Tuesday, June 25, 2013

ፕሬዚዳንት ግርማ ለፍትሕ ሚኒስቴር ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በከባድ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ ዋና ጸሐፊና የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ፣ የተከሰሱበት ክስ እንዲቋረጥላቸው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ ውድቅ መደረጉን  ሪፖርተር ዘገበ፡፡

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ፤የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ለፕሬዚዳንት ግርማ በጻፉላቸው የመማፀኛ ደብዳቤ መነሻነት ፤ፕሬዚዳንት ግርማ – ክሱ እንዲቋረጥላቸው ወይም በይቅርታ እንዲታለፉ  ደብዳቤውን የጻፉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ለአቶ ብርሃኑ ፀጋዬ  ነው።

በከባድ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው፦ የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ፣ ዋና ጸሐፊው ፲ አለቃ ሰጥአርጌ አያሌውና የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ አቶ በቀለ ሻረው ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ በደብዳቤያቸው፦ ተጠርጣሪዎቹ በአገራቸው የጀግንነት ታሪክ ከፍተኛ ቦታ እንዳላቸው፣ ለአገር ልማትም በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንና ዕድሜያቸውም የገፋ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ይቅርታ አድርጐላቸው ክሳቸው እንዲቋረጥ ነው የጠየቁት።

ፕሬዚዳንቱ ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በቁጥር መ/818/2005 የጻፉትን ደብዳቤ የተመለከቱት የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት፤ ጥያቄው ተገቢ አለመሆኑን እና ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊትም ፍርድ ቤት ቀርበው በሚደረግ የግራ ቀኝ ክርክርና የሕግ ሒደት ብቻ የሚታይ መሆኑን በመግለጽ፣ ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረጉት የጋዜጣው  ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እነ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ የተከሰሱት፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ አርከበ ዕቁባይ፣ አቅመ ደካማ ለሆኑ አባት አርበኞች የፈቀዱላቸውን 25 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለግል ጥቅም አውለዋል፣ ከሚያከራዩዋቸው ሕንፃዎች ከሚያገኙት ገቢ ላይ የአከራይ ተከራይ ግብር አይከፍሉም፣እና የማሕበሩን ገንዘብ  ያላግባብ ወጪ  ያደርጋሉ በሚል ነው ።

ዋና ጸሐፊውና የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው እያንዳንዳቸው በ25 ሺሕ ብር ዋስ ሲለቀቁ፤ ፕሬዚዳንቱ  በቀጠሮ ባለመቅረባቸው ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ  እንደተሰጠ መዘገቡ ይታወሳል።

No comments: