Thursday, June 13, 2013

ወደሶማሌ ክልል ተጉዞ የነበረው የአርቲስቶችና የጋዜጠኞች ቡድን በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዳለ ምስክርነቱን በመስጠት የአንድ ሳምንት ጉዞውን ሰኞ ዕለት አጠናቀቀ

ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ቡድኑ ከጎዴ ተነስቶ በቀብሪደህር፣ በደገሃቡር፣ በቀብሪበይህ፣ በጂጂጋ አድርጎ ወደሐረር በመግባት የሳምንት ጉዞውን በድሬዳዋ ከተማ ባለፈው እሁድ አጠናቋል፡፡

በጉዞው ወቅት በአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት የተጓዘው የዚሁ ቡድን አባላት ከሆኑት መካከል፤ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፣ደበሽ ተመስገን፣ጥላሁን ጉግሳ፣ችሮታው ከልካይ፣አብራር አብዶ፣ አበበ ባልቻና የመሳሰሉ አርቲስቶችና ጸሐፊዎች “በሶማሌ ክልል ፍጹምና አስተማማኝ ሰላም አለ” በሚል   ምስክርነት የሰጡ ሲሆን  ይህም  ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በአንድ መድረክ ላይ ባደረገው ንግግር “መጀመሪያ ከቤተሰቦቼ በቀን ለአምስት ጊዜያት ያህል ሰላም ነህ ወይ እየተባለ ይደወልልኝ ነበር፡፡ ቀስ እያለ በቀን ወደሶስቴ፣ ወደሁለቴ ወረደ፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛ እንምጣ ወይ ሳይሉ አይቀሩም” በማለት  ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

በጉዞው ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ቡድኑን ከማጀቡም በተጨማሪ በየበረሃው ከወትሮው በተለየ መልኩ የሰራዊቱ አባላት በከፍተኛ ቁጥር ተሰማርተው መታየታቸው፤ በአካባቢው የጸጥታ ችግር መኖሩን ጠቋሚ ኧንደሆነ በቡድኑ ውስጥ የተሳተፉ ወገኖች ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎችም ጉዞው ለደቂቃዎች እንዲቆም ኧየተደርገ ሰራዊቱ ቦታ ቦታውን ከያዘ በሃላ  እንዲቀጥል መደረጉታውቋል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አንዳንድ አርቲስቶች የሰጡት  ምስክርነት እውነታውን የማይገልጽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ያስገመተ እንደሆነ ለመረዳት ተችሎአል፡፡

በግልጽ ንግግራቸው የሚታወቁት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ባለፈው ዓርብ ዕለት ለአርቲስቶችና ጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር በክልሉ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ኦብነግ የተባለው ቡድን ጠንካራ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡

ኦብነግ ታላቋ ሶማሊያን ለመገንባት በእነኳታርና ግብጽ እየተደገፈ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን፣ በዚህ ምክንያት የክልሉ ሰላም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወድቆ እንደነበር በንግግራቸው ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር የኦብነግን እንቅስቃሴ በመደገፍ በሁለት ቢላዋ ይበሉ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡

በአንድ ወቅት በውጪ አገር ለኦብነግ ድጋፍ አልሰጥም ያለ የክልሉ ተወላጅ ወደሶማሌ ክልል ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ በሄደበት ጊዜ በክልሉ ፖሊስ ተይዞ ያለአንዳች ምክንያት እንዲታሰር መደረጉን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ   ኦብነግን ለምንድነው የማትደግፈው ተብሎ ሲጠየቅም፤ ሰውየው ጥፋተኛ መሆኑን፣ ከእንግዲህ ለመደገፍና ያለፈውንም ለመካስ ቃል በመግባቱ ከእስር መለቀቁን በመግለፅ ግንባሩ የቱን ያህል የመንግስት መዋቅርን ጭምር ተቆጣጥሮት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዲ በአሁኑ ሰዓት_ ኦብነግን ጨምሮ የሌሎች የጠላት ሃይሎች እንቅስቃሴ በመከላከያ ሰራዊት፣ በክልሉ ልዩ ሃይልና በሕዝቡ ትብብር ተረጋግጦአል ቢሉም አንዳንድ በጅጅጋ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ግን ዋና ከተማዋ ጅጅጋ እንኩዋን በከፍተኛ ጥበቃ ስር በመሆንዋ እንደልብ ወጥቶ ለመግባት እንደማይቻል ተናግረዋል:: አክለውም  ይህ የሰላም ምልክት እንዴት ሊሆን ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለ አርቲስቶችና ለጋዜጠኞች ቡድን በሶማሌ እና በሐረሪ ክልሎች ከፍተኛ አቀባበልና የጫት ግብዣ ተደርጎላቸዋል:: በቆይታቸው ደረጃውን ለጠበቀ የጫት ግብዝ ብቻ   ከ100ሺ ብር በላይ እንደወጣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አረጋግጠዋል፡፡
ጉዞውን የፌዴሬሽን ም/ቤት ከክልሎቹ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው ነበር፡፡

No comments: