Tuesday, August 27, 2013

ተስፋሁንን መግደል ለኢህአዴግ ተስፋ ይሆናታልን….!?



ተስፋሁንን መግደል ለኢህአዴግ ተስፋ ይሆናታልን….!?

bbbአብዲሳ የብዙ ጊዜ ወዳጄ ነበር፡፡ በየገጠሩ እየዞርን በርካታ ስራ አብረን ሰርተናል፡፡ የዋህነቱ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ በየክልሉ ስንዞር አበሉን የሚጨርሰው “ቸገረኝ” ላለው ሁላ መበስጠት እንደነበር አብረነው የሰራ ሁላ እርሱን የምንለይበት ባህሪው ነው፡፡ ይሄ ልጅ በአንዱ ቀን ለስራ ልንሄድ የተቀጣጠርንበት ቦታ ሆነን ስንጠብቀው ስንጠብቀው ሳይመጣ ቀረ… ስልኩን ብንደውልልት አይሰራም፡፡ ካለንበት እየተንቆራጠጥን… ወደ ሶስት ሰዓት ድረስ ዘግይተን ጠበቅነው የውሃ ሸታ ሆነብን… ምን ሆነ ብለን እየተጨነቅን እንጀራ ነውና ጉዟችንን ቀጠልን…

አብረን ስንጓዝ ከነበርነው መካከል አብዲሳን በቅጡ የምናውቀው ሰዎች “ይሄኔ አንድ የታመ ሰው አጋጥሞት ሆስፒታል ሳላደርስ አልሄድም ብሎ ነው…” ….ወይ ደግሞ “…አንዱ ገንዘብ ተቸግሮ አጋጥሞት  ምንም ሳያስቀር ገንዘቡን ሰጥቶ ወደ እኛ መምጫ ራሱ ተቸግሮ ይሆናል …” ካልሆነ ግን “…ዘራፊዎች አግኝተው ጉድ አድርገውት ሊሆን ይችላል…. እያልን መገመታችንን ተያያዝነው…

ግምታችን ሁሉ ትክክል አልነበረም፡፡

አብዲሳ በስንተኛው ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት መታየቱን ሰማን… በየዋህነቱ የተቸገረ በመርዳቱ የምናውቀው አብዲ “አሸባሪ” ተብሎ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ አብዲሳ “አሻባሪ” ከተባለማ እኛ ምን ልንባል ነው… ብለን ራሳችንን እንደ ነውጠኛ የምናየው እኛ በጣም ተደነቅን!

አብዲ ወደ አምስት ወራት በማዕከላዊ፣ ወደ አምስት አመት በቃሊቲ እንዲሁም ሁለት ሶስት አመት ነው መሰለኝ በዝዋይ ማሰሪያ ቤቶች ቆይቶ ነፃ ነህ ተብሎ እስኪሰናበት ድረስ በአስር ቤቱ ውስጥ ሲደርስበት በነበረው መከራ ብዙ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ታድያ ከእስር ቤት ሊወጣ አካባቢ አንድ ባለስልጣን ብጤ ሰውዬ ጎብኝተውት ነበር፡፡

እስር ቤቱ እንዴት ነበር… ሲሉ ጠየቁት፡፡ አብዲሳ ምን አላቸው መሰልዎ… እስር ቤቱ እንዴት እንደሆነ ራስዎት ገብተው ካላዩት በስተቀር እንዲህ ነው ብዬ  ብነግሮት አይገባዎትም ፡፡ አላቸው፡፡

ይሄው ሰሞኑን ወንድማችን ተስፋሁን ጫመዳ በእስር ቤት በደረሰበት ስቃይ የተነሳ ህይወቱ ማለፏን ሰማን፡፡ ተስፋሁን በ1999 ዓ.ም መንግስት ኬኒያ ድረስ አፍኖ ወሳጆቹን ልኮ ለኬኒያ ፖሊስ ሽልጉን ከፍሎ፤ (የኬኒያ ፖሊስ እንኳንስ ከፍለውት እንዲሁም ጤዛ ነው) ብቻ በትብብር ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ነበር… ከዛም በታሰረበት ሆኖ ሞተን ሰማን!

ለዚህ ጉዳይ የሚሰማ ቢኖር የኬኒያን መንግስት ራሱ ፍርድ ቤት ማቆም የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ራሱ፤ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል እግዜሩም እኛም የምንጠይቀው ግን የገዛ መንግስታችን ነው፡፡ አዎ መንግስታችን እጁ ላይ የተለያዩ ሀገራት ብድር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሰዎች እምባ የተለያዩ ሰዎች ደምም አለበት፡፡

ተስፋሁን ለምን እንዲሞት ተፈረደበት… እውን ለሀገሪቱ ደህንነት ስጋት ሆኖ ነውን… የሚለውን በፍጹም!!! ለማለት፤ እነ አብዲሳን ያየነው እኛ ምስክሮች ነን፡፡ ምስኪኑ አብዲሳ ስምንት አመት ታስሮ በነፃ ከመፈታቱ በፊት “የሀገር ስጋት ሽብርተኛ!” ተብሎ ነበር የታሰረው፡፡  በእስር ቤት የደረሰበትን ስቃይ ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ነው፡፡ የነገረኝን በሙሉ ለማሳየት በፊልም እንጂ ጽሁፍ የሚገልፀው አይደለም፡፡

እሺ ኢንጂነር ተስፋሁን የኦነግ ወይም የሌላ ተቃዋሚ አባል ወይም ደጋፊ ወይም እንዳሻቸው ይሁኑ ባይ ነው እንበለው፡፡ ግን እርሱን በመግደል የሚቃወሙ ሰዎችን ተስፋ ማስቆረጥ አልያም  ቁጥራቸውን መቀነስ ይቻላል….

ኢህአዴግ በጫካ እያለች ታጋዮቿ እና ሰላዮቿ ደርግ በቁጥጥር ስር ሲያውላቸው ቀጥታ አብዮታዊ እርምጃ ይወስድባቸው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ምንድነው  የሆነው… ብለው የጠየቁ እንደሆ፤  ውጤቱ ብሶቱን እያጠነከረው ቁጭቱን እያባሰው እምቢ ባይነቱን እያበረታው ነው የሄደው…!

ዛሬ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ውስጥ ፍዳቸውን እያዩ ነው… የምር ለኢህአዴግ እናስባለን የምትሉ ሰዎች የእነ ተስፋሁን ግድያ የኢህአዴግ ተስፋ ሟጠጡን ያሳያልና…. ይሄ ነገር መሞቻሽ ነው ብላችሁ ምከሯት፡፡ እምቢ ካለች ግን መከራው ይመክራታል፡፡

ምክር!

ባለስልጣኖቻችን ሆይ እናንተ ማረሚያ ቤት የምትሏቸው እስር ቤቶች መግደያ ቤት እየሆኑ ነው፡፡ ብልጥ ከሆናችሁ…. አብዲሳ እንዳለው ራሳችሁ ገብታችሁ ሳታዩት በፊት በእስር ለሚማቅቁ ወገኖቻችን መላ ፈልጉ!
ተስፋሁን ጫመዳ ነፍሱን ከደህናው ስፍራ ያሳርፍልን! ለቤተሰቦቹም መጸናናትን ይስጥልን!

http://www.abetokichaw.com/

No comments: