Tuesday, July 21, 2015

የወያ ኔ ኢህአዴግ ስርዓት ልማታዊ መንግስት ሊሆን አይችልም!!

July 21,2015
editorail amharic
ከአሰልቺ የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ፕሮፖጋንዳ አንዱ በአሁኑ ግዜ በአገራችን ውስጥ ፈጣን ልማት ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂ መቀየሱና ተአምራዊ ለውጥ እንዳመጣ ተደርጎ የሚነገረው ነጭ አሉባልታ መሆኑን አጠቃላይ የአገሬው ህዝብ ፍንትው አድርጎ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ኢህአዴግ በአገራችን ላይ ላሰፈነው አገዛዝ ተቀባይነት ዋነኛ መከራከሪያው “ለኢትዮጵያ ልማትን ያመጣሁና አሁንም በማምጣት ላይ ያለሁ መንግሥት ነኝ፤ ለወደፊቱም ኢትዮጵያን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመራና ቀልጣፋ ልማትን ማረጋገጥ የሚችል ሃይል ባለመኖሩ ለኢትዮጵያ  ሲባል  እኔ  ለረዥም ጊዜ  በስልጣን መቆየት አለብኝ በሚል ማደናገርያ ቃል መልዕክቱን ሲያስተላልፍ በተደጋጋሚ አየሰማነው ነው።
በዛሬቷ ኢትዮጵያ መብራት ሲቋረጥ፤ ውሃ ሲጠፋ፤ እህል ሲወደድ፤ መንደሮች ሲፈርሱ፤ የመኪና አደጋ ሲበዛ፤ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ፤ ሰበቡ ልማት ነው? ለረሀብ፤ ለጥማት፤ ለበሽታ እና  መሰል መጥፎ  ነገሮች ልማትን እንደ ምክንያት ሆኖ  ሲቀርብ፤ “መብቴ ይከበርልኝ ብሎ መጠየቅ “በፀረ-ልማትነት” ሲያስከስስ። ባገራችን ልማት ያረጋገጠ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መኖሩን የሚያመለክት ነው? ፍፁም አይደለም! የኢኮኖሚ ልማት። … በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት፤ በዋና ዋና መሠረተ ልማት አቅርቦቶች፤ በአካባቢው ገበያ በሚኖር ተወዳዳሪነት፤ በምቹ የተፈጥሮ አካባቢ፤ በማኅበራዊ መስተጋብር፤ በጤና፤ በደህንነት፤ በትምህርት’ና በመሳሰሉ ነገሮች እድገት ማምጣትን ያካትታል።
የኢኮኖሚ ልማት የአንድ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፤ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ ደህንነት የሚሻሻልባቸው ሂደቶችና ፖሊሲዎችን ያካትታል። ልማት በቁጥር የሚለካ ብቻ ሳይሆን። በቁጥሮች መለካት የሚቸግር ገጽታ  አለው። እንዲያውም የልማት ዋነኛ ግብ በቁጥሮች ለመለካት አስቸጋሪ የሆነውን “ደስተኛ  ማኅበረሰብን” መፍጠር ነው።
ልማት ማለት የአብዛኛውን ሕዝብ የዛሬ ኑሮ እና የነገ ተስፋው ላይ ተጨባጭ አዎንታዊ  ለውጥ መፍጠር ነው። ይህም በአመጋገባችን፤ በጤናችን፤ በአለባበሳችን፤ በምናገኘው ትምህርት መጠንና ጥራት፤ በሚሰማን የራስ መተማመን ስሜት፤ በምናገኘው ፍትሃዊ ዳኝነት፤ በማኅበረሰቡ ባለው የመግባባት መጠን፤ በሚሰማን የነፃነት ስሜትና ባጠቃላይ የልማት መጨረሻው ግቡ የህብረተሰቡን ድህነት መቀነስ እንጂ ሀብታሙን ይበልጥ ቱጃር ማድረግ አይደለም።
የልማት ትክክለኛው ትርጉም ያልገባው ገዢ የኢህአዴግ መንግስት! ልማት ማለት እንጀራ መጋገር ብቻ ሳይሆን የጋገሩትን እንጀራ የመብላትንም መብት ያጠቃለለ፤ የነገ እንጀራ የማግኘት ተስፋ አሻግሮ የሚመለከት በቁሳዊ ሃብቶች ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ ባልሆኑ ሃብቶችም ጭምር የሚለካ መሆኑና፤ ልማት ማለት የዛሬ ነፃነትና የነገንም ተስፋ እንደሆነ  ጠንቅቆ የተረዳው አይመስልም።
የወያኔ-ኢህአዴግ ነጋ ጠባ አስመሳይ “የልማት ጋጋታና የማደናገርያ ቃላቶች ሃቅን ለማድበስበስ ታስበው በተፈበረኩ አሃዞች የሚገለፁ መሆናቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቋል። በአገራችን ውስጥ ዛሬ ድህነትና ስራ አጥነት በዝቷል፤ ፍትህና ነፃነት የለም፤ የህዝቡ ክብርና ስብዕና አልተረጋገጠም፤ የትምህርት ጥራት አሳፋሪ ደረጃ ላይ ወድቋል፤ ስደት ተሰምቶ ወደማይታወቅ ደረጃ ደርሷል፤ ሙስና ተቀባይነት ያለው አሠራር ሆኗል ወ.ዘ.ተ….. ስፍር ቁጥር የሌለው ችግሮች ማንሳት ይቻላል።

የመብት ጉዳይም ቢሆን በጥቂት ፀረ ህዝብ አገዛዝ መሪዎች ምክንያት ሕዝቦች በግፍ የሚሰቃይበትና በባዶ ውንጀላዎች እስር ቤት ውስጥ ገብቶው የሚማቅቁበት ሁኔታ ላይ መሆኑን ይታወቃል። ስለዚ ወያኔ ኢህአዴግ ከኔ የተሻለ መንግስት አታገኙም እያለ በህዝቡ ላይ እየቀለደና ህዝቡን እያደናገረ የስልጣን ቆይታውን ለማስረዘም ላይና ታች እያለ ባለበት ሰዓት ስርዓቱ ትርጉም ያለው ልማት ማረጋገጥ ይችላል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይደለም።

No comments: