በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስልጥኖ አሰማርቷችኋል” ተብለው እንደተለመደው በሀሰት የተከሰሱ ወገኖቻችን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መከላከያ ምስክር እንዲሆኑን ይታዘዝልን“ ብለው ሲጠይቁ ዳኛ ተብየው “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ ብይን ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስር አያያዝ ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ወቅት በህወሓት አገዛዝ በተሾመ ዳኛ “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ” መባሉ አሳሳቢ ጉዳይ አድርጎ ይመለከተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተከሳሾች፣ የአቃቤ ህጉና የዳኛው ምልልስ ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለእንግሊዝ መንግሥት እንዲደርስ እንዲያደርጉም ያሳስባል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ሳይሆን በህወሓት እስርቤቶችና ከእስር ቤቶች ውጭ ባልታውቁ ቦታዎች ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ የሚወጣው፣ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ራሳችንን፣ ወገኖቻችንና አገራችን ነፃ ለማውጣት የምናደርገው ትግል ማጠናከር ግዴታችን ነው። እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ነፃነታችንን አያጎናጽፈልንም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሓትን እኩይ ተግባራት በዓለም አደባባዮች ማጋለጥ፤ የህወሓት አገዛዝን ወዳጅ ማሳጣት እና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ደህነት የሚያሻሽሉ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ተግባር በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ በህወሓት እጅ ለወደቁ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚያሰሙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment