Saturday, November 22, 2014

ተቃዋሚዎች - ግብታዊነት እና የሆያሆዬ ፖለቲካ መቆም ያለበት ጉዳይ

November 22,2014
በምንሊክሳልሳዊ‬
ከመጠላለፍ ከወሬና ሃሜት ከሴራና ደባ ይልቅ እስትራቴጂ ያለው የፖለቲካ መስመር መከትል ወሳኝ ነው::

‪ሃገሪቷ ህገ መንግስት አላት ቢደሰኮርም በስርኣት አልበኞች እየተጣሰ ህግ በህግ እየተሻረ እና ባለስልጣናት እየሸረሸሩት አማራጭ የፖለቲካ አመለካከቶች እና አስተሳሰቦች እንዳይንሸራሸሩ እና እንዳይወዳደሩ በማድረግ በህግ የተረጋገጠውን የብዙሃን የፓርቲ ስርኣት እንዳይሰፍን እንቅፋት ቢሆኑም ይህ ደሞ ከስርአቱ አምባገነንነት ጎን ለጎን የተቃዋሚዎች ድክመት ታይቶ የሚወሰድ እርምጃ ነው:: ደህንነቱ ሰራዊቱና ሚዲያው ምርጫ ቦርዱ ህዝባዊ ባልሆኑበት የአንድ ፓርቲ ወገንተኛ እና አገልጋይ በሆኑባት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊ እና ነጻ ምርጫ አለ የሚል እምነት በፍጹም የለኝም:: ስለወያኔ ምርጫ እና በምርጫው ስለመሳተፍ የፓርቲዎቹ መብት ቢሆንም ሕዝቡ እምቢኝ ብሎ አደባባይ እንዲወጣ ለማድረግ በጋራ እንዲሰሩ ይህንን ለመናገር እወዳለሁ::

ብቁ እና ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አለመገኘቱ -የአገር ጉዳይ የአንድ ሰሞን ሆሆይታ እና ትኩሳት ተከትሎ ማውራቱ በፖለቲካ ሴራ እና ጠልፎ መጣል አባዝ የተሞሉ -ፖለቲካ የትርፍ ሰአት ስራ- መሆኑ ያልበሰሉ ስሜታዊ እና የፖለቲካ ስልታዊ እውቀት ያሌላቸው በፓርቲዎች ዙሪያ መሰባሰባቸው - በሚገባ የተደራጀ፣ አቅሙን እያጎለበተና ለሕዝቡ የተሻለ አማራጭ የሚያቀርብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖር የፓርቲዎቹ አባላት እና ካድሬዎች አንድ ስትራቴጂ ሳይኖራቸው በነፈሰበት እየነፈሱ በጥቂት ድላሮች እየተሽከረከሩ አቧራ ከማጨስ ውጪ አንድ ባልፈየዱበት ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ለመፍጠር በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ሆን ተብሎ በሚፈጠረው መንቀራፈፍ የወያኔን እድሜ ማስረዘማቸው በጎሳ ፖለቲካ የሚናጠው የዲያስፖራው ዶላሮች የሚፈጥሩት ግብታዊ ተጽእኖዎች በኢትዮጵያ የሚፈለገውን ለውጥ አለማምጣቱ የታወቀ ጉዳይ ነው::ሰበብ የማያጡት ተቃዋሚዎች ይህንን ማድረግ ያልቻልነው ወያኔ እንዳንጠናከር እያዳከመን እያንገላታን እያሰረን ነው ቢሉም ይህንን አሰራር የወያኔው ጁንታ እንዲቀይር መስዋትነት ለመክፈል ምንም ያደረጉት ነገር የለም::

በእርግጥ የወያኔው ጁንታ በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ ድርጅቶቹ እንዲቀጭጩ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሚናውን እየተጫወተ ነው:: ሆኖም ግን ተቃዋሚዎች ከታጋይነት ይልቅ ባለፈ ታሪክ የመኮፈስ- እርስ በእርስ የመወቃቀስ- ያለፉትን ስርኣቶች የመናፈቅ-ህዝብን በታሪክ ስም ለመደለል መሞከር-ከመስዋትነት ይልቅ ለጥቅም መገዛት-መረጃ መሸጥ -ለስልጣን መጓጓት የመሳሰሉት ድክመቶች ያሉባቸው ሲሆን ስሜታዊ እና ያልበሰሉን ሰብስቦ ቲፎዞ በማድረግ መንጠራራትም ያልቀረፉት ችግራቸው ነው::የወያኔ ተጽእኖ እና ጫና እዳለ ድርሻው ሳይካድ መጀመሪያ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል::በውስጣቸው የሚታየውን ችግር ቢያድበሰብሱትም በአደባባይ እያየነው ያለ ጉዳይ ነው፡፡

አንድ ፓርቲ ከተለመደው ስልት ወጥቶ በአዲስ ስትራቴጂ ራሱን ሲገነባ ከፓርቲው ውጪ ያሉ ስለ ፓርቲው ምንም አይነት እውቀቱ እና ግንዛቤው የሌላቸው አባል ያልሆኑ የጠልፎ መጣል ኋላቀር ፖለቲካ ተጠቅመው ፖለቲካው አዲስ ባህል እንዳይኖረው ለመጠላለፍ እና ለማልፈስፈስ ትራካቸው ላይ ከመሮጥ አልፈው ከሴራ ፖለቲካ፣ ከሀሜት፣ ከወሬ አውጥተን መሬት በረገጠ፤ በእስትራቴጂ የሚመራ እውነተኛና ዘላቂ ፖለቲካዊ ምህዳር እንፈጥራለን ያሉት ፓርቲዎች ለማክሸፍ እየተራውጡ ነው። የአንድ ወቅት ሆያሆዬ በየጊዜው በህዝቡ ላይ የፈጠረው አጉል ተስፋ ህዝቡ የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ በዓይናችን እያየን ነው፤ ይህ ሁሉ የመጣው ፖለቲካው በስልትና በእስትራቴጂ ሳይሆን በግብታዊነት የሚመሩ ፖለቲከኞች በመብዛታቸው ነው።

ተቃዋሚዎች ራሳቸው ቆራጦች፣ ጠንካሮች፣ ቅኖችና ለመስዋዕትነት ዝግጁዎች ቢሆኑ ኖሮ ከዚህ በላይ የተጠናከሩ ይሆኑ ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከባድ እና ሊቃለል እንኳን ያልቻለ የመንግስት ጫና ....ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው በተሰገሰጉ የወያኔ ሰላዮች የታጠሩ ናቸው::ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአንድነት ችግር ....ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአደረጃጀት ችግር ...ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአመለካከት ችግር ...ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ የዲሞክራሲ ችግር.....ተቃዋሚ ፓርቲዎች የደጋፊና የአባል ብዛት ችግር ....ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፋይናንስ አቅም ችግር ... ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ መስመር፣ የስትራቴጂና የታክቲክ ችግር አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግሮችን የሚፈቱበት መንገድ ራሱ ችግር አለበት፡፡

ተቃዋሚዎች ከዚህ በላይ ለተተቀሱት ነገሮች አትኩሮት መስተት እና ማስተካከል አለባቸው ስሜታዊነት እና የሆያሆዬ ፖለቲካ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው::በውስጣቸው ያለውን አንድነት ማጠናከር እና የስርኣቱን ተላላኪዎች ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል:: የአደረጃጀት መዋቅራቸውን ማስተካከል በበሰሉ እና ወደፊትን ግብ በሚያደርጉ ጠንካራ እና ብቁ ፖለቲከኞች መታጠር አለባቸው:: አመለካከታቸውን ካረጀ እና ከታሪክ ምርኩዝነት አውጥተው በሰለጠነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሳቸውን ማስተሳሰር እና አማራጭ ሃሳቦችን በማሸራሸር ጠንካራ ብሄራዊነት መፍጠርና ለላሸቀው የዲያስፖራው ፖለቲካ ፊት አለመስጠት ስለ ፖለቲካ እውቀት ያሌላቸው ሰዎች በደመነፍስ ፖለቲከኛ እየሆኑ መምጣት የፖለቲካ ስትራቴጂ እና ታክቲክ እንዳይኖር አድርጓል:: ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች በጥራት እና በአጽንኦት አትኩሮት ከተሰጠባቸው ትግሉ ሊያብብ ይችላል:: ከዚህ ውጪ አሁን ባሉበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች ከቀጠሉ የወያኔን እድሜ ከማስረም ዉጪ ምንም ፋይዳ የለውም::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

No comments: