Saturday, December 6, 2014

‹‹የከተማ ጦርነት አውጃችኋል!የተዘጋጀ ኃይል አለን ልካችሁን ያሳያችኋል›› ኮሎኔል ዘውዴ የየካ/ክ/ከ/ፖ/መ/ኃ

December 6, 2014
ሳሙኤል አበበ (በፖሊስ ታግቶ የነበረ)

ትናንት ከቀኑ 10 ሰአት አካባቢ ልክ እንደ ሰሞኑ ሌሎች ጓዶቻችን ላይ ይደረግ እንደነበረው የፖሊስና የደህንነት አፈና ሁሉ ፍቅረማርያም አስማማውን የህወሓት ቅልብ ደህንነትና ፖሊሶች አፍነው ወሰዱት፡፡ እኛም ቢያንስ ያለበትን ቦታ ለማወቅ ከትንታጉ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ጋር በመሆን ፖሊስ ጣቢያዎችን ማሰስ ጀመርን፡፡ የመጀመሪያ መዳረሻ የሆነን የየካ ክ/ከተማ አድዋ ድልድይ ፖሊስ ጣቢያ ሆነ፡፡ እንደደረስንም በር ላይ የነበሩትን ሁለት ፖሊሶች ጓደኛችን በፖሊስ ተይዞ ወዳልታወቀ ቦታ ስለተወሰደ እዚህ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው ስንላቸው ‹‹ልጁ እዚህ ገብቷል፡፡ ግን ምርመራ ላይ በመሆኑ ትንሽ ቆይታችሁ ኑ!›› ተባልን፡፡

እኛም ‹‹ምን አልባት ሊያድር ስለሚችል እራት እናስገባለት›› አልናቸው፡፡ አሁን እኛን አላናገረንም፡፡ በቀጥታ ውስጥ የቆሙት ሁለት ፖሊሶች ጋር ሄዶ አነጋገራቸውና ተመለሰ፡፡ ‹‹አሁን አይቻልም፡፡ ሂዱና ቆይታችሁ ተመለሱ፡፡›› የሚል ትዕዛዝም ሰጠን፡፡ በትዕዛዙ መሰረት ፊታችንን ከማዞራች ሰከንድ እንኳ ሳይሞላ ከውስጥ በጎርናና ድምጽ ‹‹ኑ ተመለሱ! እናንተም ትፈለጋላችሁ፡፡›› በማለት አምባረቀብን፡፡ እኛም ሳናቅማማ ገባን፡፡ ሁለቱም ፊታቸው ላይ ከፍተኛ ጥላቻና ንቀት ይነበብባቸዋል፡፡ የማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ ቃላትን በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡

እኛ ደገሞ ውስጣችን ያለው እውነት ነውና እንዳሰቡት ልንደናገጥላቸው አልቻልንም፡፡ ጓደኛዬ በላይ ማናዬን ‹‹ስትገባ ስቀሃልና ምን እንዳሳቀህ ንገረን!›› አለው አንደኛው ፖሊስ! በላይም ‹‹ይህ የአኔ የግል ጉዳይ ነውና ልትጠይቀኝም፣ ልነግርህም አልችልም›› ብሎ በልበ­ሙሉነት መለሰለት፡፡ ቀጥሎም‹‹ተፈተሹ!›› ተባልን፡፡ እኛም ‹‹ፍ/ቤት ትዕዛዝ ካልተሰጠ በስተቀር ምንም ሰው ሊፈተሸ አይገባምና እኛም አንፈተሸም›› አልን፡፡ እነሱም አስገድደው ፈተሹን! እንዲያውም ‹‹እኛምኮ ህግ እናውቃለን፡፡ እንድፈትሽም የለበስነው የፖሊስ ልብስ መብት ሰጥቶናል፡፡.ወዘተ..›› በማለት ህጉን ሳይሆን ፍላጎታቸውን ነገሩን፡፡

በዚህም ንትርክ መሃል የክፍለ ከተማው ኃላፊ ኮሎኔል ዘውዴ የተባሉ ሰው ግቢውን ዘልቀው እኛ ጋር ደረሱ፡፡ እንደደረሱም ‹‹እነኚህን ልጆች አውቃቸዋለሁ፡፡ ከአንተ ጋር በተደጋጋሚ ቁጭ ብለን አውርተናል፡፡ ግን ሁሌም ያው ናችሁ፡፡ ሊገባችሁ አልቻለም፡፡›› አሉን፡፡ በእርግጥ እኚህ ሰውዬ ጋር ለሚያዚያ 19/06 ዓ.ም የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ የወጡትን የፓርቲውን አባላት ከመንገድ ለቅመው ያሰሯቸውን ልጆች ለመጠየቅ በሄድኩ ጊዜ ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀ እልህ አስጨራሽ ክርክር አይሉት ውይይት ብቻ ቅጥ የሌለው ንግግር እንዳደረግን አስታውሳለሁ፡፡ ያኔ ያሉኝ ‹‹እናንተ ምን ፈልጋችሁ ነው? ልማቱ ተፋጥኗል፡፡ መንገዱ ኮንዶሚኒየሙ፣ ግድቡ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ወዘተ ተገንብተዋል›› በማለት የተሞሉትን ዘከዘኩልኝ፡፡

እኔም ባይሰሙኝም ‹‹እዚህ አገር ያለው ስርዓት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ቀውስ መውጣት ወደማንችልበት አዘቅት ውስጥ እየከተተን እንደሆነ ስነግራቸው etv እንደሚለው ጸረ­ልማት ብለው ከመፈረጅ አልተቆጠቡም፡፡ ዛሬም ከ8 ወር በኋላ ስንገናኝ በአቋማቸው ጸንተው እንዲያውም ከሬድዋን ሁሴን በልጠው አገኘኋቸው፡፡ ከላይ እስከታች እየገላመጡ ‹‹ከእናንተ ጋር እንተዋወቃለን፡፡ የከተማ ጦርነት አውጃችኋል፡፡ ይህ ደግሞ አይቻልም፡፡ ጫካ ግቡና ጦርነት ክፈቱ፡፡ ያኔ የተዘጋጀ ኃይል አለን፡፡ ልካችሁን ያሳያችኋል፡፡›› በማለት የህወሓት/ኢህአዴግን ፍላጎት ነገሩን፡፡ እነሱም እንዳሰቡት ልንሸማቀቅና ልንሰግድላቸው አልቻልንም፡፡ ረዥም ጊዜ ካቆዩን በኋላ ተጠራን፡፡ ስልካችንና መታወቂያችን መንግስቱ የተባለ መጀመሪያ ያገተን ፖሊሲ ይዞት መጣ፡፡ በማዝተዛዘንም ‹‹የያዝናችሁ በአመለካከታችሁ ወይንም እኛ ለአንድ ወገን በመቆም አይደለም፡፡ የያዝናችሁ ለሁላችንም ደህንነት ስንል ነው፡፡ ግን ላንግባባ እንችላለን፡፡›› በማለት አስረዳን፡፡ እኛም መጀመሪያ ዱላ ቀረሽ ንግግር፣ ክብር የሚነኩ ቃላትን ሲተፋ የነበረ ሰው አሁን ይህን ቢለን እንዴትስ ሊገባን ይችላል? ግቢውንም በእኩለ­ሌሊት ለቀን ወጣን፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ልላቸው ወደድኩ፤ በእያንዳንዷ ቀን የምትፈጽሙብን ግፍ ለእኛ ብርታት፣ ትግላችንም አስፈላጊ መሆኑን የበለጠ ያስረዳናል እንጅ እናንተ እንደምታስቡት ይህ ግፍ መቀጣጫ ሆኖን ወደየ ቤታችን ፈጽሞ ልንመለስ አንችልም፡፡ ትግላችን እስከ መስዋዕትነት ደረስ ነው!!

No comments: