Saturday, July 18, 2015

ኢትዮጵያ ከ184 አገራት 171ኛዋ ደሃ አገር!

July 18,2015

“ኢኮኖሚ በመንገድና ፎቅ ሥራ አይለካም”
women carrying

ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የአምስት ዓመታት አኻዝ ያካተተ የዓለማችንን ሃብታምና ደሃ አገራት ዝርዝር ሰሞኑን አውጥቷል፡፡ የዓለም የፋይናንስ መጽሔት ላይ የታተመው ይኸው ዘገባ እንደሚያሳየው በሃብታምና ደሃ አገራት መካከል ያለው ልዩነት በእጅጉ እየጨመረ እንደመጣ ነው፡፡ በዚህ የአምስት ዓመት አኻዛዊ ዘገባ መሠረት ከ184 አገራት መካከል ኢትዮጵያ 171ኛ ተራ ላይ የምትገኝ ስትሆን ይህም በድህነት ከሚጠቀሱት ቀዳሚ አገራት ቁጥር ውስጥ አስገብቷታል፡፡ ዘገባውን የተመለከቱ የኢኮኖሚ ባለሙያ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በከተሞች ውስጥ በሚሰራ ፎቅ ብዛት እና የመንገድ ሥራ አይለካም ይላሉ፡፡ ሌላ የኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ “ኢኮኖሚ ከቁጥር ሌላ ሥነ ልቦናዊ ጉዳይም ነው፡፡ የኑሮ ጉዳይም ነው፡፡ የጉሮሮ ጉዳይም ነው፡፡ በቁጥር ብቻ አይለካም፡፡ … የሕንፃ መሐንዲስ ቢሳሳት ሕንፃ ይደረመሳል፡፡ የሰው ኑሮ መሐንዲስ ሲሳሳት ግን ሕይወት ይጠፋል፣ ሕዝብ ያልቃል፣ ትውልድ ይረግፋል፣ አገር ይበጠበጣል፡፡ በዓይናችን እያየነው ነው” ይላሉ፡፡
ይፋ በሆነው ጥናት እንደተገለጸው ደረጃው የወጣው በተለይ ሁለት የኢኮኖሚ መለኪያዎችን በማቆራኘት ነው፡፡ እነዚህም የአገር ውስጥ ምርት (GDP) በካፒታል የሚባለውንና የመግዛት ኃይል ንጽጽር (purchasing-power-parity (PPP) በማጣመር ነው፡፡ በቀላል አገላለጽ PPP ማለት ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን የተወሰኑ የተለመዱ ሸቀጦችን (ለምሳሌ ዳቦ፣ እርሳስ፣ የብርቱካን ጭማቂ፣ ወዘተ) ሰብስቦ በአንድ ቅርጫት ውስጥ በማድረግ ዋጋቸውን መተመን ነው፡፡ እነዚህ በአንድ ቅርጫት ውስጥ የተካተቱት ሸቀጦች አጠቃላይ ዋጋ ኢትዮጵያ ውስጥ 50 ዶላር ቢሆን ኬኒያ ደግሞ 100 ዶላር ቢሆን በኢትዮጵያና በኬኒያ መካከል ያለው የመግዛት ኃይል ንጽጽር 1፡2 (አንድ ለሁለት) ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ቀመር ከአጠቃላይ የዓለም አገራት ጋር በማነጻጸር የአንድን አገር ሕዝብ የመግዛት አቅም ከመላው ዓለም አገራት ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡ ጥናቱ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡
በኢኮኖሚክስ ጥናት መሠረት የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒን) መለኪያዎች በርካታ ናቸው፡፡ አንዱ ምርቱን ለማምረት በወጣው የመለካት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከዋጋ ንረት ጋር በማገናዘብ የመለካት ስልት ነው፡፡ ይህ ጥናት የተጠቀመበት መለኪያ ደግሞ ጂዲፒን በካፒታል መለካት ሲሆን ይህም የአንድ አገር ገቢ በነዋሪው ሕዝብ ተካፍሎ የሚመጣው ነው፡፡ የጥናቱ አቅራቢዎች ይህንን የጂዲፒ ውጤት ከመግዛት ኃይል ንጽጽር ጋር በማካፈል ነው መረጃውን ይፋ ያደረጉት፡፡ ይህ ዓይነቱ የመግዛት ኃይል ንጽጽርን ግምት ውስጥ ያስገባ የጂዲፒ አለካክ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት በስሌቱ ውስጥ የሚያካትት በመሆኑ ከሁሉም የጂዲፒ መለኪያዎች የተሻለ ነው የሚል አስተያየት ይሰጥበታል፡፡
economic map
Darkest red: highest GDP per capita (PPP) Medium red: medium-high GDP per capita (PPP) Light red: medium-low GDP per capita (PPP) Lightest red: lowest GDP per capita (PPP)
በእነዚህ የኢኮኖሚ ስሌቶች መሠረት የተደረገው የአምስት ዓመታት ጥናት (እኤአ 2009-2013) እንዳመለከተው በዝርዝሩ ከተካተቱት አገራት ኢትዮጵያ 171ኛ ተራ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ ኳታር በአንደኛነት ስትገኝ ሉግዘምበርግ ሁለተኛ፣ ኖርዌይ ሦስተኛ፣ ብሩናይ አራተኛ፣ ሲንጋፖር አምስተኛ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስድስተኛ፣ አሜሪካ ሰባተኛ፣ ሆንግ ኮንግ ስምንተኛ፣ ስዊትዘርላንድ ዘጠነኛ፣ ኔዘርላንድስ አስረኛ ተራ ላይ ሰፍረዋል፡፡ በዘገባው ላይ እንደተጠቀሰው የእነዚህ አገራት በካፒታል ላይ የተሰላው የ2013 ዓም ጂዲፒ ከመግዛት ኃይል ንጽጽር ጋር ተካፍሎ የተገኘው ውጤት በአሜሪካ ዶላር የሚከተለው ነው፡፡ ኳታር $105,091.42፣ ሉግዘምበርግ $79,593.91፣ ኖርዌይ $56,663.47፣ ብሩናይ $55,111.20፣ ሲንጋፖር $61,567.28፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ $49,883.58፣ አሜሪካ $51,248.21፣ ሆንግ ኮንግ $53,432.23፣ ስዊትዘርላንድ $46,474.95፣ ኔዘርላንድስ $42,493.49፡፡ ይህ ማለት አንድ አገር የምታመርተውን አምርታ፣ የኑሮው ውድነት ተሰልቶ እና በዚያች አገር ውስጥ ያሉት ሸቀጦች የሚያወጡት ዋጋ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ተነጻጽሮ አንድ ሰው ሊኖረው የሚችለው የገንዘብ መጠን ተብሎ በግርድፉ ሊወሰድ ይችላል፡፡ (ማሳሰቢያ፡ እዚህ ላይ ለማሳያነት የ2013 ዓም ብቻ በማውጣታችን የቁጥርና የደረጃ ልዩነት ይታያል፡፡ ይህም የሆነው የአንዳንዶቹ አገራት ዘገባ የተወሰደበት ዓመት ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ ነው፡፡ ሙሉውን ዘገባ እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል)
በድህነት ከሰፈሩት አገራት ተራ የምትመደበው ኢትዮጵያ (171ኛ $1,258.60) በበርካታ የአፍሪካ አገራት ተቀድማለች፡፡ ሴራሊዮን 170ኛ ($1,559.95)፣ ማሊ 168ኛ ($1,136.77)፣ ጊኒ ቢሳው 166ኛ ($1,268.46)፣ ኮሞሮስ 164ኛ ($1,296.77)፣ ሩዋንዳ 162ኛ ($1,591.71)፣ ዑጋንዳ 160ኛ ($1,459.62)፣ ታንዛኒያ 159ኛ ($1,670.21)፣ ዛምቢያ 158ኛ ($1,841.64)፣ ኬኒያ 156ኛ ($1,884.57)፣ ቻድ 155ኛ ($2,061.63)፣ ሱዳን 144ኛ ($2,550.10)፣ ናይጄሪያ 141ኛ ($2,883.44)፣ ጂቡቲ 139ኛ ($2,778.25)፣ ጋና 137ኛ ($3,501.53)፡፡
ኮከቡ ያልሰመረለት ትሪሊየን ጂዲፒ በሚል ርዕስ (June 14, 2015) በታተመው ሪፖርተር ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢኮኖሚ ባለሙያ ጌታቸው አሰፋ በኢትዮጵያ ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታና መጪውን እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡
“ገንዘቡ ዋጋ ያጣው ገቢ አሁንም ቢሆን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ምርታማነት የቀነሰው የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ዕድገት፣ የሥልጠና ዕድል፣ ሙያዊ ክህሎትን መገንባት፣ ወዘተ የሚቻለው አለቃን በማምለክ እንጂ ችሎታን አዳብሮ ውድድር ውስጥ በመግባት ስላልሆነ ነው፡፡ … ሥራ ፈጠራ በብሎኬት ምርት፣ መስኮትና በር መግጠም፣ አልባሳት፣ ቦርሳና ቀበቶን የመሳሰሉ የግል መጠቀሚያዎችን ማምረት ጀምሮ አሁን ወደ ጀበና ቡና፣ ቦርዴ (ሻሜታ) ጠመቃ፣ የዓረብ ሱቅ፣ በቆርቆሮ ግድግዳ ደሳሳ ጎጆ የሆቴል ኪዮስክ ወርዷል፡፡ ከዚህ በታች ወዴት እንደሚወርድ አይታወቅም፡፡ …
“ምርታማ ሆኖ ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ አጭበርብሮም፣ ቀምቶም፣ ሰርቆም፣ የሰው አካልንም ቢሆን ደልሎ ገንዘብ ለማግኘት ይሞከራል፡፡ ውድድር ሳይሆን ሽሚያ ይፈጠራል፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው ይህ አጉል የመስገብገብ፣ የመሻማት፣ የመሻሻጥ ባህሪይ ነው፡፡ ሁላችንም በባህሪይ፣ በአስተሳሰብና መስሎ በመታየት ደላላ እየሆን ነው፡፡ በመንግሥት ድጋፍ በሦስት ሺሕ ብር የፈጠራ ሥራ ጀምሮ በዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ፣ መቶ ሺሕ ብር ለደላላ ከፍሎ ወደ ሞት ለመሄድ መደራደር፣ ለጥቂት ደቂቃዎች መዝናኛ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት፣ ቅጥ ላጣ የውጭ አገር ጉዞ የቅንጦት ወጪ ማድረግ፣ ምልክት የጥሬ ገንዘብ ከጓሮ የሚሸመጠጥ ቅጠል መምሰል ነው፡፡ …
“አምና በመቶ ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል የከተማ ሥራ ጀምሬ ዘንድሮ ሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ በግማሽ ሔክታር መሬት የግብርና ሥራ አሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የወጣቱን ሥነ ልቦና ሰለበ፡፡ የሥራ ባህል ጠፋ፡፡ ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ ሳይሆን ከሜዳ የሚታፈስ ወይም ጓሮ ከበቀለ ዛፍ የሚሸመጠጥ መሰለ፡፡ መቶ ሺሕ በትኖ ሚሊዮን ለማፈስ የተሰናዳ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ ከሠርቶ በሌው አውርቶ በሌውና ዘሎ በሌው በዛ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አቋርጦ ጊታር ማንሳት ተለመደ፡፡ …
“የጋራ በሆነ መሬት ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ መሥራት የሚቻለው በጋራ ብቻ ነው፡፡ የጋራ የሆነም የግል አይደለም፡፡ የግል ያልሆነም ገበያ አይወጣም፡፡ ገበያ ያልወጣም የገበያ ዋጋ የለውም፡፡ የገበያ ዋጋ የሌለውም በገበያ ዋጋ በገንዘብ አይተመንም፡፡ ስለዚህም በሪፖርት ከምናየውና ከሚነገረን የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) መጠን ገሚሱ የገበያ ዋጋ የሌለው ምናባዊ ስሌት ነው፡፡ የኑሮ መሐንዲሱ ኢኮኖሚያዊ ኑሮን ወደ ምናባዊ ሥሌት ከወሰደው የሕዝብ ገቢ መጠንና ኑሮም በገበያ ተለክቶ እውነቱ የሚታወቅ ሳይሆን ምናባዊ ይሆናል፡፡ አመለካከቱና አስተሳሰቡም የኑሮው ነፀብራቅ ነውና ኑሮውን ተከትሎ ምናባዊ ይሆናል፡፡ ሲያገኝም ሲያወጣም በምናባዊ ሥሌት ነው፡፡ ሳይበላ የበላ መስሎ፣ ሳይጠጣ የጠጣ መስሎ፣ ሳይደላው የደላው መስሎ፣ ያላመነውን ያመነ መስሎ፣ ያልተቀበለውን የተቀበለ መስሎ፣ የናቀውን ያከበረ መስሎ፣ የጠላውን የወደደ መስሎ በመታየት በምናባዊ ዓለም ውስጥ ይኖራል፡፡…poor
“ሕዝቡ ከምናባዊ ዓለም ወጥቶ ገሃዱን ዓለም እንዲቀላቀል የኑሮ መሐንዲሱ ኢኮኖሚስት አለ ብሎ በወረቀት ላይ የሚጽፈውን የምርት መጠን ለሽያጭ ወደ ገበያ አውጥቶ፣ በበያ ዋጋ አስተምኖ እውነተኛውን በገበያ ዋጋ የተለካ የምርት መጠን ያሳየን፡፡ ያለበለዚያም የገንዘብ አቅርቦቱ ለገበያ በቀረበው ምርት መጠን ልክ ሆኖ በዋጋ ግሽበት ስቃይ እንዳን፡፡ እኔ እንኳ በሩቁ ከማውቀው ወደ ገበያ ከማይቀርቡና ማገበያያ ገንዘብ ከማያስፈልጋቸው ምርቶች ውስጥ ከጠቅላላ ጂዲፒው አንድ ሦስተኛው የሚሆነው፣ ገበሬው ከራሱ እንደገዛ ተቆጥሮ በምናባዊ ሥሌት በገንዘብ የሚለካው የግብርና ምርት ይገኝበታል፡፡ በወረቀት ላይ የሚመለከቱ የአገር ውስጥ ምርት መጠን ቁጥርና ለፕሮፓጋንዳ የሚያገለግሉ ጥንስስ ፕሮጀክቶች ስም ጋጋታ ሳይሆን፣ የአጠቃላዩ ሕዝብ ምርታማነት ብቻ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነው፡፡…
“አንጀት ላይ ጠብ የሚለው ሺዎች ለሚሊዮኖች አስበውና ተደራጅተው ሲሠሩ ሳይሆን፣ የአጠቃላዩ ሕዝብ ሚሊዮኖች ለራሳቸው አስበው በገበያ ውስጥ ተወዳድረው እንዲሠሩ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሲመቻችላቸው ነው፡፡ ‹‹ጧት ጧት ዳቦአችንን ጠረጴዛችን ላይ የምናገኘው በዳቦ ጋጋሪው የፅድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ለራሱ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በሚሠራው ሥራ ነው›› አዳም ስሚዝ፡- ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጠንሳሽ፡፡ ‹‹ልማት ማለት አንድ ሰው ሊሆንና ሊያደርግ የሚፈልገውን ሕጋዊ ነገሮች የመሆንና የማድረግ ነፃነትና አቅም ሲያገኝ ነው›› አማርተያ ሴን፡- በ1998 በልማት ኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ፡፡”
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በፋይናንስ መጽሔት ላይ ያወጣውን ይህንን መረጃ የተመለከቱ በኢትዮጵያ የግል ትምህርት ተቋም የኢኮኖሚክስ ባለሙያ የሆኑ ለጎልጉል እንዳሉት የዴሞክራሲን መንገድ የተከተለችው ጋና ከሌሎቹ የሰሃራ በታች አገራት በከፍተኛ ፍጥነት የማደጓ ምክንያት ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደሚጠቀስ ጠቁመዋል፡፡ የዕድገቷ መጠንም ዘገባው በተጠናቀረበት ባለፉት አምስት ውስጥ ያልተዛባ ነገር ግን ሥርዓት ያለው ዕድገት እያሳየች መሆኗን ጨምረው ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሲናገሩ “አንድ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ያልሆነ ሰው ይህንን ዘገባ በመመልከትና የኢትዮጵያን ደረጃ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ጋር በማነጻጸር ብቻ ለምን ኢትዮጵያውያን ለተሻለ ኑሮ ወደሌሎች አገራት እንደሚኮበልሉ መናገር ይችላል፤ የአገራችን ሕዝብ ያለው አቅም እጅግ የወደቀ በመሆኑ በአቅም ከምትበልጠን ጂቡቲ መሰደድ እንደ አማራጭ ሊወሰድ ይችላል” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም “እንደ ባለሙያ ለመንግሥት አካላት የኢኮኖሚውን ጉዳይ ስናስረዳ የሚሰማን የለም፤ ከዚያ ይልቅ እንደ ካድሬ ፕሮፓጋንዳ እንድንናገር፣ ኢኮኖሚው በድርብ አኃዝ እንዳደገ እንድንደሰኩር፣ ወዘተ ነው የሚፈለግብን፡፡ ሃቁ ግን ይኸው በገሃድ የሚታይ ነው፤ የአንድ አገር ዕድገት በበርካታ የኢኮኖሚ መመዘኛዎች በሳይንሳዊ መንገድ የሚለካ ነው እንጂ በዘጋቢ ፊልም በታጀበ የመንገድ ሥራና የፎቅ ብዛት ጨርሶውኑ ሊሆን አይችልም፤ ምናልባትም ካልተሳሳትኩ በዓለም ላይ ኢኮኖሚዋን በመንገድ ሥራና በፎቅ ብዛት የምትለካ አገር ኢህአዴግየሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም” ብለዋል፡፡ethio poor
የኢኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው አሰፋ ሪፖርተር ላይ ያወጡትን ጽሁፍ ሲያጠናቅቁ እንዲህ ይላሉ፤ “የአገር ውስጥ ምርት በግሳንግስ ምርቶች ማበጡ የምርታማነት ማደግ አይደለም፡፡ ያበጠ ነገርም ይፈርጣል፡፡ ኢኮኖሚ ሲፈርጥ ደግሞ ማኅበራዊ ቀውስ ያመጣል፡፡ ‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል› ተረት እንዳይተረትብን፡፡ የብሔራዊ ገቢ ሒሳብ ባለሙያው በተቀመጠለት የማዕከላዊ ዕቅድ የጊዜ ገደብ አገሪቱን በእጁም በእግሩም ገፍቶ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማድረስ አስቦ፣ በነፃና በጋራ የሚሠራውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በምናባዊ ሒሳብ የአገር ውስጥ ምርት ሥሌት ውስጥ አካቶ ሊሆንም ይችላል ምርቱን ያሳበጠው፡፡ ኢኮኖሚ ከቁጥር ሌላ ሥነ ልቦናዊ ጉዳይም ነው፡፡ የኑሮ ጉዳይም ነው፡፡ የጉሮሮ ጉዳይም ነው፡፡ በቁጥር ብቻ አይለካም፡፡ እንደ ዶሚኖ ጨዋታ ቁጥር በመገጣጠም ብቻም የሚገነባ አይደለም፡፡ የሕንፃ መሐንዲስ ቢሳሳት ሕንፃ ይደረመሳል፡፡ የሰው ኑሮ መሐንዲስ ሲሳሳት ግን ሕይወት ይጠፋል፣ ሕዝብ ያልቃል፣ ትውልድ ይረግፋል፣ አገር ይበጠበጣል፡፡ በዓይናችን እያየነው ነው፡፡”
ይህንን ዓለምአቀፍ የደረጃ ዘገባ በመመርኮዝ እኤአ እስከ 2020 ድረስ ይህ የደረጃ ስሌት እምብዛም ለውጥ ሳያሳይ እንደሚቀጥል በርካታ ትንበያዎች አሉ፡፡ በሌሎች ደግሞ ምናልባትም በዝቅተኛው ተራ ላይ የሚገኙት አገራት እጅግ እየደኸዩ በሃብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ለከፍተኛ የማኅበራዊ ቀውስ እየተጋለጡ ይሄዳሉ የሚል ሙያዊ ስሌትም ይሰጣል፡፡ (ፎቶ: ከኢንተርኔት የተገኙ በጎልጉል የተገጣጠሙ)
ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተወሰደ

No comments: