Wednesday, September 4, 2013

መብራት ኃይል ከ5ሺ የሚልቁ ሰራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ

ከቅነሳው ጀርባ የዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል እጅ እንዳለበትም እየተነገረ ነው “ሰራተኛ ሊቀነስ ነው የተባለው ግን የውሸት ውሸት ነው” አቶ መስክር ነጋሽ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ከ5ሺ የሚልቁ ሰራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ዶ/ር ደብረፂዮን ነገ ከኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ጋር በሚያደርጉት የፕላዝማ ውይይት ስለሚቀነሱት ሰራተኞች ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት መስሪያቤቱ ይህንን ያክል ሰራተኛ ከስራ ከስራ ውጪ ለማድረግ የተዘጋጀው መንግስት ኮርፖሬሽኑን ለፓውርና ማኔጅመንት በሚል ከሁለተ ከፍሎ አንድ የህንድ ኩባንያ እንዲያስተዳድረው በመወሰኑ ነው፡፡
 
የፍኖተ ነፃነት የዜና ምንጮች ጨምረው እንደገለፁት መብራት ኃይል ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ትራንስፎርመሮችን እንዲገዛ መደረጉ መስሪያ ቤቱን ለከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ የኮርፖሬሽኑ ደንበኞቸም ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ተጠቂ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ “አሁንም መስራቤታችን ለህንድ ካምፓኒ እንዲሰጥ መደረጉ ከፍተኛ ጦስ ሊያመጣ እንደሚችል እንጠብቃለን” የሚሉት ምንጮቻችን “ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የቴሌን ሰራተኞች እንደበተኑት ዛሬም ኤልፓን ሊያንኮታኩቱት ነው” ብለዋል፡፡
 
ፍኖተ ነፃነት ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስክር ነጋሽ በመደወል የመስሪያቤቱን ምላሽ አግኝታለች፡፡ አቶ ምስክር “ነገ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና አለን፤ ሰራተኛ ሊቀነስ ነው የተባለው ግን የውሸት ውሸት ነው” የሚል ምላሸ ሰጥተዋል፡፡ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ለህንድ ካምፓኒ ሊሰጥነው የተባለው ገና ሂደት ላይ ያለ ነው ብለዋል፡፡

No comments: