Thursday, October 24, 2013

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ከማስረጃ አልባ ፍረጃ እንዲላቀቁ አንድነት አሳሰበ

October 23/2013

 አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ካለፈው ስህተታቸው በመማር ከአጉልና ማስረጃ አልባ ፍረጃ እንዲላቀቁ አሳሰበ። ፓርቲው ከትናንት በስትያ ባወጣው መግለጫ እንደገለፀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመሪ ደረጃ በማይጠበቅ መልኩ የአንድነትን እንቅስቃሴ ስም ለማጥፋት በመሞከራቸው ከዚህ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸው አጀንዳ የላቸውም፣የሻዕቢያ መልእክት አድራሾች ናቸው ያሉት የራሳችን አጀንዳ እንዳለን ጠፍቷቸው ሳይሆን ሆን ብለውና አቅደው ስም ለማጥፋት እንዲሁም ህዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ ለመጫር በመፈለግ ነው ብሏል።

ፓርቲው ተላላኪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ይጠቅማል ብሎ ለቀረፃቸው የፖለቲካ ፕሮግራም ብቻ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፤ እንዲህ አይነቱን ስም ማጉደፍም በቸልታ እንደማያልፈው ገልጿል። በተጨማሪም የሙስሊም ወገኖችን ጥያቄ በተመለከተ ፓርቲው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ይመለስ፣ ዜጎች የመብት ጥያቄ ሲያነሱ መፈረጁ ይቁም እንዲሁም ካለአግባብ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ በማንሳታቸው ወደ እስር ቤት የተወረወሩ ዜጎች በአስቸኳይ ይፈቱ የሚል ጥያቄ ማንገቡን ፓርቲው ገልጿል። በመሆኑም ፓርቲው ከኢፍትሃዊት ጋር እንደማይደራደር እና እንደማይቀበለው አመልክቶ፣ ፓርቲውን ከሙስሊም ወገኖች ጥያቄ ጋር በማያያዝ ትርፍ ፍለጋ መሯሯጥ ወንጀል ነው ብሏል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተ የተናገሩት በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን መብት በአደባባይ የጨፈለቀ ነው ብሏል ፓርቲው። ሰላማዊ ሰልፍ ለሚያደርጉ በቂ ጥበቃ የለንም በሚል ተልካሻ ሰበብ የዜጎችን መብት መንጠቅ እንደማይቻል የገለፀው ፓርቲው፤ ጥበቃ ማድረግ ያልቻለ መንግስትም ስልጣኑን ለህዝብ በማስረከብ ይቅርታ ጠይቆ መሄድ እንጂ ከአሁን በኋላ መብታችሁን አታገኟትም ብሎ መዛት ትዝብት ላይ ይጥላል ብሏል።
 
ፓርቲው አያይዞም የአፍሪካ መሪዎች ተሰብስበው አይ ሲሲ ሊከሰን አይገባም ሳይሆን ማለት ያለባቸው፣ የዜጎቻቸውን እንባ ማበስ እና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ መጣር ነው ብሏል። መሪዎች በርካታ መፍትሄ ፈላጊ ችግሮች ባሉባት አፍሪካ ተሰብስበው እንግደል፣ እንሰር፣ እንጨፍጭፍ፣ ዘር እናጥፋ፣ ዜጎቻችንን እናሰቃይ ግን መታሰርም፣ መከሰስም የለብንም የሚለው አቋም አሳፋሪ በመሆኑ ፓርቲው እንደማይቀበለው ገልጿል። በመሆኑም ዜጎች ላይ ግፍና ስቃይ የሚፈፅሙ ሁሉ ሳይውል ሳያድር ወደ ፍርድ መቅረብ አለባቸው በማለት፤ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች አይሲሲን በተመለከተ የሚያራምዱትን የአትክሰሱን አቋም ፓርቲው እንደማይቀበለውም ገልጿል።

No comments: