Thursday, June 13, 2013

ኢሕአፓ በአዲስ አበባ በርካታ ቦታዎች በህቡዕ ወረቀት በተንኩ አለ


Imageበስውር የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)አባላት በአዲስ አበባ በርካታ ቦታዎች ረቡዕ ሌሊት ሰኔ 5/2005 ዓ.ም. /June 12, 2013/  ተነሥ በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ቀስቃሽ ፅሑፎችን የበተኑ ሲሆን በዋናነት በቦሌ፣በካዛንቺስ፣በአራት ኪሎ፣በሽሮ ሜዳ፣በቄራ፣በፈረንሳይ ለጋሲዪን፣በሜክሲኮ፣በፒያሳ፣በመገናኛ፣በኮልፌ፣በመርካቶ፣በጎፋ እና በመሳሰሉት ዋና ዋና የከተማዋ ክፍል በሚገኙ የማስታወቂ ቦርዶች ላይ ተለጥፈው የታዩ ሲሆን በተለይ ሐሙስ ሰኔ 6/2005 ዓ.ም. በርካታ ነዋሪዎች ጽሑፉን ማንበብ ችለዋል።ይሁን እንጂ ይህ ዜና የደረሳቸው የገዢው ፓርቲ አመራሮች ወዲያው የፌደራል ፖሊሶችን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትን በማሰማራት በዋና ዋና ቦታዎች ላይ የሚገኙትን ያነሱ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢ ግን ጽሑፎቹ እስከ ቀትር ሳይነሱ በበርካታ ሰዎች መነበብ ችለዋል።
 
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በ5ለ1 አደረጃጀት ጠርንፎ እንደያዘ የሚነገርለት ኢህአዴግ ይህ አይነቱ ድንገተኛ ክስተት ዛሬም ድረስ ከህዝብ ጋር ሆድ እና ጀርባ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲሉ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ትዝብታቸውን የገለፁ ሲሆን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የአዲስ አበባ ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ የወጣቶች ሊግ አመራሮች አስቸኳይ ስብሰባ ሐሙስ ዕለት እንደተቀመጡ ከስፍራው መረዳት ተችሏል።
 
ተነሥ  በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የዚህ ጽሑፍ ይዘት የሚከተለው ነው፦ “እጅግ የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፦ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት፤ይልቁንም ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ጮራን የፈነጠቅህ ፋና ወጊ የነፃነት አርበኛ መሆንህ የአደባባይ ምስጢር ነው።
 
Imageይሁን እንጂ የዚህ ሁሉ ጥንካሬህ መሠረት የሆነው አንድነትህ በጎጠኛው የወያኔ ቡድን የዘውጌ አስተዳደር ተሸርሽሮ ዛሬ በሀገርህ ተንቀሳቅሰህ የመስራት መብትህ ተገድቦ፣ከችሎታህና ከግለሰባዊ ክህሎትህ ይልቅ በዘር ማንነትህ እየተመዘንክ የኢኮኖሚ መገለል እየደረሰብህ ህይወት ብርቱ ሠልፍ ሆናብህ ሀገርህን ጥለህ እንድትሰደድ በተሰላ ስሌት በመኖርና ባለመኖር ቅርቃር ውስጥ እንድትባዝን ተደርገህ፣ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብትህ ተገፎ የመናገርና ሃሳብህን በነፃነት የማራመድ መብትህን ከመነጠቅህ ባሻገር በአጠቃላይ ህልውናህ በወያኔ የግፍ መዳፍ ውስጥ ወድቋል።

ስለሆነም እንደመዥገር በላይህ ላይ ተጣብቆ በደምህ የሰባውን ይህን ዘረኛ ቡድን ከጫንቃህ ላይ አራግፈህ በፍትህ አደባባይ የምታቆምበት ጊዜው አሁን ነው።ሀገርህንና ራስህን ለማዳን ተነሥ!!!”

No comments: