኮርፖሬሽኑ በአዋጅ ለመከላከያ የተሰጡት ስልጣኖች አሉት። የልማት ድርጅት ቢሆንም፤ የጦር መሳሪያ የሚያመርት ተቋም ነው። የመከላከያ ሰራዊት አባላትም የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ናቸው። ተቋሙ በተወሰነ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ መብት ገደብ የሚጣልበት በመሆኑ ጦር መሳሪያ የሚያመርት ተቋም የተደራጀ ሰራተኛ እንዴት እንደሚኖረው ተጠንቶ ተግባራዊ መደረግ አለበት የሚለው ተጠንቷል። ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ታይቶ በሚመለከተው አካል ሲፀድቅ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል። ጀነራሉ እግረ መንገዳቸውንም ኢሰማኮ ኮርፖሬሽኑን ቀርቦ በማየት በኩል ድክመት ያለበት ኮንፌዴሬሽን መሆኑን በመግለፅ “የተንሳፈፈ” ሲሉ ወቅሰዋል።
አሰሪዎችን በመወከል አቶ ታደለ ይመርም በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሰራተኛ ማኅበራት ከድርድር ባለፈ ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። አሰሪዎችና ሰራተኞች ከተጠራጣሪነት መንፈስ እንዲላቀቁ መፍትሄ ነው ያሉትን ጉዳይ ዘርዝረዋል።
     በአጠቃላይ መድረኩ ሰራተኞችም አለብን ያሉዋቸውን ችግሮች ያቀረቡበት መንግስም ለሰራተኞቹ ጥያቄ ከገቢ ግብር የማሻሻያ ተስፋ ውጪ ሌሎች ጥያቄዎች በአመዛኙ አርኪ ምላሽ ያላገኙባቸው መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።

No comments: