Wednesday, February 18, 2015

ምርጫ ቦርድ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን መሰረዙን ቀጥሏል

February 18,2015
• ‹‹አባላቶቻችን በትግስቱ ደጋፊዎች የእጅ ጽሁፍ በሚቀርብ አቤቱታ በቀጥታ እየተሰረዙ ነው››
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያስመዘገባቸው ዕጩዎች በትግስቱ አወሉ ደጋፊዎች የእጅ ጽሁፍ በሚያቀርቡት አቤቱታ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ እየሰረዛቸው እንደሚገኝ ከተለያዩ የሰማያዊ ፓርቲ መዋቅሮች ለነገረ ኢትዮጵያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡ በደቡብ ወሎ፣ በወላይታ፣ በሲዳማና ጎጃምን ጨምሮ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከአንድነት ፓርቲ አልለቀቃችሁም፣ ንብረት አላስረከባችሁም፣ የሁለት ፓርቲ ዕጩ መሆን አትችሉም›› በሚሉ ምክንያቶች ምርጫ ቦርድ እየሰረዛቸው እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በወላይታ ዞን ዳሞት ወይቴ ወረዳ ምርጫ ጣቢያ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ የትግስቱ አወሉ ተወካዮች ባቀረቡት አቤቱታ ከዕጨነት መሰረዛቸውን የወላይታ ዞን የድርጅ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ታደመ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አቶ ታደመ ‹‹አባላቶቻችን ፎርም ሞልተው፣ መዋጮ እያወጡ ነው፡፡ ምንም አይነት የአንድነት ፓርቲ ንብረት እጃቸው ላይ ሳይኖር በትግስቱ ደጋፊዎች የእጅ ጽሁፍ በሚቀርብ አቤቱታ በቀጥታ እየተሰረዙ ነው›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ፣ በሲዳማ ዞን፣ ምስራቅ ጎጃም ሞጣ፣ ትናን፣ ዲቡኝና ደጀን ወረዳዎች ‹‹ለአንድነት እንጅ ለሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ መሆን አትችሉም ተብለው እንተሰረዙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርቶ የሌሎቹን ፓርቲ አባላት በዕጩነት እያቀረበ ነው›› በሚልም በርካታ ዕጩዎቹ እንዲሰረዙ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል በሲዳማ ዞን የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከምርጫ እንዲወጡ ወከባ እየፈፀሙ እንደሚገኙም የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሰቢ አቶ ደም መላሽ አበራ ለነገረ ኢትየጵያ ገልጸዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ይርባ ከተማ ከንቲባ የሆነው እና ባለቤቱ በዕጩነት የቀረበችው አቶ ኑሩ ቱኪሳ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከምርጫው እንዲወጡ ወከባ እየፈጸመ እንደሚገገኝ የገለጹት አቶ ደም መላሽ አቶ ኑሩ ተኪሳ ይርባ ከተማ ውስጥ ከባለቤቱ ጋር የሚወዳደረውን የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የሆኑት አቶ ተስፋ ማሪያምን ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ወክለህ መወዳደር አትችልም፡፡ እገድልሃለሁ›› እያለ እንደሚያስፈራራው ገልጸዋል፡፡

No comments: