Monday, December 1, 2014

ለሀገር ነጻነት የወጣቱ ተሳትፎ ቀጣይነት ይኑረው!

December 1,2014
ከ1997 ምርጫ ማግስት ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣቶችና በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ለሀገራቸው የዲሞክራሲ መብት መከበር እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ላቅ እያለ መምጣቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይህን ተከትሎ ዛሬ ወጣቱ የወላጆቻችን ደምጽ ይከበር፣ ኢትዮጵያዊነት በዘረኝነት አይፈተንም! ነጻነት ዳቦ አይደለም! እስራትና ግድያ በኢትዮጵያ ይቁም! የወያኔ አገዛዝ በቃን! በሚሉ በበርካታ ወጣቶች ጩኸት የወያኔ ሹማምንትና አገልጋዮቹ ላይ የፈጠረው ድንጋጤ ወጣቱን ሽብርተኛ አስደርጎታል።
ወጣቶች ህዝብን አስተባብረው ለተቃውሞ በማሳደም የወያኔን ዘረኝነት በመቃወም ረገድ የተለያዩ ዘዴዎችን ከሌሎች የነጻነት አቢዎት እንቅስቃሴ በመማር እምቢተኝነትን በማሳየት ጅማሮ ላይ ናቸው። ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ የተጀመረው የእምቢተኝነት ዘመቻ በሚቀጥለው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ይቀጣጠል ዘንድ ወጣቱ ሃላፊነት አለበት። ሀገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው መራራ ትግል ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል። አባቶቻችን የውጪ ሀገራትን ወራሪዎች ወራራ ለመመከት ሁሉም ሰው የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ያደረጉት ጥሪ አሁንም ላይ ይሰራል።
ለራሳችን ክብር፣ አንድነት፣ ለሀገር ነጻነትና ህልውና መከበር ኢትዮጵያዊ እምቢተኝነት የሚጀምረው ከትንሽ ነው። ህወሃት በጠላትነት የፈረጃችሁ የዛሬ ወጣቶች የሆናችሁ ዘመን በሚፈቅድላችሁ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በመላው ሀገሪቱ ወረቀት ከመበትን አንስቶ ሌሎች ይትግል ስልቶችን ተጠቀሙ። ኢትዮጵያ ሀገራችሁ በአንድ ጠባብ ዘረኛ ቡድን መዳፍ ውስጥ ማልቀስ ከጀመረች ሰነባብታለች። ዜጎቿ የግለሰብም ሆነ የቡድን መብታቸው ተረግጦ በባርነት እየተገዙ ነው። ጉልበታቸውና ሀብታቸው እየተመዘበረ ሲሆን፤ ለነጻነት፣ ለዲምክራሲና ለፍትህ የጮኹ ሁሉ ሽብርተኛ ተብለው ወደ ማጎሪያ እየተወረወሩ ነው።
ስለዚህ ስለ ሀገራችን፣ ስለራሳችን የግልም ሆነ የቡድን ጥቅም ስንል በሀገሪቱ የትኛውም ከፍል የተጀመረውን የእምቢ አልገዛም ባይነት እንቅስቃሴ እንደግፍ፣ እንሳተፍ! በባህርዳር የተጀመረውን የወጣቶች እንቅስቃሴን አድንቀን ይህ ተነሳሽነት በሌላውም የሀገሪቱ ክፍል መቀጠል ያለበት ነው።
ይህን በማድረግ ወደ ትግሉ በመቀላቀል ካልተሳተፍን በስተቀር ትግላችን አንድ እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ ማድረግ እንደማንችል ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ሁሉም አካላት በያለበት በየሚኖርበት፣ በሚችለው አቅሙ ሁሉ ወደትግሉ በንቃት ተሳተፍ! አብረን ታግለን ነጻነታችንን እናረጋግጥ! ለኢትዮጵያ ትንሳኤ፣ የነጻነት አዋጆች ነጋሪ፣ አብሳሪ ትውልዶች እንሆን ዘንድ ሳንታክት እንታገል ዘንድ ወቅቱ የሚጠይቀው ጥሪ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

No comments: