Wednesday, June 5, 2013

ከተቃውሞ ሰልፉ በሁዋላ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አመራሮች እየተገመገሙ ነው

ግንቦት ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፈው እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ ያካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በማግስቱ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አመራሮችን እንዲሁም በፕሮፓጋንዳ መስክ ላይ የተሰማሩትን በመጥራት ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ግምገማ እያካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።

 አብዛኞቹ አመራሮች ሂስና ግለሂሳቸውን እንዲያወርዱ የተጠየቁ ሲሆን፣ የድርጅቱ አባሎች በጸረ ህዝቦች ፕሮፓጋንዳ በመወናበድ እና ለግንባሩ ርእዮተ አለም ትኩረት ባለመስጠት ድርጅቱን ከውስጥ እያዳከሙት ነው የሚል ወቀሳ ከከፍተኛ አመራሮች ተስምቷል።
ግምገማው በክልል ከተሞችም በመካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል። አብዛኞቹ ነባር አመራሮች ” በጦር ያልተፈታው ኢህአዴግ በወሬ አይፈታም” በማለት በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አመራሮች፣ ጸረ ሰላም ሀይሎች ከሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ተነግሮአቸዋል።

በግምገማው የተሳተፈ አንድ የድርጅት አባል “እንዲህ አይነት ግምገማ በድርጅቱ ታሪክ ውስጥ አጋጥሞኝ አያውቅም፣ ከእሁድ በሁዋላ ድርጅታችን ታምሷል፣ መሪዎቻችን በጣም ተበሳጭተው መግቢያ እያሳጡን ነው” በማለት ለኢሳት ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራ ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ እየተዘዋወረ የህዝብ አስተያየት በመሰብሰብ ላይ ነው።  አቶ አዲሱ ትናንት በዴቻ ወረዳ  160 ሰዎችን ሰብስበው ስለመልካም አስተዳደርና ስለሌሎች ጉዳዮች አወያይተዋል። በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የጠየቁ ወጣቶች ስብሰባውን እንዳይካፈሉ መደረጋቸው ታውቋል።

No comments: