![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEgZns02tEpL6g-0cWYqgQgK4y3UBw5LNucoBTfr68YJqvDOMinzxiTzzEWBO7rpQAWX-7Pu6ZfAT83MKYC-LxmNs47M5E-0TWNsty7Up0z82jE97Z7hItF5zXZk5Rz5_xsHPvy8whyphenhyphen5E-E/s200/Benji+article+pic+7.jpg)
አሁን አሁን እጅግ እየከፋ የመጣው የወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ ፀረ ዴሞክራሲ እና ፀረ ሰላም መሆኑ በይበልጥ ግልጥ እየሆነ ከቀን ወደ ቀን እየተሰፈረ ያለው የግፍ ፅዋ ሞልቶ የመፍሰሱ ጉዳይ አለም ሁሉ የሚያውቀው የወቅቱ ዘገባ ነው። የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየጋመ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም አቅጣጫ መከራና ግፍ እየተቀበለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ወያኔ ባቡር አሳይቶ ህዝብን ለማሳቅ መሞከሩ ትውልድን እንደህጻን ቆጥሮ በብልጭልጭ ነገር እያባበሉ ማስተኛትን ይመስላል። መጽሀፍ ስለ ሰይጣን ሲናገር እንደ ብርሀን መልዐክ ለመግደልና ለማሳሳት ራሱን ይለውጣል ይላል። ታዲያ ቢያብለጨልጭ ለመግደል ብቻ መሆኑ ደግሞ ሊታሰብበት ይገባል።
ስለ ሶርያ ጥቂት ነገር እናንሳ። ጥንታዊ እና ስልጣኔ የጀመረባት ሀገር እንደነበረች በከብት እርባታ እና በእርሻ ዘመናዊ ሁኔታዎች የበቀሉባት ስለመሆንዋ ተወስቶላታል። ቀደምት ተብላ እንደመጠራቷም ሀገሪቷ ከ100 አመታት በፊት በቱርክ ግዛት ስር ሆና ደማስቆን እና የቤሩትን የወደብ ከተሞች የሚያካልል ሀዲድ ተዘርግቶ የባቡር መጓጓዣ አገልግሎት ተጠቃሚም ሆናለች። ከዚያም በመነሳት ነጻነቷን አውጃ ራስዋን ማስተዳደር ስትጀምር የዛሬ 60 አመት በፊት 1956 እ.ኤ.አ ሞደርን ሲኤፍኤስ ፓሴንጀር ትሬን በማለት አዲስ መዋቅር አበጅታ እስከ 2012 ተገልግላበታለች።አሁን ያ ያላት መልካም ገጽታ እና ታሪኳ እንዲሁም ከሁሉ በፊት ባብር ነጂ መሆናዋ ከመሰባበር አላዳናትም።
የሶርያ ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድ በአንባገነንነት ምድሪቷን መግዛት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ አሁን ድረስ መልኩን ቀያይሮ እና የተለያየ ስም ይዞ ታልቅ እልቂት ያስከተለው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ220,000 ንጹሀን ዜጎች በላይ ለህልፈተ ሞት ያበቃ ሲሆን 11 ሺህ 420 ህጻናት መገደላቸው እና ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የሆነ ዜጋ ሀገሩን ጥሎ በየጎረቤቱ ጥገኛ እና ስደተኛ ሲሆን የፍትህ የዲሞክራሲ ረሀብ እና ናፍቆት እንጂ መንገድ፣ ፎቅ፣ ባቡርና ሀዲድማ ነበራቸው። ዴሞክራሲ የሰፈነበት አገዛዝ እና ስርዓት ምድሪቷን እስካልተቆጣጠራት ድረስ ሁሉም ነገር ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው።
![](https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEh-scirVhIKJVvWrgo5FhlbH0qLkmx5czTKc5vx5hd2JtI6UN_clf-LNxwHIRdnfdwUoUfzJ_JJHQMCohU_GnuhygWGT6I4tFQqhUojHN2aNal9_na7T1_Pm1Vlvl1sKsBT2SjeIUpWpfs/s1600/unnamed.jpg)
የዛሬው ዘመን ላይ ደርሰን ባቡር እና ሀዲዱ ብርቅ ሆኖ ባብር! ባብር !ባቡር እየተባለ ጡርንበኞች ሲጮሁ መስማት ምን ያህል ከፍትህ እና ከሰላም ይልቅ ግኡዝ ነገር አእምሮአቸውን እንደጨመደደው ልብ ይሏል። በምድሪቷ ላይ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የተከሰከሰው የአባቶች አጥንት ለባቡር ለፎቅ እና ለመንገድ አልነበረም። ይልቁንም ለፍትህ ለሉዐላዊነት ለነጻነት እና ለአንድነት ነበር። አሁንም ያ አጥንት ትውልዱን ይወቅሳል። ባቡርማ ብርቅ አይደለም! ኢትዮጵያም ነበራት። ሶርያም ኢራቅም ነድታለች ዳሩ የህዝብ ረሀብ ነጻነት ሆነ እንጂ። ሶርያ ያላት ህንጻ፣መንገዷ፣ባብሯ እና ሀዲዷ ከመበታተን ከመሰባበር አላዳናትም።የሀገር ሀብት ዲሞክራሲ የሰፈነበት አገዛዝ የሆነ እንደሆን ብቻ ሀገር ይለማል። ሀብት እና ንብረታችን ነጻነት እና አንድነታችን ነው። የድል ክንዳችን መያያዛችን እና መቀባበላችን ብቻ ነው።
በወያኔ አለንጋ ደንዛዛ እንዲሆን የተመተተብት ትውልድ አፍዝ አደንግዙን ረግጦ ስለኢትዮጵያው ሊነቃ የሚገባበት ዘመን አሁን ነው። ባቡሩና ሀዲዱ መጥፎ ነው ለማለት አይደለም ስላስፈለገም ነው ከ98 ዓመት በፊት የተገነባው። ድሮስ ወያኔ የራሱን ሆድ ሲያጭቅ ድሆች ከፍርፋሪው ባቡር እና ሀዲድ እንደቡችላ ቢወረውርላቸው ምን ይከፋል። ይህ እኮ የወያኔ ካዝና ውድቅዳቂ እና ፍርፋሪ ነው።ፍርፋሪ ደግሞ ሆድ አይሞላም እንዲያውም ቢያስርብ እንጂ።ይህ ማታለያ ወያኔ ሀፍረቱ እንዳይታይበት የለበሰው ብጣቂና ቅዱስ የመሰለበት ማስመሰያው ነው። ተኩላ በበግ ለምድ እንዲከለል ሰይጣንም አውሬነቱን ለመደበቅ ራሱን እንዲከልል ወያኔም ነፍሰ ገዳይነቱን ለመደበቅ አዛኝ መስሎ የማይበስል ቅቤ ያነጉታል። ለኢትዮጵያ እድገት እና ልማት ለሀገሪቷ ፍቅር ያለው መሪ ህዝብን ነጻ ከማድረግ እና የእኩልነት መንፈስ በምድሪቷ ላይ እንዲሰፍን ከመትጋት ይጀምራል ። ነጻነት የሌለው ህዝብ ፎቅ ላይ ቢወጣ በባቡር ቢሳፈር ዳሩ እስረኞቹ ተሳፍረው እየሔዱ ነው ቢባል እንጂ ሌላ የማታለያ መጠርያ ቢሰጠው በመጫኛ መጣል ይሆናል። እንዶሮዋ።
ዳሩ በግኡዛን ቁሳቁስ ብናምር ብንቆጠቆጥ ማን እርሱን ይጠላል። ግን እርሱ ሐብት አይደለም። አንድ ቀን ይከዳል። ምድሪቷ ድንገት ቢያስነጥሳት አሊያም ብትንጠራራ ከበላይዋ በብድር ገንዘብ ያንጋጠጠው ፎቅም በሉት ባቡር አሊያም ሌላ ግኡዝ የፍርስራሽ ቁልል ሁኖ ለመዛቅ ዕዳ ይሆናል። ስለዚህ ስለብልጽግና ስናወራ ስለ ገንዝብ ካወራን ስተናል ማለት ነው። ገንዘብ ኖሮህ ነጻነት ከሌለህ ፎቅ ገንብተህ በየደቂቃው የወያኔ አባት በጣረ ሞት መንፈስ እየመጣ ካስጨነቀህ ከዚህ በላይ ምስኪንነት የለም። ኢትዮጵያ በለጸገች አሊያም ብሩህ ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሎ ወያኔ ራሱን በራሱ ቢያንቆለጳጵስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ የማባበያ እና የማታለያ ባዶ ዲስኩር ፊቱን ሊመልስ እና ሊነቃ ግድ ነው።
የሀገር ሀብት ፍትህ፣አንድነት፣እኩልነት፣ እና ለአንዲት ሀገር በአንድ ክንድ ለሀገር ሉአላዊነት የቆመ አንድ ህዝብ እንጂ ብሩም ወርቁም ነጻ ባልወጣ ሀገር አያምርም! አያደምቅም! የውሸት ነው። በአዲስ አባባ ላይ ብቻ የታየው ብልጭልጭታ ህጻኑ እንዳያለቅስ የተሰጠው ማታለያ ይመስላል። ኢትዮጵያ አዲስ አባባ ብቻ አይደለችም ።
ከቤት እንሰሳት ጋር የውሀ ጥሙን ለመቁረጥ ወደወንዝ የሚርደው ህዝብ፣ ዛፍ ስር በድንጋይ ላይ ተቀምጦ ወጉ እንዳይቀር ሀ ሁ ሂ . . . እያለ ፊደል የሚቆጥረው፣ ለቀዶ ጥገና የ2 አመት ቀጠሮ የሚጠብቁ ታማሚዎች፣በየክፍለሀገራቱ ከልጅነት እስከእውቀት በበጋም በክረምትም መጠለያ ሳይኖራቸው በየጥጋጥጉ ቆሼ ተራ እየተመገቡ ያደጉት ሌላም ቢተረክ ጌዜ የማየበቃው ቁርቁዝና ከሁም በላይ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን እንዳይናገር የታፈነ እና የተለጎመ የታሰረ አንደበት የተጠራቀመባት ምድር ናት ኢትዮጵያ የሚትባለው። ይህች ናት በወያኔ የተቀረጸችው ኢትዮጵያ። ስለዚህም ነው አሁን የመንቃት ጊዜ እንደሆነ የምንናገረው። ኢትዮጵያውያንን እንደ ህጻን በብልጭልጭ ነገር የማታለል የወያኔ ዘመን ያክትም። ሀብታችን ባቡርና ፎቅ ሳይሆን አንድነት እና እኩልነታችን ነው። በመጀመሪያ ነጻነት!!!
እናቸንፋለን !!!
Biniam Gizaw (Norway)
No comments:
Post a Comment