Tuesday, August 6, 2013

ወያኔዎች ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሽብር ተግባር ለመወንጀል ቦምብ አያፈነዱም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው

August 6, 2013
እንደልቡ ወርቁ

A bomb exploded near a court in the west of Ethiopia's capital Addis Ababaባለፉት ሀያ አንድ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ “የሽብር ተግባራት” የሚመስሉ “ሽብሮች” ተከናውነዋል። በሚኒባስ ዉስጥ፣ በሆቴሎች ዉስጥ፣ በቤተ ክርስትያን ቅጥር ግቢ ዉስጥ ወዘተ… ይሁንና ለአንዳቸውም የሽብር ጥቃቶች ባለቤት ተገኝቶላቸው አያውቅም፣ ባለቤት መገኘቱ ይቅርና የረባ ተጠርጣሪ ተይዞ ፍርድ ቤት ሲመላለስ እንኳ አልታየም።

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ህዝቡ ግን “ሽብሮቹን” የሚፈጽመው እራሱ ወያኔ ነው በማለት ያጉረመርሙ ነበር።
ህዝቡም ሆነ ተቃዋሚዎች በሽብር ተግባራቱ ወያኔን ክፉኛ ከሚጠረጥሩባቸው ምክንያቶች ውስጥ፣

1) ወያኔዎች በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻን እንዳተረፉ ስለሚረዱ ማናቸውም አይነት የፖለቲካ ድርጅት ሀገር ውስጥ መንቀሳቀስ ከቻለ ህልውናቸው እንደሚያከትም እርግጠኛ ሆነዋል። ስለዚህም የሚያስፈራቸውን የተቃዋሚ ድርጅት በሽብር ተግባራት ፈርጆ ከጫወታ ውጭ ማድረግ የዘወትር ተግባራቸው ነው። ታድያ እንዚህን ያስፈሯቸውን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች በሽብር ተግባር ለመወንጀልና ለመክሰስ ሽብር ቢጤ መከናወን አለበት።
 
2) ሌላው ወያኔዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር አለ ብለው እራሳቸውን የምዕራባውያን የጸረ-ሽብር አጋር አድርገው ለማቅረብ ያላቸው ፍላጎት ነው። ሶማሊያ ውስጥ ያሉትን አክራሪዎች እጃቸው ኢትዮጵያም ይደርሳል በማለት ምዕራባውያንን ማሳመንና ማግባባት ያስፈልጋቸዋል፣ ለዚህም ደግሞ እዚህና እዚያ በአካራሪዎች የተፈጸመ የሚመስል የሽብር ተግባር እንዲኖር ያስፈልጋል።
 
ይህን የህዝቡንና የተቃዋሚዎቹን ጥርጣሬ እውነት ነው የሚያስብል ሁኔታ የተከሰተው ግን ዘግይቶም ቢሆን “ዊኪሊክስ” የአሜሪካ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ይፋ ባደረገ ማግስት ነው። የአሜሪካ ዲፕሎማቶች “በአዲስ አበባ የሚፈነዱት ቦንቦች የአሸባሪዎች ጥቃት ናቸው ብለው እንደማያምኑ” የሚያመላክቱ መልዕክቶችን በተደጋጋሚ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግቶን ዲሲ ሰደዋል።
ቦታ እየቀያየረ መጫወት የማይሆንለት የጥንቱ የጥዋቱ የደደቢቱ ወያኔ ዛሬም ድረስ ይህኑ ተጨፈኑ ላሞኛችሁ “ሽብር መጣባችሁ” ድርጊቱን ገፍቶበት ይገኛል።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሀይማኖታቸው ጉዳይ መንግስት ጣልቃ በመግባቱ ፍጹም ሰላማዊና ስልጡን በሆነ መንገድ ከአንድ አመት በላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የፍትህ ያለህ በማለት ላይ ናቸው።

ምንም እንኳ ወያኔ በጸረ-ሽብር አጋርነቱ ታውቆ ከአሜሪካና ምዕራባውያን አሳዳሪዎቹ ዘንድ እርጥባንና የፖለቲካ ድጋፍ እየተቸረው የዘለቀ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን “አሸባሪ” ናቸው ብሎ ለማስፈረጅ ግን አልተቻለውም።
ሰሞኑን የፊታችን አርብ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የኢድን በዓል አስመልክተው በመላ ሀገሪቱ ሊያደረጉ ያሰቡት ተቃውሞ ወያኔን አስደንግጦታል። በኮፈሌ ከ25 በላይ ንጹሀን ሙስሊሞችን በአጋዚ የጎሳ ወታደሮቹ አስጨፍጭፎ ሲያበቃ በአዲስ አበባ ደግሞ ሙስሊም ወላጆችን ሰብስቦ ልጆቻችሁ ለተቃውሞ እንዳይወጡ እያለ ይማጸናል።

ወያኔ ጭንቀቱ እንደበረታበት የሚያሳየው ሌላው ትዕይንት ደግሞ፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ከ30 በላይ ኤምባሲዎች የፊታችን አርብ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል መልዕክት ማስተላለፉ ነው።
ወያኔዎች ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሽብር ተግባር ለመወንጀል ቦምብ አያፈነዱም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በዚህ ወቅት ነቃ ብሎ አካባቢን እያጠኑ መንቀሳቀስ ደግሞ ብልህነት ነው።

No comments: