Friday, December 5, 2014

በአዳር ሰልፉ ኢህአዴግ “ተሸብሯል”

December 5,2014
በስውርና በግልጽ አፈናው ተጧጡፏል
police 11
* የከምባታ ጠንባሮ ዞን ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ተገለጸ
* የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በፖሊስ ተከብቦ አደረ
የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በፖሊስ ተከብቦ ማደሩንና አባላት ከውጭ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ለአዳር ሰልፉ ቅስቀሳ ዝግጅት ቢሮ ያደሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አመራሮችና አባላቱ እራት በልተው ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት ሲመለሱ ቢሮው በፖሊስ ተከብቦ እንዳገኙትና ወደ ውስጥ እንዳይገቡ እንደተከለከሉ በቦታው የነበሩት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገልጸዋል፡፡
police 14አመራሮችና አባላቱ ፖሊስ ከ200 ሜትር ርቀት ውጭ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤት መጠጋት እንደማይችል ቢከራከሩም ፖሊሶቹ “መመሪያ ተሰጥቶናል፤ አንሄድም!” ማለታቸው ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹና አባላቱ ከፖሊስ ጋር ሲከራከሩ የአካባቢው ህዝብ በመውጣቱ ፖሊሶቹ ፓርቲው ጽ/ቤት እንደራቁ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ከውጭ ወደ ቢሮ ከሚመጡበት ወቅት የፓርቲው ቢሮ አካባቢ ምንነቱ ያልታወቀ ወረቀት ተበትኖ እንዳገኙና እነሱ ሲደርሱ ፖሊሶቹ እንዳነሱት የፓርቲው የምክር ቤት አባል ወጣት እየሩስ ተስፋው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡
*********************
በነገረ ኢትዮጵያ የፌስቡክ ገጽ ላይ የታተመው መረጃ እንደሚያመለክተው ፖሊስና ደህንነቶች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት የሚገቡና የሚወጡ አባላትንና አመራሮችን እያዋከቡ ይገኛሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን “እንፈልጋችኋለን!” በሚል እየያዙ ሲሆን በተለይ ደህንነቶቹ መታወቂያ አሳዩ ሲባሉ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡
ሰማያዊ ቢሮ ጽ/ቤት የሚገኙ ደህንነቶች የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን እያፈኑ እየወሰዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ የሆነውን ፍቅረ ማሪያም አስማማውን አፍነው ወስደውታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የገዥው ፓርቲ ደህንነቶች ተጨማሪ ሰዎችን አፍነዋል፡፡ የነገረ ኢትዮጵያ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የብሄራዊ ምክር ቤት ፀኃፊ ወጣት ሳሙኤል አበበ በደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸውን ነገረ ኢትዮጵያ በዚሁ የፌስቡክ ገጹ ዘግቧል፡፡volunteers of 9 parties
ከጥቂት ሰዓታት በፊት የተሰራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው የአዳር ሰልፉን የጠሩት የ9ኙ ፓርቲዎች ቢሮ በፌደራል ፖሊስ ተከብቧል፡፡ እንዲሁም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አባል የሆነው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቸርቺል የሚገኘው ጽ/ቤት በፌደራል ፖሊስ ተከቧል፡፡ ከሰማያዊ ጽ/ቤት መውጣትም ሆነ መግባት የማይቻል ሲሆን በርካታ አመራርና አባላት ታፍነው ታስረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትብብሩ አመራሮች ስልክ እንዳይሰራ እየተደረገ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ ሊቀመንበር የኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ስልክ እንዳይሰራ ተደርጓል፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በተሰራጨ መረጃ መሠረት የሰማያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ፀኃፊ የሆነው ወጣት አወቀ ተዘራ ወደ ቤቱ በሚገባበት ወቅት በስርዓቱ የደህንነት ኃይሎች ተይዞ ታስሯል፡፡ ፍቅረማሪያም አስማማው፣ አወቀ ተዘራና ተስፋሁን አለምነህን ጨምሮ በደህንነቶች የታፈኑት ወጣቶች የካ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የከምባታ ጠንባሮ ዞን ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ በገዥው ፓርቲ አድሏዊ አሰራር ምክንያት ልማትና መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ የከንባታ ጠንባሮ ነዋሪዎች ዛሬ ህዳር 26/2007 ዓ.ም ዱራሜ ከተማ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን የከምባታ ህዝብ ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዲሎ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ህዝብ ያለ ማንም ቀስቃሽና አስተባባሪ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱን የገለጹት አቶ ኤርጫፎ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አከብራለሁ በሚል ለፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ከማድረጉ ውጭ በተግባር ግን በህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የከንባታና ጠንባሮ ህዝብ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ተቃዋሚዎችን በተለይም የከምባታ ህዝብ ኮንግረንስን ትደግፋላችሁ በሚል በደል እንደሚደርስበት የገለጹት አቶ ኤርጫፎ “ህዝቡ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በደል እየደረሰበት ነው፡፡ ምርጫ ሲደርስ መንገድ፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ይሰራልሃል ይባላል፡፡ ምርጫው ሲያልፍ ለማታለያነት ይሰራሉ የተባሉ ነገሮች ተግባራዊ አይሆኑም፡፡ እስካሁን ከ1993 ዓ.ም አንስቶ ይሰራል የተባለ መንገድ አልተሰራም፡፡ በምርጫ ወቅት አርሶ አደሮችን እያፈናቀሉ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ እንሰራለን ይላሉ፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን ይህ መሬት የሚሰጠው ለሹመኞች ነው፡፡ ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሮች የምርጫ ሰሞን በየቦታው የመሰረት ድንጋይ ተክለዋል፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን ለሹመኞች ይሰጣል፡፡ ዛሬ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣውም ከዚህ አንጻር ነው” ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ ህዝብ ባለፉት ምርጫዎች ተቃዋሚዎችን በመምረጥ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ እንዳሳየ የገለጹት አቶ ኤርጫፎ “ወጣቶች ልማትና የትምህርት እድል ስለማያገኙ ወደ ደቡብ አፍሪካና አረብ አገራት እየተሰደዱ መንገድ ላይ እየሞቱ ነው፡፡ በቀን 11 አስከሬን የመጣበት ጊዜ አለ፡፡ በስርዓቱ አድሏዊ አሰራር ምክንያት ከንባታ ጠንባሮ ወጣቱ ከቀየው እየተፈናቀለ የሚሰደድበት ትልቁ ዞን ነው ማለት ይቻላል” በማለት አስረድተዋል፡፡
በዛሬው እለት አርሶ አደሩ፣ ተማሪውና ነጋዴው የዞኑ ጽፈት ቤት ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረጉም ባሻገር በቀጣይነት በየወረዳዎቹ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚየደርግ ገልጾአል ሲሉ ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ (ለመረጃ ጥንቅሩና ለፎቶዎቹ፡ ነገረ ኢትዮጵያ)
ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተወሰደ

No comments: