Wednesday, November 5, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር አስተባባሪ ታሰረ

November 5,2014
ነገረ ኢትዮጵያ
• ‹‹ጎንደር ውስጥ ያለውን የህዝብ ጥያቄ ለማፈን የተደረገ ነው፡፡›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ

• ‹‹የፀረ ሽብር ህጉ የገዥው ፓርቲን ስልጣን ለመጠበቅ እየዋለ ነው፡፡›› አቶ ይድነቃቸው ከበደ


የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እና የሰሜን ጎንደር የዞን ሰብሰቢ አቶ አግባው ሰጠኝ ጎንደር ከተማ ውስጥ ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በገዥው ፓርቲ ደህንነቶች መታሰሩን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስና የደህንነት ኃይሎች አቶ አግባው ሰጠኝን ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ ከ1 ሰዓት ተኩል በላይ ፍተሻ እና ብርበራ በማካሄድ ስፍራው ወደልታወቅ ቦታ እንደወሰዷቸው ጎንደር ውስጥ የሚገኙ የፓርቲ አመራርና አባላት ገልጸዋል፡፡

አቶ አግባው ከተያዘ በኋላ ጎንደር ከተማ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ዘመዶቹ ፖሊስ ጣቢያዎችን እየዞሩ ቢያጠያቁም ‹‹ነገ ጠዋት ጠይቁ!›› ከሚል ትዕዛዝ ውጭ የታሰረበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ አግባው ሰጠኝ ከመታሰሩ በፊት የማያውቃቸው ሰዎች ለእሱ ተቆርቋሪ መምሰል ‹‹አርፈህ ስራህ ስራ፣ ከሰማያዊ ጋር የምታደርገውን እንቅስቃሴ አቁም፣ አዲስ አበባ ያሉት የፓርቲው አመራሮች ግንኙነታቸው ከሌላ ሰው ጋር ነው፡፡ ስለማታውቅ ነው፡፡›› ይሉት እንደነበር እንዲሁም ከመታሰሩ በሁለት ቀናት በፊት ከደህንነት የተላኩ ነኝ የሚል ግለሰብ ‹‹ከዚህ የማትወጣ ከሆነ በህይወት ላይ እርምጃ እንወስዳለን፣ መጀመሪያም መክረንሃል›› ብለው ይዝቱበት እንደነበር የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

ፖሊሶች የያዙት የፍርድ ቤት ማዘዣ ‹‹በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ በመሆናቸው አስፈላጊውን ፍተሻ ማካሄድ እንዲችሉ›› እንደሚል መረጃው የደረሳቸው የህግ ጉዳይ ኃላፊው ‹‹በመጀመሪያ የፀረ ሽብር አዋጁም ተቀባይነት የሌለውና የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ለማሰቃየትና ገዥውን ፓርቲ ለመጠበቅ የወጣ ህግ ነው፡፡ አሁንም የምናየው በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አባላት በመጠናከራቸው ለመገደብ እየተጠቀመበት ነው፡፡›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡

በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ‹‹ጎንደር አካባቢ በማህበራዊና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለ፡፡ አቶ አግባውን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮችና አባላት ህዝቡን ስለሚያስተባብሩ ነው የታሰሩት፡፡ ጎንደር ውስጥ ያለውን የህዝብ ጥያቄ ለማፈን የተደረገ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም አርባ ምንጭ ላይ ህዝቡ ተቀባይነት ያላቸውና ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አመራሮችና አባላት ላይ ተመሳሳይ እስር ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ሌሎች አባላትና አመራሮችም አሁንም ድረስ እያዋከቧቸው ነው፡፡›› ብሏል፡፡

ኃላፊው አክሎም ‹‹በተለይ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በጋራ እየሰሩ በመሆኑ ስጋት ውስጥ የወደቀው ገዥው ፓርቲ እንቅፋት ለመፍጠር ነው እስራቱን የሚፈጽመው፡፡›› ሲል ገዥው ፓርቲ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን የፓርቲ አመራሮችና አባላት በማሰር ፓርቲውን ለማዳከም የሚያደርገው የተለመደ ስልት መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ በተመሳሳይ ሰሞኑን በመኢአድ፣ አንድነትና አረና አመራሮችና አባላት ላይም ተመሳሳይ እስር እንደተፈጸመ ተዘግቧል፡፡


No comments: